Friday 14 December 2012

ደም መስጠት እና የሰውነት አካልን መለገስ ይፈቀዳል?

በዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ
ከፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ

የሰው ልጅ በዚህች የመከራ ቦታ በሆነች ምድር እስካለ ድረስ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ ‹‹ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል ፤ ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም›› ኢሳ. 1.5
ከሚቻለን በቀር እንድንፈተን የማይፈቅደው እግዚአብሔር ‹‹ከፈተናው ጋር አብሮ መውጫውን ያደርግላችኋል፡፡›› ተብሎ እንደተነገረ የሰው ልጅ በተሰጠው ብሩሕ አእምሮ ተጠቅሞ በሚያድንበት የሕክምና ጥበብ እንዲራቀቅ አድርጓል፡፡ እኛ ክርስቲያኖችም ሐኪሙ የአርብ ዕለት ፣ የሚሰጠው መድኃኒት ደግሞ የማክሰኞ ዕለት ፍጥረታት መሆናቸውን በማሰብ የሰው ልጅ ስለደረሰበት የህክምና ጥበብ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ማዳን የእርሱ ነውና ፤ ሐኪሞቹ ሌላ ፣ ህክምናው ሌላ ቢሆንም ፈዋሹ እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን እናምናለን፡፡




መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በሚደንቅ ጥበቡ ዓለምን ስለመፍጠሩ የሚናገር ሲሆን በአዳም ላይ እንቅልፍ ጥሎ በኪነ ጥበቡ ከአዳም ጎን አንዲት ዐጽም በመውሰድ ሔዋንን ስለፈጠረበት መንገድም ያስረዳል፡፡ የሰው ልጅ ተራቅቆ ከደረሰበት የማደንዘዣም ሆነ የአካል ማዘዋወር ዘርፍ (Anesthesia & Transplantology) በስተጀርባ ይህን የመሳሰለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ እንዳለም መረዳት ይቻላል፡፡

የሰው ልጅ ልዩ ልዩ የአካል ክፍሎች ያሉት ሲሆን እጅግ ወሳኝ የሆኑና ያለእነርሱ ሊኖር የማይችልባቸው አካላት አሉት፡፡ እነዚህ አካላት በልዩ ልዩ ምክንያት በአግባቡ መሥራት ካልቻሉ ለሞት የሚዳርጉም ናቸው፡፡ እንዲሁም በሰውነት አካል የሚመላለሰው ደምም ከአካል በላይ እጅግ ወሳኝ ሲሆን በአደጋም ሆነ በበሽታ የሚከሰት የደም መፍሰስም ለብዙዎች ሞት ቀዳሚው ምክንያት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ለመፍታት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጥበብ ተመራምሮ በየጊዜው መፍትሔን እያበጀ መጥቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ደምን ቀድቶ ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ማስተላለፍ (Blood transfusion) የሰውነት አካልን ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ማዘዋወር (Organ transplantation) ዘመኑ የወለዳቸው እና የህክምናው ዘርፍ የደረሰባቸው መፍትሔዎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደምንም ሆነ የሰውነት አካልን ስለመለገስ በቀጥታ የሚናገርበት አንቀጽ የለም፡፡ ይህም የተጻፈበት ዘመን እነዚህን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች ሕግ የሚሠራበት ሁኔታ ስላልነበረ ነው፡፡

