የተዋህዶ አባቶች

ሐዋርያው ታዴዎስ

ሐዋርያው ታዴዎስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ነው። ዓለምን ዞራችሁ ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ስበኩ በተባሉት መሰረት ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ሲከፋፈሉ ለዚህ ሐዋርያ ሶርያ ደረሰችው። ዛሬ የእርስ በእርስ እልቂት ያለባት አገርማለት ነው። ይህ ሐዋርያ እጅግ ድንቅ ታአምራት በሶርያ ምድር አድርጓል፤ ነገሩ እንዲህ ነው፤ አንድ ትዕቢተኛ ሰይጣን ያደረበት ባለጸጋ ቀርቦት "መምህር ሆይ በመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ሀብታም መንግስተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ይላል። እስኪ መጽሐፍ ቅዱሳችሁ እውነት ከሆነ አድርገህ አሳየን?" ይለዋል። 

ሐዋርያው ታዲዎስም መርፌ የሚሰራ ባልንጀራ ነበረውና መርፌ እንዲልክለት ሰው ይሰዳል። ያ መርፌ ሰሪም ሐዋርያውን ለመርዳት አስቦ ቀዳዳውን ትንሽ አስፍቶ ይልክለታ። ታዴዎስም ፈገግ አለ! የመርፌ ቀዳዳ ምን ቢሰፋ እንዴት ግመል ያሳልፋል ስለውለታህ አመሰግናለው ትክክለኛውን መርፌ ላክልኝ ብሎ ይመልስለታል። እርሱ ድጋሚ አስተካክሎ ይልክለታል፤ ከዚህ በኋላ አገሬው በአደባባይ ተሰበሰበ ጭነት የያዘች ግመልና አንድ ነጋዴም ተዘጋጁ ሐዋርያው ዓይኑን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ "አምላኬ ሆይ ይህን የማደርገው ክብርህ እንዲገለጽ እንጂ ክብሬ እንዲገለጽ ብዬ አይደለም ጸሎቴን ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ!" አለ። 

ጸሎቱን እንደጨረሰ ጭነት የተሸከመችውን ግመል እንድታልፍ አደረጋት። ሰው ሁሉ እያየ በመርፌው ቀዳዳ ሾለከች። አገሬው እልልታውን አቀለጠው! ለሁለተኛ ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜም እንድትሾልክ አደረገ። ህዝቡ ይህን የእግዚአብሔር ድንቅ ተአምራት አይቶ ብዙዎች አመኑ ተጠመቁም። ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ እንደዚህ ያለ ተአምራት ያየ ማን አለ? እኛ ግን ከሶርያ ህዝብ ጋር አየን ተመለከትን። በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እንዳለ " በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል ከእኔም በላይ ያደርጋል" 

ግሩም ነው የፈጣሪ ስራ። ሐዋርያው ቅዱስ ታዲዎስ በብዙ አገር ተዘዋውሮ ሲያስተምር ጣኦት አምላኪዎች ይዘው አሰቃዩት በሐምሌ 2 ቀንም ገድለውታል። እርሱም የሰማዕትነት አክሊል ተቀብሏል። 

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሐዋርያው በረከት ያሳትፈን። 

ስንክሳር፤ ገድለ ሐዋርያት።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


አባ ፓምቦ

ቅድስት ሜላኒያ ስለ አባ ፓምቦ እንዲህ አለችው "ገና መጀመሪያ ጌዜ ከሮም ወደ እስክንድርያ ስመጣ የእርሱን ቅድስና ሰምቼ እንዲሁም አባ ኤስድሮስ ስለ እርሱ ነገረኝና ከዚያም እርሱ ወዳለበት ወደ በረሃው ወሰደኝ። እኔም በሳጥን ውስጥ የታሸገ ሦስት መቶ (300) ወቄት ወርቅ ወሰድኩና የሚፈልገውን ያክል እንዲወስድ ለመንኩት። እርሱ ግን ከተቀመጠበት ሳይንቀሳቀስ ሰሌን እየታታ ባረከኝና "እግዚአብሄር ዋጋሽን ይሰጥሽ ዘንድ ፈቃዱ ይሁን" አለኝ። ከዚያም ረድኡን "ይህን ውሰደውና በሊቢያና በደሴቶች ለሚኖሩት ወንድሞች ለሁሉም አከፋፍላቸው፣ እነዚህ ገዳማት ከሌሎቹ ይልቅ ድሃዎች ናቸውና" አለው። በግብጽ ላሉት ግን  የእነርሱ መሬት የተሻለ ለምነት ስላለው ምንም እንዳይሰጥ አዘዘው።

እኔ ግን ስለ ስጦታዬ የበለጠ እንዲያከብረኝና እንዲያመሰግነኝ ተስፋ በማድረግ እዚያው ቆምኩ። ሆኖም ምንም ሲለኝ ስላልሰማው፣ አባ ውስጡ ምን ያህል እንዳለ ታውቅ ዘንድ 300 ወቄት ነው አልኩት። እርሱ ግን እራሱን እንኳ ቀና ሳያደርግ "ያመጣሽለት እርሱ፣ ልጄ ሆይ፣ መጠኑን የሚነግረው አያስፈልገውም። ተራሮችን የሚመዝን እርሱ የዚህን ወርቅ ክብደት የበለጠ ያውቀዋል። የሰጠሺው ለእኔ ቢሆን ኖሮ በእርግጥ መንገርሽ አግባብ ነበረ። የሰጠሽው ለእግዚአብሄር ከሆነ ግን የመበለቲቷን ሁለቱን ሳንቲሞች ያልናቀ እርሱ ያውቀዋልና መንገር አያስፈልግሽም" አለኝ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምንም ሳይታመም ቅርጫት እየሰራ እያለ በሰባ ዓመቱ ዐረፈ። ሊያርፍ ሲል እየሰራ የነበረውንና ሊያልቅ ትንሽ የቀረውን ቅርጫት ላከልኝ፣ እንዲህ በማለት፣ "ታስቢኝ ዘንድ በእጆቼ የተሰራውን ቅርጫት ተቀበዪ፣ ታስቢኝ ዘንድ የምተውልሽ ሌላ ምንም ነገር የለኝምና።" ስጋውን ለመቃብር ካዘጋጀው በኋላ ቀበርኩትና ከበረሃው ተመለስኩ። ያቺን ቅርጫትም እስከ ህይወቴ ፍጻሜ ድረስ በክብር አኖርኋት።

