Friday 16 May 2014

ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

ብዙዎች ኢየሱስ ክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን እንደማትሰብክ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ፤ ነገር ግን ሐዋርያዊት የኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስለክርስቶስ ያላስተማረችበት ጊዜ የለምም አይኖርም፤ ደግሞም እናት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በጊዜያችን አንዳንዶች መናፍቃን የኢየሱስን ክብር አሳንሰው ከአብ በታች አድርገው እንደሚያስተምሩት ሳይኾን በእውነት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብሩ የተካከለ፣ ቅድመ ዓለም የነበረ አኹንም ያለና ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፤ ለፍርድ ዳግመኛ የሚመጣ፤ እውነተኛ ፈራጅ የአማልክት አምላክ የነገሥታት ንጉሥ ነው ብላ የምታስተምረው፡፡ ይኽ ብቻ ሳይኾን ሥጋውን ደሙን በምትሠዋበት በቃል ኪዳን ታቦቱም ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው” (የሕያው የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ) ብላ አክብራ ስሙን ትጽፋለች እንጂ በድፍረት ሆና ስሙን መቀለጃ አታደርግም፡፡
ለምሳሌ ከፍሬ ቅዳሴዋ ውስጥ በዮሐንስ ቅዳሴ ላይም ስለክብሩ ስታስተምር ላይ “ንሰግድ ለከ ወንሴብሐከ ነገረ ጥበብ ወቃለ ምክር መዝገበ ረድኤት ወምሥያመ ትፍሥሕት…” (እንሰግድልኻለን እናመሰግንኻለንም የጥበብ ነገር፣ የምክርም ቃል፣ የረድኤት መዝገብ፣ የደስታም መኖሪያ፣ የጥቅም መገኛ፣ የትንቢትም ምንጭ፣ ደገኛ ፈሳሽ፣ በሐዋርያት የተመሰገንኽ፣ የክብር ጒድጓድ፣ የመንግሥት ጌጥ፣ የካህናት ንጹሕ ዘውድ፣ ዘውዱ የተመሰገነ ንጉሥ፣ የሚሰግዱለት የምስጋና መገኛ፣ የክብር ብርሃን፣ ...የበዛ ምናን፣ ዕጽፍ ድርብ የኾነ መክሊት፣ ዱቄትን የቻለው ዕርሾ፣ አልጫ የኾነውን ያጣፈጠው ጨው፣ ጨለማን ያሳደደው ብርሃን፣ ዓለምን ኹሉ ያበራው ፋና፣ የማይነዋወጥ መሠረትና የማይፈርስ ግንብ፣ የማይሰበር መርከብና የማይሰረቅ ማኅደር፣ የለዘበ ቀንበርና የቀለለ ሸክም ርሱ ለአባቱ ኀይሉ ጥበቡም የሚኾን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ለኹሉ ያስባል፣

ኹሉንም ያጠግባል፣ ለዕውራን ያዩ ዘንድ ብርሃንን ይሰጣቸዋል፣ የተዘጉ መስኮቶችንም ይከፍታል፣ ጽሙማንን ያሰማቸዋል፣ የተደፈነችውን ዦሮ እንድትሰማ ያደርጋል፣ ነፍስን ወደ ሕዋሷ ይመልሳል፣ መንፈስንም በማደሪያዋ ያኖራታል፣ አለቆች ባሏቸው አጋንንት የእሪያን መንጋ ያሰጥማል፣ ከደከመች ሰውነት ደዌን ያርቃል፣ ከክንፍኽ (ከሥልጣንኽ) የእውነት ፀሓይና የጥቅም ምንጭ የሚወጣ የጽድቅ ፀሓይ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንተ ጌትነትና ክብር ምስጋናም ለዘላለሙ ይገባኻል) በማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምትሰብከውን ርቱዕ ትምህርትን በቊርባን ምስጋናው ላይ አስቀምጧል፡፡