በዚህች አጭር ጽሑፍ ደምንም ሆነ የሰውነት አካልን ለሌላ ሰው መለገስ ፣ መሸጥ የመሳሰሉት ነገሮች ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንቃኛለን፡፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ በሀገራችን የህክምናው ዘርፍ ከነበረበት የዕድገት ደረጃ አንጻር ለኢትዮጵያውያን አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ያልተነሣና በቤተ ክርስቲያኒቱ በኦፊሴላዊ መግለጫ ይፋ የሆነ አቅዋም ባይኖርም ደም ልገሳ በሀገራችን ህክምና ከተስፋፋበት ዘመን ጀምሮ ሲፈጸም የኖረ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በዘርፉ በሚፈጠረው ዕድገት የተነሣ እንዲሁም ባሕር ማዶ ተሻግረው የሚታከሙ ኢትዮጵያውያን በመብዛታቸው ጉዳዩ የበለጠ ምላሽ የሚሻ ሆኗል፡፡ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሀገራት ሔደው የሰውነት አካሎቻቸውን በመሸጥ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚንከራተቱ ኢትዮጵያውያን የመኖራቸውም ጭምጭምታ ይህንን ጉዳይ ለመዳሰስ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ስለሚኖረን ኦርቶዶክሳዊ አቋም በአኃት ኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በመለካውያን ዘንድ ያለው አቋም ተመሳሳይነት ለዚህ ጽሑፍ እንደ ግብዓት የሚሆነን ሲሆን በኢትዮጵያ የደም ልገሳ ለዓመታት ሲካሔድ መቆየቱና በቤተ ክርስቲያኒቱም የተወገዘበትና ምእመናን ደም እንዳይለግሱ የተከለከሉበት ሁኔታ አለመኖሩ ፣ የደም ልገሳን በማስተባበርና በመሳሰለው የተራድኦ ሥራ ላይ የተሠማራው የቀይ መስቀል ማኅበርን ዓላማ ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ የምትደግፍ መሆኗና በማኅበሩ በሚዘጋጁ ልዩ ልዩ መድረኮች ላይ በመገኘት ቤተ ክርስቲያን ድጋፏን ማሳየቷም ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ባልንጀራ እንደ ራስ አድርጎ ስለመውደድ›› ‹‹ሌላው እንዲያደርግልን የምንፈልገውን ነገር ለሌላው ማድረግ›› የሚገባ ስለመሆኑ የሚያስረዱ ወርቃማ የፍቅር ሕግጋትን የያዘ ነው፡፡ ፍቅር ደግሞ መቀበልን ብቻ ሳይሆን መሥጠትን ፣ ለራስ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ማሰብን የሚያስከትል ነው፡፡ ‹‹ፍቅር ብቻዬን ይድላኝ አይልም›› እንዳለ ሐዋርያው፡፡ (1ቆሮ. 03.5) የፍቅር ደረጃው ከፍ ሲል ደግሞ ራስን ለሌላው አሳልፎ እስከመስጠት ያደርሳል፡፡ ‹‹እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት ፤ ነፍሱን ስለ ወዳጁ አሳልፎ ከመስጠት በቀር ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም›› የሚለው ኃይለ ቃልም ይህንኑ የሚያስረዳ ነው፡፡ (ዮሐ.05.03) እግዚአብሔር እርሱ ነፍሱን አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ እንደወደደን እኛም እርስ በእርሳችን በዚያው ልክ እንድንዋደድ አዝዞናል፡፡ ሐዋርያው በመልእክቱም ፍቅራችን እንዲህ ባሉ ተጨባጭ ሥራዎች መገለጥ እንዳለበት ሲያስረዳ ‹‹ልጆቼ ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ›› ብሏል፡፡ (1ዮሐ.3.08) ይሁንና ደምንም ሆነ አካልን መለገስ በፈቃደኝነት የምናደርገው የትሩፋት ሥራ ነው እንጂ ግዴታ አይደለም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ባልንጀራ ፍቅር ነፍሳችንን አሳልፈን እስክንሰጥ ድረስ እንድንዋደድ ካዘዘን ከሰውነታችን አንዱን የአካል ክፍል ፣ ወይም ደማችንን ለሌላው ሰው ብንለግስ እንዴት እንከለከላለን? ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ‹‹ፍቅር እስከ መሥዋዕትነት ከደረሰ ሕይወትን እስከመስጠት ያደርሳል፡፡ ሕይወቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ደግሞ ሌላውን ለመታደግ የሰውነት አካሉን ወይም ደሙን መስጠት ምንኛ ቀላል ይሆንለት ይሆን?›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በመሠረታዊ ሃሳቡ ለሌላው ማሰብንና የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ የራስን አካል መስጠትን ይደግፋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የገላቲያ ምእመናን ለእርሱ የነበራቸውን ፍቅር ሲገልጽ ‹‹እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ እንደ ክርስቶስ ተቀበላችሁኝ ፤ ቢቻላችሁስ ዓይናችሁን እንኳን አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደነበረ እኔ ምስክራችሁ ነኝ፡፡›› (ገላ.4.05) ብሏል፡፡ በእርግጥም ፍቅር አካልን እስከመስጠት የሚያደርስ ነው፡፡ ሐዋርያው ለገላትያ ሰዎች ይህን ቃል በተናገረበት በ49 ዓ.ም. ዓይንን አውጥቶ መስጠት የማይቻል ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ግን የጥበብ ምንጭ የሆነ እግዚአብሔር ክብር ይግባውና ይህ መሆን ችሏል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ደምን ወይም አካልን መለገስ በእግዚአብሔር ሥራ ጣልቃ መግባት ፣ ‹‹የእግዚአብሔር መቅደስ›› የሆነን ሰውነት ማፍረስ እንዳይሆንባቸው ይሰጋሉ፡፡ አንድ ሕመምተኛ ከሞት መዳንና አለመዳኑ የሚወሰነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንጂ በምንለግሰው ደም ወይም የሰውነት አካል ባለመሆኑ በእግዚአብሔር ሥራ መግባት ሊባል አይችልም፡፡ አምላካችን አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣ ድንጋዩን ማንከባለል የሰዎች ሥራ እንደነበረ ለሌሎች መዳን የበኩላችንን የማበርከት ዕድል ቢሰጠንም ማዳን ግን የእግዚአብሔር ነው፡፡ ደም እና አካልን መለገስ ጣልቃ ገብነት ከሆነ ደግሞ ምጽዋትም ጣልቃ ገብነት ሊሆን ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱም ያለንን መስጠት ሲሆን በሰውነታችንም ሆነ ከሰውነታችን ውጪ የእኛ የሆነ አንዳች ነገር የለንም፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔር መቅደስ የሆነ ሰውነታችንን እንደማፍረስ አድርጎ መረዳት የተሳሳተ ነው፡፡ የተቀደሰው ሰውነታችን የሚፈርሰው በደምና አካል ልገሳ ሳይሆን በኃጢአት ፣ በጎጂ ልማዶች ፣ ጤናን ባለመጠበቅና ራስን በመግደል እንጂ ሌላውን ለማዳን በሚደረግ መሥዋዕትነት አይደለም፡፡