ይህ አባ ፓምቦ ሊሞት ሲል እንዲህ አለ ፦ "ወደዚህ በረሃ ከመጣሁበትና በአቴን ሠርቼ በዚህ መኖር ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በእጄ ያልሰራሁትንና ያልደከምኩበትን ነገር አልተመገብኩም፣ የምጸጸትበት ቃል አልተናገርኩም። ሆኖም ሃይማኖተኛ መሆን ገና ምንም እንዳልጀመረ ሰው ሆኜ ነው ወደ እግዚአብሄር የምሄደው።"

የአባታችን የአባ ፓምቦ ምልጃውና በረከቱ አይለየን። አሜን።

(ከበረሓውያን ሕይወትና አንደበት በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ)
ጥር 2003 ዓ.ም


==================///////////////================


ነገረ ማርያም በነገረ ድኅነት


ቤተ ክርስቲያናችን ለምን ስለ እመቤታችን ዘወትር እንደምታስተምር አንዳንድ ሰዎች ግር ሲላቸው ይታያል፡፡ እንዲያውም ‹‹አላዋቂ ሳሚ...›› እንዲሉ ስለ እመቤታችን ማስተማå ስለ ጌታችን እንዳታስተምር አድርጓታል ብለው የሚናገሩም አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ግን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምታስተምረው ለርሷ ካላት ልዩ ፍቅር ብቻ ወይም ስለጌታችን የምታስተምረው ለርሷ ካላት ልዩ ፍቅር ብቻ ወይም ስለጌታችን የምታስተምረው አልቆባት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ሊቃውንት በላይ ለነገረ መለኰት ምሁርና ጥንቁቅ ከማግኘት የሰማይን ስፋት ልክ ማግኘቱ ሳይቀል አይቀርም፡፡

በቅዳሴያችን፣ በዘወትር ጸሎታችን፣ በመዝሙራችን፣ በሥርዓታችን፣ በትውፊታችን፣ በአለባበሳችን ሳይቀር የነገረ ድኀነት ትምህርት የሌለበት የለም፡፡ ሰዎች ዐረፍተ ዘመናቸው ደርሶ ወደ መቃብር ሲሸኙ በምናደርግው ጸሎተ ፍትሐት ለክርስቲያኑ በሚደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሁሉ ነገረ ድኀነት ይሰበካል ይገለጣል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ነገረ ማርያምን ዘወትር ለምእመናን የምታስተምረው ከነገረ ድኀነት ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምሥጢር ስላለው ነው፡፡ ነገረ ድኀነትን ለመማር፣ ለመረዳትና ለማመን ነገረ ማርያም መሠረትና መቅድም ነው፡፡ ያለ ነገረ ማርያም ነገረ ድኀነት፣ ያለመሠረት ቤት ማለት ነው፡፡ እስቲ ለዚህ ምስክር የሚሆኑ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡

1. የሔዋን ካሣ
ሀ. እናታችን ሔዋን ምክንያተ ስህተት፣ ምክንያተ ሞት በመሆኗ ፍዳ መርገም ደርሶባት ነበር፡፡ ያበላችን ፍሬ ሞትን የሚያመጣ ከገነት የሚያስወጣ በመሆኑ ትውልድ ሁሉ ሲወቅሳት ይኖር ነበር፡፡

ዳግማዊት ሔዋን እመቤታችን ግን ምክንያተ ድኂን ሆነች፡፡ የሰጠችን ፍሬ ሞትን የሚያመጣ ሳይሆን ተበልቶ ተጠጥቶ የዘላለም ሕይወት የሚያሰጥ ነው /ዮሐ6&36/:: ትውልድ ሁሉ ሔዋንን ሲወቅስ ኖረ፡፡ እመቤታችንን ግን ትውልድ ሁሉ ያመሰግናታል /ሉቃ 1&48/:: ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴው ‹‹ስለ… ሔዋን የገነት በር ተዘጋ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን፡፡ ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን›› ብሏል፡፡

ለ. ሔዋን በዲያቢሎስ ተመክራ ኃጢአትን ጸነሰች፡፡ ሞትንም ወለደች፡፡ እመቤታችን ግን በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ሕይወትን ፀነሰች ትንሣኤን ወለደች /ሉቃ 1&28-38/፡፡
በሴት የመጣ ሞት በሴት ድል ተመታ፡፡ ‹‹እመቤታችንን የሔዋን መድኃኒቷ›› ያሰኛትም ይኼው ነው፡፡ ይኼንን ድንቅ ምሥጢር ካልተረዳንና ካላመንን ሔዋን መካሥዋን፣ የሴቶች ክብራቸው መመለሱን በምን ተረድተን እንዴትስ ልናምን እንችላለን?

