Friday 6 September 2013

ስብሓት ነጋ ጥፋቷን ስለሚመኙላት ቤተ ክርስቲያንና መግደያ ብትር ሊያደርጉት ስለሞከሩት ማኅበረ ቅዱሳን ይወተውታሉ

‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሚያስተኛ አይደለም
/አቶ ስብሓት ነጋ/
(ኢትዮ-ምኅዳር ቅጽ 01 ቁጥር 34፤ ረቡዕ ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋራ በመተባበር በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ከነሐሴ ፳፩ – ፳፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ‹‹የሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር እሴት በማጎልበትና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የሀገራችንን የሕዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባኤ ላይ ‹አቦይ› ስብሐት ነጋ በመገኘት አነጋጋሪ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ አንጋፋው የህወሓት/ኢሕአዴግ መሥራችና የጀርባ ሰው የሚገልጹት ሐሳብ የመንግሥትን ቀጣይ ርምጃ ያመላክታል በሚል በአጭሩ እንደሚከተለው 
አክራሪነት ይዘቱ ሃይማኖታዊ እንዳልኾነ ሕዝቡም የተገነዘበው ጉዳይ መኾኑ ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ ሃይማኖትን የፖሊቲካ መድረክ የሚያደርጉት የሽብርተኝነት ተግባር ለመፈጸም መኾኑ ግልጽ የኾነልን ይመስለኛል፡፡
አክራሪነትና ጽንፈኝነት በሃይማኖት ውስጥ ማስገባት የመጀመሪያው አደጋ ሲኾን በዚህ ኹኔታ ሃይማኖቱም ሃይማኖት አይኾንም፡፡ አማኞች፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት በየሃይማኖታቸው ውስጥ ሲታይ ሃይማኖታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡
አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን (የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ) እንዳለውም፣ በጣም አስደናቂ የኾነውን የኢትዮጵያ ዕድገት ማደናቀፍ ከማንኛውም ወንጀል በላይ በሕዝብ ላይ ከባድ ወንጀል መፈጸም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዓመታት ሲሠቃይ የነበረ በመኾኑ አሁንም ሕዝቡን ለሥቃይ መዳረግ ተወዳዳሪ የሌለው ወንጀል ነው፡፡
በማንኛውም ሃይማኖታዊ አክራሪነት እና ጽንፈኝነት፣ በምንም ዐይነት ኹኔታ አንድም ሰው ለአንድ ደቂቃ እንኳ ተዘናግቶ መተኛት የሌለበት ሲኾን በተለይ ይህን ነገር በጥብቅ በሁሉም መንገድ መታገል አለብን፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ዕድገት የሚቀናቀነው የውጭ ተቀናቃኝ ነው፡፡ የእነዚህን ተቀናቃኞች ዓላማ በመያዝ በአክራሪነትና በጽንፈኝነት መልክ ታላቅ ክሕደት መፈጸም ከባድ አገራዊ ክሕደት ነው፡፡ የውጭ ጠላት ቀላል ስላልኾነ አንድም ሰው ሳይቀር በጣም ተጠናክረን መመከት ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ የፖሊቲካ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ዝንባሌ ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥቱ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጸደቀው የራሱ ሕገ መንግሥት ስለኾነ ሕዝብ በመራራ ትግል ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት መጣስ የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ነው፡፡
በዚህ ስብሰባ ከፍተኛ ግንዛቤ መያዙ በጣም የሚያስደስት ነው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ተስፋ ነው፡፡ ለውጭ ጠላት ደግሞ ሲጠብቀው የነበረ ብጥብጥ መቅረቱ ሕዝብን የሚያስደስት፣ ጠላትን ደግሞ የሚያሳፍር ነው፡፡