ለቀናች ሃይማኖታቸው ሲሉ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡ በየቀኑ አንድ የሰውነት አካሉን እየቆራረጡ ያሰቃዩት እንደነበረው እንደ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ ያሉ ሰማዕታት ራስን የመስጠት አብነት ናቸው፡፡ በአንጻሩ ሀገርን ለመከላከል ፣ የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ ተብሎ የሚደረገውም መስዋትነት እጅግ የከበረና የሚመሰገን ነው፡፡ከሁሉ በላይ ግን ‹‹ሥጋዬንና ደሜን እንካችሁ ብሉ›› ብሎ ለነፍሳችን ድኅነት የሰጠንን መድኃኔዓለምን የምናምን ክርስቲያኖች የወገኖቻንን ሕይወት ለመታደግ ደምን ወይም አካልን መስጠት የሚከብደን አይሆንም፡፡

ሲሞቱ የሰውነት አካልን ተናዝዞ መሞትን ይፈቀዳል?

በርካታ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ዓይናቸውን ፣ ልባቸውን ወዘተርፈ ለሌላ ሰው እንዲሰጥ ተናዝዘው ይሞታሉ፡፡ እንዲሁም ሥጋቸውን ለህክምና ማስተማሪያነት ውሎ ሰዎችን እንዲረዳ የሚፈቅዱም አሉ፡፡ በአንዳንድ ያደጉ ሀገራት አንድ ሰው ከመሞቱ አስቀድሞ ስለ ሥጋው ምንም ዓይነት ውሳኔን ካላስተላለፈ በፈቃደኝነት እንደሰጠ ተቆጥሮ (Hypothetical donation) ለቀዶ ሕክምናና ለማስተማሪያነት ይውላል፡፡