2. የአዳም ካሣ
ሀ. አዳም የተወለደው ከኀቱም ምድር ነው፡፡ ከአዳም በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ ልጅ የላትም፡፡ አዳምን ያስገኘችው በጥበበ መንፈስ ቅዱስ በፈቃደ ሥላሴ እንጂ ዘር አላስፈለጋትም፡፡ ያ በዚህ ግሩም ድንቅ ምሥጢር የተገኘ አዳም ግን ሞትን በራሱ ላይ በማምጣቱ ወደቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትም አንዱና ዋነኛው ምክንያት ለቤዛ ዓለም፣ ለካሣ ዓለም ነው፡፡ ይኸንንም በመዋዕለ ይጋዌው በሠራው ሥራ ሁሉ ገልጦታል፡፡

ጌታችን ሲወለድ ያለወንድ ዘር፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በኀቱም ድንግልና ከእመቤታችን ነው፡፡ የእመቤታችንን ድንግልና ካልተቀበልን የመጀመሪያው አዳም ከኋለኛው አዳም ይበልጣል ማለት ነው፡፡ ያነሰው ደግሞ የበለጠውን ሊያድን እንዴት ይቻለዋል? እኛስ እንዲህ አናምንም፡፡ ከኀትምት ምድር ተወልዶ የወደቀውን አዳም ያነሣው ዘንድ ያለወንድ ዘር ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ምድር ከአዳም በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ ልጅ እንዳላስገኘች እመቤታችንም ከጌታችን በፊትም ሆነ በኋላ በድንግልና ኖረች፡፡ በዚህም ዘላለማዊት ድንግል ትባላለች፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ይኼንን በምሳሌ ሲያስረዳን፡-
‹‹እውነት ከምድር በቀለች
ጸድቅና ሰላም ተስማሙ›› ብሏል (መዝ 84&1ዐ-11)፡፡ እውነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ዮሐ14&7/፡፡ እውነት የበቀለባት ምድር ደግሞ እመቤታችን ናት፡፡ ጽድቅና ሰላም የተስማሙትም በልደተ ክርስቶስ ነው፡፡

ለ. አዳም የተገኘው መርገም ካልደረሰባት ምድር ነው፡፡ ምድር መርገምን ያመጣችው በልጅዋ በአዳም በደል ነው፡፡ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምም በደል መርገም ያልደረሰባት ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡ አስቀድማ በደል /ጥንተ አብሶ/ ነበረባት ካልን ከኋለኛው ምድር የቀደመችው ትበልጣለች ያሰኝብናል፡፡ ይኸ ከሆነ ደግሞ አዳም አዳም ተዋጀ፣ ተካሠ ወደ ክብሩ ተመለሰ ማለት አይቻልም፡፡ ያነሰው የበለጠውን ሊያከብረው አይችልምና፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን እመቤታችን የአዳም ኃጢአት ያልደረሰባት ናት ብላ የምታስተምረው ርቱዕ እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፣ እምነቷ እንደ ሌሎቹ አይጣላምና፡፡ የሌሎቹ ግን የሚናገሩትም ሆነ የሚጽፉት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፡፡

አንዳንዶች እመቤታችን ‹‹ከአዳም ኃጢአት የነጻችው በብሥራተ ገብርኤል ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ ከሆነማ የክርስቶስ መሞት ለከንቱ ሆነ ያሰኝባቸዋል፡፡ ብሥራተ መልአክ ከቀደመ ኃጢአት /ከጥንተ አብሶ / ነጻ የሚያወጣ ቢሆን ኖሮ በብሉይ እነ ብእሲተ ማኑሄ /መሳ 1&131-20/ በሐዲስ ደግሞ እነ ዘካርያስ /ሉቃ 1&13-20/ ከዚህ ቀንበር ነፃ በወጡ ነበር፡፡ በብሥራተ መልአክ ልጅ አግኝተዋልና፡፡ በሌላ በኩልም የመልአክ ብሥራት ከጥንተ አብሶ ለመላቀቅ ካስቻለ እልፍ አእላፍ መላእክት ተልከው አዳምን ከነዘሮቹ ባዳኑት ነበር፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከጥንተ አብሶ ካላቀቀ ከክርስቶስ ሞት ጋር እኩል ነው ማለት ነው /ሎቱ ስብሐት/፡፡ እኛስ እንዲህ አንልም ይህ ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው የሃይማኖት ስሕተትን ያስከትላል፡፡

3. የሕያዋን እናት
አዳም ለሚስቱ የሕያዋን እናት ብሎ ስም አውጥቶ ነበር፡፡ ሔዋን ማለት የሕያዋን እናት ማለት ነውና /ዘፍ 3&2ዐ/፡፡ ነገር ግን የሕያዋን እናት በርግጥ አልነበረችም፡፡ እርስዋም ልጆችዋም የሞት ባሮች ነበሩና፡፡ ‹‹ከአዳም እስከ ሙሴ ሞት ነገሠ›› እንዲል (ሮሜ 5&19)፡፡ ታዲያ የሕያዋን እናት ማንናት?

