Monday 27 January 2014

የሆሳዕና ቡሻና በዐታ ለማርያም ገዳም ተቃጠለ

በእንዳለ ደምስስበሐድያና ስልጢ ሀገረ ስብከት ጎረጎራ ወረዳ ውቅሮ ፋለታ ቀበሌ የደብረ ምጥማቅ ሻና በዓታ ለማርያም ገዳም ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የከተራ ዕለት መነሻው ባልተወቀ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ቢኒያም መንቻሮ ገለጹ፡፡



ሥራ አስኪያጁ በሰጡን መረጃም የከተራ ዕለት የበዐታ ለማርያም ታቦት ወደ ጥምቀተ ባሕር ከወረደ በኋላ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ መቃጠሉን ገልጸው ቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅዱሳቱን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ብለዋል፡፡

በካዝና ውሰጥ የነበረው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽላት ካዝናው በእሳቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመለብለቡ ምክንያት መክፈት እንዳልተቻለና መቃጠልና አለመቃጠሉን እንዳልተረጋገጠ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ፤ ጉዳዩን ለፖሊስ በማሳወቅ የቃጠሎውን መንስኤ ለማጥራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የቡሻና በዐታ ለማርያም ገዳም ከዚህ በፊት ሥዕለ አድኅኖ በዛፎች ላይ ታይቶበት በነበረ ቦታ መቃኞ ተሰርቶለት ሐምሌ 2001 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ እንደተከበረ ይታወቃል፡፡

የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሻረው!


በርካታ ሚልዮን የምእመናን ገንዘብ የተመዘበረበት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታና ሒሳብ በብቁ እና ገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር ቅ/ሲኖዶሱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ልዩ ጽ/ቤቱ እንዲዘገይ አዘዘ – በውል ከተያዘው ገንዘብ ውጭ ከ8 ሚልዮን በላይ ብር የወጣበትና ሥራው ሳይጠናቀቅ በ6 ዓመት የዘገየው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ተሰነጣጥቋል፤ ዋናው መካከለኛ ጉልላት እንዳይወድቅ ያሰጋል

‹‹ብፁዕ አባታችን፣ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኃይል ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እየተፈጸመ የሚገኘው ከባድ ወንጀል ሕዝበ ክርስቲያኑን እያስቆጣ ከመምጣቱም ባሻገር ብፁዕ አባታችን ይህን እየሰሙና እያወቁ ምነው ዝም አሉ ብሎ ሕዝቡ እንዲያስብ አድርጎታል፡፡… የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ጅምር ሥራ አልቆ ማየት እንፈልጋለን፡፡ የደብሩ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በአስቸኳይ ሕዝቡ በሚመርጣቸው የኮሚቴ አባላት ይተካልን፡፡ ይህ የማይደረግ ከኾነና ኹኔታው ባለበት ከቀጠለ ለሚፈጠረው ችግር ሓላፊነቱን የማንወስድ መኾኑን እናሳውቃለን፡፡›› /የደብሩን ወቅታዊ ጉዳይ ለማሳወቅ ምእመናኑ በኅዳር ፳፻፬ ዓ.ም. ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ከጻፉት አቤቱታ የተወሰደ/