Friday 2 November 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ መግለጫም በማውጣት ተጠናቀቀ


  • ምልአተ ጉባኤው የዕርቀ ሰላሙንአምስት የመነጋገሪያ ነጥቦች ለይቷል፤
  • ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ደቡብ እና ምዕራብ አዲስ አበባን፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ሰሜንና ምሥራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትን ይመራሉ፤
  • “የመነኰሳት መተዳደሪያ ደንብ” ይወጣል፤ የገዳማት ተወካዮች በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉና ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይደረጋል፤
  • ለአኵስም ጽዮን ማርያም አዲስ ንቡረእድ ይሾማል፤
  • ለካህናት ማሠልጠኛ፣ ለገዳማት፣ ለአብነት ት/ቤቶች (ብር 10 ሚልዮን+) እና ለሌሎችም የልማት ዕቅዶች ማስፈጸሚያ ከብር 128 ሚልዮን በላይ በጀት ተመድቧል፤
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 21/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶ. 31/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ላለፉት ዐሥር ቀናት በሥራ ላይ የቆየው የጥቅምት 2005 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ላይ መግለጫ ተጠናቀቀ፡፡ በ“ልዩ ልዩ ጉዳዮች” አጀንዳዎች ሥር በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰውና የበጀት ምደባን ጨምሮ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቀደም ሲል ውሳኔ ያሳለፈባቸውን የመነጋገሪያ ነጥቦች ዳግመኛ በጥልቀት ሲመለከት የቆየው ምልአተ ጉባኤው÷ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ ለሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት የቅዱስ ሲኖዶሱ ልኡክ መነጋገሪያ (መደራደሪያ?) የሚያደርጋቸውን አምስት ነጥቦች መለየቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱን አቋም የሚገልጡ ናቸው የተባሉት አምስቱ ነጥቦች “የሰላምና አንድነት ጉባኤው” ላቀረባቸው ሰባት ጥያቄዎች በተሰጡ መልሶች ላይ በመመሥረት የተዘጋጁ መኾናቸውን የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ዜና ሕይወቱ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ


ከደቂቀ ናቡቴ ድረ-ገጽ ላይ የተወሰደ

ልደቱ 

የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ደራሲ፣ መናኝ፣ ጻድቅ፣ ሊቅ፣ የሕዝብ መምህር እና የሥነ ምሕንድስና ባለሙያ የሆነው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የተወለደው በ1357 ዓመተ ምሕረት በወሎ ክፍለ ሀገር በዛሬው ቦረና በጥንቱ ወለቃ ወረዳ ሸግላ በተባለ ቦታ ነው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ስለ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ሁለት የተለያዩ ታሪኮች ይተረካሉ፡፡ የሰኔ ድርሳነ ዑራኤል ምንባብ አባቱ በመጀመሪያ የትግራይ በማስከተል የሰግላ /ጋሥጫ/ አገር ገዢ እንደነበር ይወሳል፡፡ ገድሉ ደግሞ /ጠቢብ ወማእምረ መጻሕፍት ወአቡሁኒ መፍቀሬ እግዚአብሔር አምኁልቈ ካህናተ ደብተራ ዘውሳጤ ዓጸደ ቤተ ንጉሥ/ አባቱም የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳን /ሥዕል ቤት/ ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበረ ይላል፡፡ እንደ ገድሉ ገጸ ምንባብ ትርጉም ሕዝበ ጽዮን ከንጉሡ ሥዕል ቤት በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ከሚያገለግሉ ካህናት አንዱ ነው፡፡ /. . . ወእሙኒ እም ሥዩማነ ወለቃ/ እናቱም ከወለቃ ሹማምንት ወገን ነች ይላታል፡፡ ይኸውም የጥንቱ ወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና ከላላ/ ከነበሩ መኳንንት ወገን መሆኗን ያመለክታል፡፡      የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ልጅ ሳይወልዱ ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የልጅ ፍላጎታቸው እንዲሠምር ለሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳሉ፡፡ ስእለታቸውም ሥምሮ በመልአኩ ቀዱስ ዑራኤል አብሣሪነት ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ልጃቸውን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመማጸን ስለወለዱ ስሙን ጊዮርጊስ ብለው ጠሩት፡፡ ወላጆቹ የታላቁን ሰማዕት ስም ለልጃቸው ያወጡት ወደ ፊት በዓላውያን ነገሥታት ፊት ምስክር፣ አፅራረ አምነትን አሳፋሪ፣ ካህናትንና ምእመናት በየዘመናቱ ከሚነፍሱ የኑፋቄና የክህደት ነፋሳት በወንጌል ብርሃን ነፃ የሚያወጣ ሲሉ ይህን ስም እንዳወጡለት ድርሳነ ዑራኤል እንዲህ ይተርካል፡፡ ‹‹ዘይከውን መምህረ ኵሉ ዓለም ወበጸሎቱ ዘያድኅን አሞተ ሲኦል ፍቁረ ድንግል ማርያም ወላዲቱ ለአማኑኤል፡፡ ወመገሥጾሙ ለነገሥት፡፡ ወፀሮሙ ለዐላውያን ሃይማኖት በሰይፈ ቃሎሙ ለሐዋርያት ዘያጠፍኦሙ እም ብሔረ ኢትዮጵያ፤ ወለካህናተ ጽድቅ ዘይመርሆሙ እምጽልመተ ኑፋቄ መንገለ ብርሃን ቃለ ወንጌሉ ለክርስቶስ በትምህርተ ሕጎሙ ለሐዋርያት›› ይላል፡፡
ትምህርት :-አባ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርቱን ከወላጅ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እንደተማረ ይገመታል፡፡ አባቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተምህርቱን ካስተማሩት በኋላ መዐርገ ዲቁና እንዲቀበል ማድረጋቸውን  ገድሉ ይነግረናል፡፡ ወሶበ ልህቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆነ፡፡ ባደገም ጊዜ ከጳጳስ ዘንድ ወሰደው ጳጳሱም በዲቁና አሾመው ይላል ገድሉ፡፡ ዲቁና መቀበሉን እንዲ መዓርገ ዲቁና የሰጡትን ጳጳስ ስም አይገልጽም፡፡ ዳሩ ግን መዓርገ ዲቁናን በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ አካባቢ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ መተርጉም እንደተቀበለ ይገመታል፡፡