የሰው ልጅ በጥፋቱ እናትም አባትም አጥቷል፡፡ አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ከገነት ተባረሩ፡፡ ለኛ ቤዛ መከታ፣ አለኝታ ሊሆኑን ቀርቶ ለነርሱም አስፈልጓቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ተገብቶ በሥጋ ብዕሲ መጣ፡፡ ወንዶቹ #እኛ ብቻ ተካስን የሔዋን ነገር ግን መና ቀረ$ እንዳይሉ እመቤታችንን መርጦና ቀድሶ አዘጋጀ፡፡ አባትም እናትም ያጣው የሰው ዘር አባት አገኘ፡፡ ‹‹አባ አባት ብለን የምንጠራበት የልጅነት ጸጋ ተሰጠን›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባታችን ሆይ›› በሉ የተባልነውም ይኸ ክብር ስለተመለሰልን ነው (ሮሜ 8&15)፡፡ ስለሔዋን ደግሞ የሕያዋን እናት ትሆነን ዘንድ እመቤታችንን አገኘን፡፡ የሰው ልጅ ገነትንም እናቱንም ያጣው ባንድ ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ገነትንም እናቱንም ያገኘው ደግሞ በአንድ ጊዜ ነው፡፡ እመቤታችን በጸሎታችን ብዛት፣ በቅድስናችን ብቃት ያገኘናት ሳትሆን ስለምታስፈልገን የተሰጠችን እናት ናት፡፡ ይህም ጌታችን በመልዕልተ መስቀል የሚወደውን ደቀመዝሙሩን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹እነኋት እናትህ›› ባለው ጊዜ ታውቋል /ዮሐ 19&19/፡፡ ነቢዩ ዳዊትም አስቀድሞ ‹‹ሰው እናታችን ጽዮን ይላል›› ሲል ተናግሮላት ነበር (መዝ 86&5)፡፡

አማናዊቷ ሔዋንም /እመሕያዋን/ እመቤታችን ናት፡፡ ልጇ ሞትን አሸንፎ እኛ ልጆቿ የምናሸንፍበትን ሥልጣን እንደሰጠን እርሷም ሞትን አሸንፋዋለችና እንዲህ እናምናለን እንዲህም እንመሰክራለን፡፡ ያለበለዚያ ግን የሰው ልጅ ወደ ጥንተ ክብሩ ተመለሰ ፍጹም ድኀነትን አገኘ ለማለት አንችልም፡፡

እንግዲህ በነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ነገረ ማርይም ለነገረ ድኀነት ምን ያህል መሠረት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ነገረ ማርያምን በሚገባ ያልተረዳና ያልጠነቀቀ ነገረ ድኀነትንም ሆነ ነገረ መለኰትን ጠንቅቆ መረዳት አይቻለውም፡፡ አንድ ድንጋይ ከመሠረቱ ላይ በተነሣለት ቁጥር ቤቱም የዚያን ያህል እንደሚናጋ በነገረ ማርያም አንዳች ስህተት ብንጨምር የነገረ መለኰት ትምህርታችንም ሆነ እምነታችን የዚያኑ ያህል የተሳሳተ ይሆናል፡፡ ያለ ንጽሕት ሃይማኖት ደግሞ ንጽሕና አይገኝም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ማርያምን አዘውትራ የምታስተምረው ያለ ጥርጥርና ያለነቀፋም የምታምነው ለድኅነት መሠረት መሆኑን በተረዳ ነገር ስላወቀች ነው፡፡ በሥዕሎቻችን፣ በጸሎታችን፣ በመጻሕፍቶቻችን፣ በዝማሬዎቻችን፣ በሥርዓታችንና በትውፊታችንም ስለእመቤታችን የሚነሣው ለዚህ ነው፡፡ የቀረውን ደግሞ ሥላሴ ይግለጥልን፡፡ አሜን

--------------------//---------------

አባ መቃርዮስ


በአንድ ወቅት አባ መቃርዮስ ይህንን ታሪክ ተናግሮ ነበር። ወጣት ሆኘ በአንዲት በዓትውስጥ ስኖር መንደሩ ጸሐፊ ሊያደርጉኝ ፍለጉ። ይህንን ክብር መቀበል ስላልፈለኩ ሸሽቼ ወደ ሌላ መንደር ገባሁ። ሸሽቼ ስሔድም አንድ ሰው አብሮኝ ነበረ።  ም ሰው እኔ በእጄ የምሰራውን እየሸጠልኝ ያገለግለኝ ነበር። በዚህ መሐል በዚያ መንደር የምትኖር አንዲት ድንግል የነበረች ሴት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ አርግዛ ተገኘች። ማርገዟም በታወቀ ጊዜ ከማን እንደጸነሰች ቤተሰቦቿ አጥብቀው ጠየቋት። እሷም የደፈረኝ እና የጸነስኩትም ከዛ መናኝ ሰው ጋር ነው ብላ ነገረቻቸው። ቢዚህን ጊዜ መንደርተኞቹም ሲሰሙ በፍጥነት መጥተው ያዙኝ። በጣም ጥቁር የመሰለ ማሰሮ እና ሌሎችንም የወዳደቁ ነገሮች በአንገቴ ዙሪያ አጠለቁብኝ ከዛም ወደ መንደሮችና አደባባዮች እያዳፉ ወሰዱኝ። በጣምም አብዝተው ይደበድቡኛል። ደግሞም « ይህ መነኩሴ ልጃችንን አበላሸ፤ ያዙት፤ በሉት እያሉ ይቀጠቅጡኛል» ብዙም ክፉ ቃላትን ይናገሩ ነበር። እስከ ሞት ድረስ ደበደቡኝ። ከሽማግሌዎች አንዱ ወደ እኔ ቀረበና « ምን እያደረጋችሁ ነው? ምንስ መስራታችሁ ነው? ይህን እንግዳ መነኩሴ መከራውን የምታሳዩት? ደግሞስ እስከሞት ድረስ እንደዚህ የምትደበድቡት» ምክኒያታችሁስ ምንድን ነው? ብሎ ጠየቃቸው። ያ እኔን ያገለግለኝ የነበረ ሰው በሃፍረት ስሜት ውስጥ ሆኖ በኋላዬ ይከተለኝ ነበር። እሱም እኔን እንደሚያገለግለኝ ያውቁ የነበሩ ሰዎች እርሱን ይሰድቡት ነበር። « ተመልከት ይህንን አብዝተህ ታምነውና ታገለግለው የነበረው መነኩሴ እንደዚህ አሳፋሪ፤ ዘግናኝ እና አስነዋሪ ስራ በንጹህ ልጃችን ላይ ያደረገውን ስራ። አያሳፍርም? ምን እንደሰራ አየህ? ይሉትነበር። የልጅቱም ወላጆች « ልጃችንን ለመንከባከብ ቃል እስኪገባ ድረስ እንዳትለቁት» ብለው ትዕዛዝ አስተላለፉ። እኔም ያንን ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ እንደምፈጽምላቸው ቃል ከገባሁላቸው በኋላ ወደ ቤቴ እንድሄድ ፈቀዱልኝ። እኔም ከዛ መከራ፤ ስቃይና እንግልት እንደተላቀኩ ባየሁ ጊዜ አምላኬን አመስግኜ ወደ በኣቴ ተመለስኩ። ከዚያም የሚያገለግለኝን ሰው « ያለኝን ቅርጫቶች ሽጥና ለዚያች ሴት ስጥልኝ» አልኩት እርሱም እንዳልኩት አደረገ። ለራሴም መቃርዮስ ሆይ ለራስህ ሚስት አግኝተሃል፤ እርሷን መንከባከብ ትችል ዘንድ ካለፈው የተሻለ ስራ መስራት አለብህ ብየ ለራሴ ነገርኩት። ከዚያም ሌትና ቀን መስራት ጀመርኩ። ያፈራሁትንም ገንዘብ ለልጅቷ እየላኩ መርዳት ጀመርኩ። ለብዙ ጊዜ እንደዚህ እያደረኩ መውለጃዋ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እረዳት ነበር።የመውለጃዋ ቀን በደረሰ ጊዜ ምጡ በዛባት ለብዙ ቀናት ብታምጥም መውለድ ግን አልቻለችም ነበር። «መንደርተኞችም ተሰባሰቡ፤ ተጨነቁ ደግሞም እርስ በእርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር ምንድን ነው ችግሩ እያሉ። የልጅቷ ምጥም እየበዛ፤ እየተሰቃየች በመጣች ጊዜ ምንድን ነው ችግሩ? ብለው እሷን ጠየቋት። እሷም « ምክኒያቱን አውቄዋለሁ፤ ያንን መናኝ ባልፈጸመው ድርጊት ስለወነጀልኩት ነው። የጸነስኩት ከሱ አልነበረም፤ የጸነስኩት ከእገሌ ነው ብላ እውነቱን ከእንባ ጋር ነገረቻቸው። በዚህን ጊዜ ያ ያገለግለኝ የነበረው ሰው በጣም ከመደሰቱ የተነሳ እይሮጠ ወደ እኔ ፈጥኖ መጣና የምስራች ብሎ ሁሉን ነገር ገልጦ ነገረኝ። ያች ሴት የጸነስኩት ከመነኩሴው አይደለም እስክትልና እውነቱን እስክትናገር ድረስ መውለድ አልቻለችም ስለዚህ ያ እንደዚያ ሲያሰቃዩህ የነበሩት መንደርተኞች በሙሉ መጥተው ይቅርታ ሊጠይቁህ በዝግጅት ላይ ናቸው አለኝ። ነገር ግን ይህንን ስሰማ ሕዝቡ ስለ እኔ መልካም በማውራት ነብሴን በውዳሴ ያዝሏታል ብየ በመፍራት ሸሸሁ ወደ ሌላ ገዳምም ሄድኩ።  ስለዚህ እኛ ከዚህምን እንማራለን? ሰውን በሃሰት ከመክሰስ፤ ከመውንጀል መታቀብ ይኖርብናል። ለዚህም እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን።  

የአባታችን የመቃርዮስ በረከታቸው እና ረድኤታቸውአይለየን አሜን።

ቅዱሳን

 "እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እርሱንም እሻለሁ በህይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን አይ ዘንድ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።መዝ 26:4
የቅድስና መሰረቱ ራስን መቆጣጠር መቻል፣የሚሰሩትንም ሆነ የሚናገሩትን ማስተዋልና ጠንቅቆ ማወቅ፣ ጎጂ ከሆኑ ልማዶች ራስን መቆጠብ፣ የሌሎችን ጉድለትና ስህተት ከማጉላት ይልቅ ፍቅረ እግዚአብሔርን እያሰቡ ከመልካም ምግባራቸው መማር መቻል፣ እኔ ከሁሉ ያነስኩ ነኝ ብሎ ማመንና ከምንም በላይ ደግሞ ከቤተ መቅደሱ አለመራቅ...ወዘተ ነው።
ቅዱሳን አባቶች ፍቅራቸው ራስን አሳልፎ እስከመስጠት ነውና እውነተኛና ከቅን ልቡና የመነጨ ፍቅር መሆኑ አያጠያይቅም። ስለ ሃይማኖታቸው አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ጀርባቸውን ለግርፋት፣ ፊታቸውን ለጽፋት  ነፍሳቸውን ለሞት የሰጡና "ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ "ማቴ 5:6 የመጨረሻ ግባቸው የመንግስቱ ወራሾች መሆን ነው።


ቅዱሳን ሰዎች ሰው ሲሆኑ እንደ መላእክት የሚኖሩ፣ በምድር ሳሉ ምድራዊ አሽንክታብን የናቁ፣ እነርሱ የእግዚአብሔር መሆናቸውን ከማመን በስተቀር በምድር ላይ የኔ ነው የሚሉት ምንም ነገር የሌላቸው፣ በመንፈስ ከመላእክት ጋር የሚዘምሩ፣ ከቅዱሳን ጋር የሚያመሰግኑ  ጸጋ እግዚአብሔርን የተላበሱና ሰማያዊ ኅብስት እየተመገቡ የሚኖሩ ናቸው። ህይወታቸውን በሙሉ በተጋድሎ ያሳለፉ ቅዱሳንን ታሪክ ማንበብ ራሳችንን ለመልካም ስራ እንድናዘጋጀው ይረዳናል። ህገ እግዚአብሔርን ስለ መጠበቃቸው፣ ስለ ጽናታቸውና ትዕግስታቸው፡ተግተን ባነበብንና በተገነዘብን ቁጥር የራሳችንን ህይወት እንድንመረምርና በመልካም ምግባር የዳበርን  ከሰይጣናዊና እንስሳዊ አስተሳሰብ የራቅን፣ ከእኩይ ተግባር የተቀጠብን እንድንሆን ይረዳናል።ፍጹም ቅንነትና ርህራሄ የሞላበት ህይወታቸው እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ምን እንደሆነ ያሳየናል። ፍጹም ፍቅር፦ ትዕዛዘ እግዚአብሔርን ያስፈጽመናል፤ ሰላምና መረጋጋትን፣አንድነትን፣ልግስናን፣ የበደሉንን ይቅር ማለትን፣ የባልንጀራችንን በደል መሸፈንን ያስተምረናል።

2, ቅዱሳን ሰማእታት
የሰማዕትነት መሰረቱ ምንኩስና ሲሆን የምንኩስና የትውልድ ስፍራ ደግሞ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ነች። ገዳማዊ አኗኗር ለመንፈሳዊነትና ለሰማዕትነት አመቺ ሆኖ ያገኘው በምድረ-በዳ (ገዳም) ለዘጠና አመታት የኖረው የመጀመሪያውና አንጋፋው መናኝ አባታችን ቅዱስ ጳውሊ ነው።
፠ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሀሴትንም አድርጉ፣ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።" በማለት ጌታችን ደቀ መዛሙርቱ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር አስቀድሞ ገልጾላቸዋል።ማቴ ፭:፲፪"...ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፤ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። "ማቴ፲:፴፱
በ፪፻፳፰ ዓ/ም ሰማዕቱ ቅዱስ ሂፖሊጦስ st.Hippolytus "ሰማዕታት ይህን ዓለም በጸጋ ይተዋሉ ፣ ኃጥያታቸውም ይሰረይላቸዋል ፣ እንደ ሰለስቱ ቅዱሳን ወጣቶች ሰማያዊ አክሊል ይሸለማሉ። በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነት ከፍተኛ ቦታ ነበረው።" በማለት ገልል።
ከ፪፻፶፮-፪፻፶፰ ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ ንጉስ ዳኬዎስ Emperor Decius የክርስትናን ሃይማኖት ለማስወገድ አዋጅ አወጣ። በዚህ አዋጅ መሰረት የተቀረጸ በድን ጣዖት ላመለከ የሞት ቅጣት ይፈረድበት ነበር። ብዙ ግብጻውያን ክርስቲያኖች ራሳቸውን በመሰዋዕትነት አሳለፉ።የተቀሩትም ወደ ምድረበዳ ተሰደዱ። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁና የመጀመሪያው ግብጻዊ መናኝ አባ ጳውሊ የበረሃ ኑሮውን የተያያዘው። ንጉስ ዳኬዎስ ከበርበሮች ጋር ሲዋጋ ሞተ። በእርሱ ምትክ ንጉስ ቫሌሪያን Valerian (፪፻፶፫-፪፻፷) ህጉን በማደስ ጣዖት እንመልኩ አወጀ። ከቫሌሪያን ሽንፈት በኋላ ለአርባ ዓመታት ቤተ ክርስትያን በሰላም ቆየች።
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በንጉስ አርያኖስ Arrianus ዘመን የተቆረቆረችው አንቴኖፖሊስ ወይም አንሴና Antenoepolis or Ansea በግብጽ አሉ ከሚባሉ የክርስቲያን መናኸሪያ አንዷ ነበረች።
ከጥንቱ ዘመን ሰማዕታትም በግብጽ ለሃይማኖታቸው ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ከሰጡት ክርስቲያኖች ውስጥ የአብዛኛዎቹ ደም የፈሰሰበት ቦታ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ ከከተማዋ በስተምዕራብ በሚገኘው ኮረብታማ ቦታ ላይ በመወሰድ የሞት ቅጣት ተቀብለዋል። በዚሁ የብዙ ክርስትያኖች ደም በፈፈሰበት ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው 
ውሃ ጉድጓድም ቦታውን ታሪካዊ ካሰኙት ነጥቦች አንዱ ነው።
ምንኩስና የምድራውያን ወይም የሰብአውያን መላእክት ህይወት እንደሆነ ይነገራል። ራስን ከዓለማዊ ፍላጎትና ከምድር አሽንክታብ ቆጥቦና ለይቶ በቅድስና ለመኖር ዋነኛ መሣሪያው ምንኩስና ነው። ይህም ለሰማዕትነትና ለብትህውና ጥርጊያ መንገድ ያዘጋጃል። አንድ ሰው መነኮሰ ማለት ዓለማዊ ወይም ሥጋዊ ዓይኑን ጋርዶና ዓይነልቡናውን ከፍቶ ለእግዚአብሔር በማደር በተመስጦና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ኖረ ማለት ነው። የዚህ ውጤት ደግሞ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት ይሆናል።
መንፈሳዊ ፍሬ ማለት፦ ፍቅር፣ ደስታ ፣ሰላም ፣ ቅንነት፣ ትዕግስት፣ ቸርነትና ትህትናን ገንዘብ ማድረግ ነው። ይህ የሚገኘው ደግሞ ራስን በውስጥም በአፍአም ለእግዚአብሔር ማስገዛት ሲችሉ ነው።

ታሪክ ጸሃፊው ላክታንቲየስ Lactantius "ሰማዕትነት ኢ-ክርስቲያኖችን ለማስተማሪያ
 ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲመጡ፣ ለአገልግሎትም እንዲተጉ የሚያበረታታ ታላቅ መሳሪያ ነው። ሰማዕትነት ሰማዕታት ለፈጣሪያቸው ያላቸውን ታላቅ ፍቅርና ክብር እስከ ሞት ድረስ የሚያሳዩበት ብቸኛ መንገድ ነው። እነርሱን በማየት ብዙ ከሐድያን ወደ ክርስትናው ዓለም ይመለሱ ነበር።" ብሏል። ህይወታቸውን ለእውነተኛዋ ወንጌል አሳልፈው የሰጡ ሰዎች የክብር ቦታቸው ከቀዳማውያን ክርስቲያን አባቶቻችን ጋር ነው።
በቅብጥ ስንክሳር ላይ ከተጠቀሱት ፫፻፹፩ ሰማዕታት ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ከ፪፻፺፮-፫፻፭ ዓ/ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ መከራን የተቀበሉ ናቸው። ከእነርሱም ውስጥ ከደሀ ሸማኔ አንስቶ እስከ ተራ ወታደር፣ ጀኔራል፣ ሀብታም፣ ነጋዴና ንጉሳዊ ቤተሰብ ይገኙባቸዋል። አንዳንዶች ሰማዕታት ለተጋድሎ ከመነሳታቸው በፊት ሰማያዊ ጥሪ ይደረግላቸዋል። ለምሳሌ ቅዱስ ኢሶዶር St.Isidore የተባለ ሰማዕት በቅዱ ሚካኤል አማካኝነት ነበር ለሰማዕትነት የተጠራው። ቅዱስ ሚናስ ተአምር ሰሪው St.Mina the miraculous ደግሞ እግዚአብሔር በዙፋኑ በሰማዕታት ታጅቦ ሳለ በራዕይ ተገለጠለት። የአንጾኪያው ጀነራል የቅዱስ ፋሲለደስ St. Basilides Stratelates of Antioch ልጆች የሆኑት ቅዱስ አፓተር St.Apater እና ቅዱስ ኢሬን St.Eirene በመላዕክት ተጠርተው ወደ ግብጽ በመሄድና በእስር ቤት ለረጅም ጊዜ በመቆየት ነበር ሰማዕታት የሆኑት። እነዚህ ሁለት ቅኡሳን በቅብጥ አባድርና ኢራ SS.Abadir & Ira'i በመባል ይታወቃሉ። ቅዱስ ቴዎድሮስ እስትሬሪለትስ St.Theodore Stratelates ከሰማዕትነቱ በፊት ድራጎን ገድሏል።

ቅዱሳን ሰማዕታት ከእለተ ሞታቸው በፊት በያሉበት ሀገር ነገስታት ፊት ይቀርባሉ eror's Goverror of Upper Egypt እጅ የእነ 
ቅዱስ ጁልየስ ዘ-አክፋ፣ አባድርና ኢራ SS Julius of Aqfas, Apater & Eirene እና ሌሎችም ሰማዕታት ህይወት አልፏል። ቅዱሳኑ ይህ ነው  የማይባል ሥቃይ ቢደርስባቸውም በጸሎታቸው ጸንተው ይቋቋሙታል። ከዚያም አልፈው ይህን በደል ለሚፈጸምባቸው ሰዎች የኃጥያትን ስርየት ይለምናሉ። ቅዱሳን መላእክት አብረዋቸው ሆነው ህመማቸውን በማስታገስና ቁስላቸውን በመፈወስ ይረዷቸዋል። ተጋድሎአቸውን በትጋት እንዲፈጽም ያጽናኗቸዋል። ቅዱስ አቢስክሪዮስ St.Abiskhirun ይህ በተደጋጋሚ ተደርጎለታል።