ዐምደ ሃይማኖት የሚባለው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር “ለሊሁ በግዕ ወደሙ ወይን፤ ለሊሁ መርዓዊ ወገቦሁ ዐዘቅተ ማየ ሕይወት፤ ለሊሁ መምህር መክስተ አፉ መዐዛ ዕጣን…” (ርሱ ራሱ በግ ደሙም ወይን፤ ርሱ ሙሽራ ጐኑም የሕይወት ውሃ ምንጭ፤ ርሱ መምህር የአፉም ትንፋሽ የዕጣን መዐዛ፤ ርሱ መብራት መስቀሉም መቅረዝ፤ ርሱም የገነት ዛፍ የጸጋውም ወንጌል መዐዛው ያማረ አበባ፤ ርሱ የጽድቅ ፀሓይ ሐዋርያቱም የብርሃን ከዋክብት፤

ርሱ የበረከት ማዕድ ካህናቱም የምስጢር አገልጋዮች፤ ርሱ የቅድስና ልብስ ዲያቆናቱም በልብስነቱ ዘርፍ ኾነው ልብሰ ተክህኖውን የሚከብቡት የወርቅ ጸናጽል፤ ርሱ እረኛ ያመኑበትም የምስጢር በጎች፤ ርሱ ንጉሥ ሰማዕታቱም የመንግሥትን አዳራሽ የሚያስጌጧት ዕንቊዎች፤ ርሱ አውነተኛ የወይን ስፍራ መነኮሳቱም ለሚያዩት ሰዎች ለአይን ያማረ የጽድቃቸውም ፍሬ በሚያነብበው ሰው አፍ የሚጣፍጥ የወይን ዘለላዎች ናቸውና፤

ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን ኹሉ ንጉሥ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠራው ስሙ የጣፈጠ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያዳምጠው ቃሉ የጣፈጠ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚበላው ሥጋው የጣፈጠ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠጣው ደሙ የጣፈጠ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ዜናውን ለሚነግር መታሰቢያው የጣፈጠ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የሰውም ልጅ ነው) በማለት ቤተ ክርስቲያናችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላትን ንጹሑን ትምህርት አስተምሯል፡፡

ይኸው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በማሕፀነ ማርያም ከተከናወነው አንሥቶ በልደት እስከኾነው ታላቅና አስደናቂ ምስጢርን በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ሲገልጸው “ወሶበ ይቤላ መልአክ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ተቀደሰት በርደተ መንፈስ ቅዱስ ለከዊነ እመ አምላክ..." (መልአክ መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል ባላት ጊዜ የአምላክ እናት ለመኾን በመንፈስ ቅዱስ ተለየች ይኽም ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ነው የልዑል ልጅ ይባላል ሲላት ያን ጊዜ ከርሷ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ አስተዋለች (ሉቃ ፩፥፴፭)፤ ኅሊናዋን ወልድ ከአባቱ ጋር ወዳለበት ወደ ጽርሐ አርያም አሳረገች፤ ርሱም ዝቅ ብሎ ከሰማያት ወረደ ራሱንም በማሕፀኗ ውስጥ አሳደረ (ዮሐ ፩፥፲፬)፤

ዳግመኛም ድንግል መልአኩን እንዳልኸኝ ይኹንልኝ አለችው ያን ጊዜ ቃል ከርሷ ሥጋን ተዋሐደ (ሉቃ ፩፥፴፰)፤ አይታ እንዳትደነግጥ ተመልክታም እንዳትፈራ ሰው በኾነ ጊዜ ከርሱ ጋር አራቱን እንስሳውን አላመጣም በሰማይ ሥርዐት የተጠበቁ ሰማያውያኑን በዚያ ተወ (ራእ ፬፥፮-፱)፤ በዚኽም ለቅዱሳን መላእክት የሚረባ ምድራዊት ሥርዐትን ሠራ (ሉቃ ፪፥፲፫)፤ በዚያ በአባቱ ቀኝ አለ በዚኽም በእናቱ ማሕፀን ውስጥ አለ፤ በዚያ ብቻውን የማይታይ ኀይል ነው በዚኽም የማይዳሰስ ኀይል ከሥጋው ጋር የሚዳሰስ ኾነ፤ በዚያ ተሸካሚዎቹ እሳት የተሣለባቸው አራቱ እንስሳ ናቸው (ሕዝ ፩፥፬-፳፮) በዚኽም ተሸካሚዎቹ ለሰውነት መንገድ የተገቡ አራቱ ጠባይዐት ናቸው፤ በዚያ ያለ እናት አባት አለው (መዝ ፪፥፯፤ ዳን ፯፥፲፫-፲፬)

በዚኽም ያለምድራዊ አባት እናት አለችው (ሉቃ ፪፥፯)፤ በዚያ ገብርኤል በፍርሀት ይቆማል (ሉቃ ፩፥፲፱) በዚኽም ገብርኤል በሐሤት የምሥራችን ይናገራል (ሉቃ ፩፥፳፮)፤ በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው በዚኽም በቤተልሔም ከድንግል መወለድ ምስጋና አለው (ሉቃ ፪፥፩-፯)፤ በዚያ ከሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት የዕጣኑን መዐዛ ይቀበላል (ራእ ፰፥፫-፬) በዚኽም ወርቅንና ከርቤን ዕጣንንም ከሰብአ ሰገል ተቀበለ (ማቴ ፪፥፲፩)፤ በዚያ ኪሩቤልና ሱራፌል ከግርማው የተነሣ ይንቀጠቀጣሉ በዚኽም ማርያም ዐቀፈችው ሰሎሜም አገለገለችው፤ በዚያ የመብረቅ ብልጭልጭታ በፊቱ ይገለባበጣሉ የእሳትም ወላፈን ከአዳራሹ ይወጣል (ሕዝ ፩፥፲፫) በዚኽም አህያና ላም በትንፋሻቸው አሟሟቁት (ኢሳ ፩፥፫)፤

በዚያ የእሳት ዙፋን አለ በዚኽም የደንጊያ በረት አለ፤ በዚያ የእብነ በረድ የሰማይ ንጣፍ አለ በዚኽም የላሞች መጠጊያ በረት አለ፤ በዚያ የትጉሃን ሥፍራ በሰማያት ያለች ኢየሩሳሌም አለችው በዚኽም የእንስሳት ጠባቂዎች ማደሪያ በኣት አለው (ሉቃ ፪፥፯)፤ በዚያ ርዝማኔ የማይታወቅ የዳንኤል ብሉየ መዋዕል አባት አለው (ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም የዓመቶቹ ቊጥር በሰው ልጅ ዐቅም መጠን የኾነ ሽማግሌ ዮሴፍ ተሸከመው …

የአምላክን ልጅ ሰው መኾኑን በዓል እናድርግ የተሸከመችውን ማሕፀን እናመስግን፤ ላቀፉት ጉልበቶች እንስገድ፤ ላሳደጉት ጡቶች እንዘምር፤ የዳሰሱትን እጆች እናመስግን፤ ለሳሙት ከንፈሮች እናሸብሽብ፤ ከእረኞች ጋር ምስጋናን እናቅርብ፤ ከሰብአ ሰገልም ጋር እጅ እንንሣ፤ እንደ ዮሴፍ እናድንቅ እንደ ሰሎሜም እናገልግል በተኛበት በረት እንስገድ፤ በተጠቀለለበት በረት እንበርከክ፤ ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና ይኹን በምድርም ሰውን ለወደደ እንበል (ሉቃ ፪፥፲፬)፤ እግዚአብሔር ሰው ኾነ የሰው ልጅ ሴት ልጅም የእግዚአብሔር እናት ኾነች፤ ለርሱ ምስጋና ይኹን ለርሷም ስግደት ይገባል ለዘላለሙ አሜን ይኹን) በማለት በጥልቀት ገልጾታል፡፡

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
አቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከልክ የባሕርይ አምላክ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ እውነተኛ ፈራጅ መኾንህን የምታስተምረውን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ጠብቅ አሜን

No comments:

Post a Comment