ይህ ድርጊት ‹‹መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ›› በሚለው ቃል መሠረት ግብዓተ መሬት መፈጸሙን እስካላስቀረው ድረስ የሚደገፍ የርኅራኄ ተግባር ነው፡፡ ከሞትን በኋላ የማያይ ዓይናችንን ፣ የማይሠራ ልባችንን ለሌሎች ሕይወት ማዳኛ እንዳይውል መሰሰት ለትቢያና ለትል ማሰብ እንጂ ሊባል አይችልም፡፡ ‹‹ከሞት በኋላ ሥጋችንን ትሎች ይበሉታል ፣ ወደ ትቢያ ይቀየራል፡፡ ስለዚህ ይህችን ዓለም ትቶ የሔደን ሰው አካላት ለትሎች ምግብ ከሚሆኑና ወደ ትቢያ ከሚቀየሩ ከሌላ ሰው ጋር እንዲኖሩ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡›› ብለዋል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ፡፡

ምናልባት አንዳንድ ሰው ስሞት ዓይኔን ወይም ሌላ አካሌን ሰጥቼ በኋላ በትንሣኤ ጊዜ ዓይን ወይም ሌላ አካል የጎደለኝ ሆኜ ብነሣስ የሚል ስጋት ሊገባው ይችላል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ የተሳሳተ ግንዛቤም ‹‹ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት ሙሉ ሰውነትህ በከሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና ፤ ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና፡፡›› የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደ ማስረጃ መስሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ (ማቴ.5.!9) ይሁንና ይህ የተነገረው ቃል በቃል ስለ ዓይን ስለ እጅ ሳይሆን ዓይን ስለምትባል ስለ ሚስት ፣ እጅ ስለሚባሉ ስለ ልጆች የተነገረ ነው፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል) እንዲሁም በትንሣኤ ዘጉባኤ የሰው ልጅ በሚነሣበት ወቅት ይዞ የሚነሣው ይህንን የሚፈርስ የሚበሰብሰውን መሬታዊ አካል ሳይሆን ሌላ የማይፈርስ የማይበሰብስ መንፈሳዊ አካልን ነው፡፡ (1ቆሮ.05.#2-$) ደግሞም በእግዚአብሔር መንግሥት አጭር ረዥም ፣ ወፍራም ቀጭን ፣ ቀይ ጥቁር የሚባል ሥጋዊ መለኪያ ሁሉ የለም ፤ የተረፈውን ለመንግሥቱ ቢያበቃን የምናየው ነው፡፡

የሰውነት አካልን መሸጥ ይፈቀዳል?

መጽሐፍ ቅዱስ አካላችን የክርስቶስ አካል እንደሆነና የራሳችን እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ሥጋችሁ የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፡፡›› እንዳለ ሐዋርያው፡፡ (1ቆሮ. 03.!7፤6.9) ስለዚህ ሌላውን ለማዳን መለገስ የምንችለው ቢሆንም እንኳን እንደ ሸቀጥ የእኛ ያልሆነውን የሰውነት አካላችንን የመሸጥ ሥልጣን የለንም፡፡ ባለ ዕዳ የሚያደርገን እንጂ የሚያጸድቀን አይደለም፡፡ በሰውነት አካላችን ላይ ለሌላው የመስጠት እንጂ የመሸጥ መብት አልተሰጠንም፡፡ ምናልባትም ይህ ዓይነቱ መብት የሕግ ባለሙያዎች አላባ (Usufractury) ከሚሉት የማስተላለፍ ነገር ግን ያለመሸጥ መብት ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ (ፍት.ብሔ.አን.1160)

ደም መቀበል / መስጠት እና ደም መብላት

መጽሐፍ ቅዱስ በሕገ ኦሪት ከሚከለክላቸው ነገሮች አንዱ ደምን መብላት ወይም መጠጣት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከኖኅ ዘመን አንሥቶ ለሙሴ ሕግን እስከሰጠበት ዘመን ድረስ ደምን መብላት እንደማይገባ አዝዞአል፡፡ (ዘፍ.9.4 ዘሌ.7.!6 ፤ዘዳ.02.06) በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ባደረጉት የመጀመሪያው ሲኖዶስ ካወጡትና በአፈ ጉባኤው በቅዱስ ያዕቆብ ከተነበበው መግለጫ አንዱ ‹‹ከደም (ከመብላት) እንድትርቁ›› የሚል ነበር፡፡ (ሐዋ.05.!) ስለዚህ ደምን መብላት የተከለከለ ነው፡፡