ህጻኑ 
ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅዱስ ኢየሉጣ SS.Cyriacus & Julitta ለጣዖት እንዲሰግዱ ሲጠየቁ ቅ/ኢየሉጣ " ለጣዖት መስገድ አግባብ መሆን አለመሆኑን ከሶስት አመቱ ህጻን ጠይቃችሁ ተረዱ" ብላ መለሰች። ህጻኑም በተጠየቀ ጊዜ ጣዖት ሀሰተኛ አምላክ መሆኑን ተናገረ። ቅ/ኢየሉጣ በዚህ ምክንያት ስለሚደርስባቸው ቅጣት ፍርሃት ቢያድርባትም፤ በህጻኑ ቂርቆስ አበረታችነት ሁሉንም በመቋቋሟ፤ የቀለጠ መዳብ ላይ ቢጣሉም እንኳ ለእነርሱ የተሰማቸው መንፈስ ቅዱስ ያለበት የመጽናኛ የመታደሻ ቦታ ላይ እንደ ተቀመጡ ነበር እንጂ ቃጠሎው አልተሰማቸውም።እነርሱ የተጣሉበት እሳት ፍንጣሪ ንጉሱ ላይ ቢያርፍበት አጥንቱ ድረስ ገብቶ አቃጥሎታል።ይህ ንጉስ በህጻኑ ቂርቆስ አማካኝነት ፈውስ ቢደረግለትም በክርስቶስ ግን አላመነም፣ ልቡ እንደ ፈርዖን ልብ ደንድኖ ቀረ። አስደናቂው ተአምር ግን እነዚህ ቅዱሳን ከሞት በኋላ ዳግም በመነሳት በህይወት መገኘታቸው ነው። ቅዱስ አይሲዶር St.Isidore አምስት ጊዜ ተገድሎ ከሞት ተነስቷል፣ የልዳው ቅዱስ ጊዮርጊስም ሶስት ጊዜ ሞቶ ተነስቷል።
የእነዚህ ቅዱሳን ከሞት በኋላ መነሳት ለብዙ ሃይማኖት የለሾች ድህነት ምክንያት ሆኗቸዋል። ለዚህም ነው የታሪክ ሰዎች ሲጽፉ "ሰማዕትነት የኢ-አማንያን ትምህርት ቤት ነው" የሚሉት።በህጻኑቂርቆስና በእናቱ ኢየሉጣ ምክንያት አስራ አንድ ሺህ ሰዎች ክርስቲያን ሆነዋል።የንጉስ ድዮቅልጥያኖስ ሚስት በቅዱስ  ጊዮርጊስ አማካኝነት ከኢ-አማኒነት ከተመለሱት ሶስት ሺህ ክርስቲያኖች አንዷ ስትሆን ሁለተኛው አብሮ አስፈራጅ የነበረውና በጭካኔው ወደር የሌለው  አርያኖስ ነው።

 "ሰማዕትነት በሥጋ  መሞት/ መጎዳት ብቻ አይደለም። ነገር ግን ድንግልና፥ የመንፈስ ድኅነት፣ የዓለምን አሸንክታብ መናቅ፣ የተቸገረን መርዳት፣ ያዘነን ማጽናናት፣ ቅንነት፣ የዋህነት፣ ስለ ጽድቅ መራብና መጠማት፣ የልብ ንጽህና፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ ጠላትን መውደድ" ነው። ተብሎ በአንቀጸ ብጹዓን እንደተጻፈው "ክርስቲያኖች ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በአንክሮ ከፈጸሙ በጽድቅ መሰላል ወደ እግዚአብሔር ሊደርሱ ይችላሉ" ብለዋል። ማቴ ፭፥፫-፱
በአራተኛው መ/ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ በንጉስ አርያኖስ Arrianus ዘመን የተቆረቆረችው አንቴኖፖሊስ ወይም አንሴና Antenoepolise or Ansena በግብጽ አሉ ከሚባሉት የክርስቲያን መናኸሪያ አንዷ ነበረች። ከጥንቱ ዘመን ሰማዕታትም በግብጽ ለሃይማኖታቸው ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ከሰጡት ክርስቲያኖች ውስጥ የአብዛኛዎቹ ደም የፈሰሰበት ቦታ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ ከከተማዋ በስተ ምዕራብ በሚገኘው ኮረብታማ ቦታ ላይ በመወሰድ የሞት ቅጣት ተቀብለዋል። በዚሁ የብዙ ክርስትያኖች ደም በፈሰሰበት ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው የውኃ ጉድጓድም ቦታውን ታሪካዊ ካሰኙት ነጥቦች አንዱ ነው። ከዚሁ ከክርስቲያን ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ ምክንያት የቅብጥ የዘመን አቆጣጠር ወይም ባህረ ሐሳብ ዘመነ ሰማዕታት በመባል ይታወቃል። የተጀመረውም በ፪፻፹፬ ዓ/ም ድዮቅልጥያኖስ Diocletian በሮም በነገሠበት አስከፊ ዘመን ነበር። ከ፪፻፹፬-፫፻፭ ዓ/ም ድዮቅልጥያኖስ ህዝባዊ ጦርነትን ያቆመበትና ኃያል መንግሥት መሆኑን ያሳየበት ዘመን ሲሆን በ፪፻፺፰ ዓ/ም በቤተ ክርስቲያን ላይ ጦርነት አወጀ። ከ፫፻፫-፫፻፲፪ ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ ክርስቲያኖችን ከሥልጣን በማውረድና ወታደሮችን ከሥራ በማባረር በየካቲት ወር ፫፲፳፮ ዓ/ም እያንዳንዱ ሰው ለጣኦት እንዲሰዋ የሚል በጽሁፍ የተደገፈ አዋጅ በሀገሪቱ ሁሉ አወጀ። መከራው ቢበዛባቸውም ለጣኦት ከመስገድ ይልቅ በዚያው ልክ የሰማዕታት ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ቁጥራቸው በአኅዝ ለመወሰን ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። አብዛኛው ግብጻዊ ክርስቲያን በመሆኑ ጭፍጨፋው የሁሉንም ቤት አንኳኳ። አውሳብዮስ የተባለው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሀፊ "በሺህ የሚቆጠሩ ቅብጦች ሞቱ፣ በአንድ ቀን ብቻ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ህጻናት አንገታቸው ይቆረጥ፣ ወደ እሳትም ይጣል ነበር" ብሎ ጽፏል።


           ===========================++++++===================

No comments:

Post a Comment