Thursday 20 September 2012

እናቁም?

አንዳንዴ የትግላችን፣የጥረታችን፣የልፋታችን ውጤት መና የቀረ የሚመስልበት ጊዜ አለ፡፡ ውኃ አልቋጥር፣ ጠብ አልል ሲልብን፤ መንገዱ ሁሉ ረዥም፣ በሮቹ ሁሉ ዝግ፣ ጩኸቱ ሁሉ ሰሚ አልባ ሲመስለን፣ በመጨረሻ የምንወሰደው መፍትሔ ነገር ዓለሙን ሁሉ መተውና መሸነፍ ይሆናል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ አበቃ›› ማለት እንጀምራለን፡፡ እንኳን እኛ ቀርቶ ሌሎች እንኳን እንዳይበረቱ ‹‹ባክህ እኛም ብለነው ብለነው አቅቶን ነው›› እያልን ተስፋ እናስቆርጣቸዋለን፡፡ግን ሰው መልፋት ያለበት፣ መትጋትስ ያለበት፣ መታገልስ ያለበት፣ መሮጥስ ያለበት እስከ የት ነው?ሰው ተስፋ መቁረጥ ያለበት የት ደረጃ ሲደርስ ነው? የመንገድ ማለቂያው የት ነው? ውጤቱን ዛሬ ያላየነው ነገር ሁሉ ውጤት አልባ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላልን? በታሰበው ጊዜ ያልተደረሰበት ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይችል ነገር ነው ማለት ነው? መንገዱስ ይሄ እኛ የያዝነው መንገድ ብቻ ነውን? በሌላ መንገድስ ሊሞከር አይቻልምን?መሆኑ ከማቆምና ከመቀጠል የትኛው ይመረጣል? ከማቆም ምን ይገኛል? ከተስፋ መቁረጥ በቀር፡፡ የሚጓዝ ሰው ጊዜው ይረዝም ይሆናል እንጂ አንድ ቀን የሚፈልገው ቦታ ይደርሳል፡፡ የቆመ ሰው ግን እንኳን ወደሚፈልግበት ለመሄድ  ወደ ተነሣበት ቦታም ተመልሶ አይደርስም፡፡ የሚታገል ሰው አንድ ቀን ያሸንፋል፤ ያቆመ ሰው ግን ሳይማረክ እጁን ሰጥቷል፡፡ ደጋግሞ የሚያንኳኳ ሰው ከተኙት ሰዎች አንዱን መቀስቀሱ አይቀርም፤ ማንኳኳት ያቆመው ግን እንኳን ሊቀሰቅስ ራሱም ይተኛል፡፡ የሚሄድ መኪና ጋራጅ ይደርሳል፤ የቆመ መኪና ግን ባለበት ይወላልቃል፡፡ ለማሸነፍ ትልቁ መፍትሔ አቋምን መቀየር ሳይሆን መንገድን መቀየር ነው፡፡ የተለያዩ ነገሮችን መሞካከር ሳይሆን አንድን ነገር በተለያዩ መንገዶች መሞከር ነው፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ማየት ሳይሆን አንድን ነገር በተለየ መንገድ ለማየት መቻል ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን፣ በውሳኔ ጊዜ መቁረጥ መቻል ነው፡፡ የምታገኘውን ሞት ከመመኘት የማታገኛትን ሕይወት በሚገባ ለመኖር ጣር፡፡ሁለት ዕንቁራሪቶች እየተጓዙ ነበር፡፡ አንዷ ወፍራም ሌላዋም ቀጭን ነበሩ፡፡ እንዳጋጣሚ በገረወይና የተሞላ ወተት አገኙና ሰፍ ብለው ገቡበት፡፡ እዚያም አስኪበቃቸው ጠጡና ሲጠግቡ መውጣት ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ውስጡ ያንዳልጥ ስለ ነበር ለመውጣት አልቻሉም፡፡ እግራቸውን ባንቀሳቀሱ ቁጥር ወተቱ እያንዳለጠ እዚያው ይጨምራቸዋል፡፡ ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ እጅግ ደከሙ፤ ነገር ግን ከድካም በቀር ያተረፉት ትርፍ አልነበረም፡፡በምን ቀን ነው እዚህ ወተት ውስጥ የገባነው? እያሉ ቀናቸውን የሚያማርሩበት ሰዓት ላይ ደረሱ፡፡