‹‹የይሖዋ ምስክሮች›› በሚል ስም የሚታወቁት ወገኖች ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ በመጥቀስ ደም መለገስም ሆነ ደም መቀበልን ኃጢአት ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ደም መብላትና ደም መቀበል ፈጽሞ የማይገናኙ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ‹መጠበቂያ ግንብ› ብለው በሚጠሩት መጽሔታቸው በ1961 ዓ.ም. ኅትም ‹‹ደምን በማስተላለፍ ሕይወትን ማቆየት በምንም ዓይነት መልኩ ስኅተት ነው፡›› የሚል ድርቅ ያለ አቋም አስተላልፈው ነበር፡፡ (Blood, Medicine and the Law of God,1961,pp.13,14 ) በዚህም የተነሣ ብዙ የእምነቱ ተከታዮች ደም መስጠትንም ሆነ መቀበልን አይቀበሉም ነበር፡፡ በተለይም አንዳንድ ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸው ደም ወስደው እንዲታከሙ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ምክንያት ሕይወታቸው አልፎአል፡፡ ንቁ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ‹የይሖዋ ምስክሮች› መጽሔት በግንቦት 22, 1994 እ.ኤ.አ. ባወጣው ኅትሙ ወላጆቻቸው ደም እንዲወስዱ ስላልፈቀዱ ሕይወታቸው ያለፈ ሕፃናትን ፎቶ ‹‹አምላክን ያስቀደሙ ልጆች›› በሚል ርእስ በሽፋን ሥዕሉ ላይ አውጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና አምላክን ማስቀደም ማለት በሕፃናት ሕይወት ላይ መወሰን ሳይሆን ራስን መስጠት ነው፡፡

ይሁንና አብዛኛዎቹ የእምነቱ ተከታዮች ደም መለገስና ደም መቀበልን ብቻ ሳይሆን ደም መመገብንም በተግባር የሚደግፉ ነበሩ፡፡በምሥራቅ አውሮፓ በናዚ ጦር ታስረው ከነበሩ የእምነቱ ተከታዮች ውስጥ ከ275 መካከል 25 ብቻ ደም አንበላም ማለታቸውንና የቀሩት በሙሉ የተጠበሰ ደም ሲበሉ እንደነበር በወቅቱ የነበረች ማርጋሬት ቡቤር የተባለች ጸሐፊ መዝግባለች፡፡

በደም ልገሳ ላይ ያለቸው አቅዋም ተቀባይነቱ አጠያያቂ ሲሆን የእምነቱ ሐላፊዎች የአቋም ማስተካከያ አደረጉ፡፡ ስለዚህም ደምን ሙሉ በሙሉ መቀበል ባይፈቅዱም በታማሚው ምርጫ የደም ክፍልፋዮችን መጠቀም እንደሚቻል በ2000 እ.ኤ.አ. በሰኔ ወር ባወጡት መጽሔት ላይ ይፋ አደረጉ፡፡ በዚህም መሠረት ቀይ የደም ሴል ፣ ነጭ የደም ሴል ፣ ፕላዝማ እና ፕሌትሌት (Red cells, white cells, plasma, platelets) ተብለው የሚጠራውን ሙሉ ደም መቀበል ክልክል ሆኖ የአራቱን እንደ ሄሞግሎቢን ያሉ ክፍልፋዮች ግን መጠቀም ይቻላል ማለት ነው፡፡ ነገሩ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› እንደሚባለው ሆኖ እንጂ የሚያስኬድ ሆኖ አይደለም፡፡

አንደኛ አስቀድመው ደም ላለመስጠትና ላለመቀበል ያቀረቡት ምክንያት ደም አትብሉ መባሉን ከሆነ እግዚአብሔር ደም አትብሉ ሲል የደም ክፍልፋዮችን (Blood fractions) ግን ለይታችሁ መብላት ትችላላችሁ አላለም፡፡ እንዲሁም እናንተ ደም አትለግሱ ሌሎች ከለገሱት ደም ላይ የሚወሰዱ ክፍልፋዮች ግን ተጠቀሙ ማለት ዓይን ያወጣ ግለኝነት ነው፡፡ ‹‹እያንዳንዱ የባልጀራውን ጥቅም እንጂ አንድስ እንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ›› ተብሎ ተጽፏልና፡፡ (1ቆሮ. 0.!4)

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

2003 ተጻፈ

ምንጭ ፡- So Many years with the problem of people {Pop Shenouda iii}

1 comment: