Thursday 8 November 2012

ለአዲስ አበባ አራት አህጉረ ስብከት ሥ/አስኪያጆች ተሾሙ



(ደጀ ሰላም ጥቅምት 29/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 8/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በቅዱስ ሲኖዶስ የተቋቋመው ኮሚቴ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የገነገነውን ሙስናና ሌሎችም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያቀረበውን ጥናት የመረመረው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሀገረ ስብከቱ በአራት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ እንዲደራጅ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ስለ አከፋፈሉ እና አደረጃጀቱ መነሻ “አቤት ባዩ በዛ፤ ጩኽት በዝቷልና” በማለት የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ ለጋዜጠኞች ያስረዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል÷ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በየአካባቢያቸው እንዲስተናገዱ በፓትርያርኩ ጊዜ በአባቶችና ሊቃውንት ተጠንቶ ቀጠሮ ተይዞበት የቆየ ጉዳይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ቀሲስ በላይ መኰንን ከሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲንነት ተነሡ


(ደጀ ሰላም ጥቅምት 29/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 8/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ባለፉት የዜና ዘገባዎቻችን ስንጠቅሳቸው የነበሩትና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን የነበሩት ቀሲስ በላይ መኰንን ከዚህ ሓላፊነታቸው መነሣታቸው ታውቋል፡፡ የደጀ ሰላም ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሰሞኑን በሚደረገው የከፍተኛ ሓላፊዎች ሽግሽግ ቀሲስ በላይ መኰንን የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው አማካሪ ኾነው መመደባቸውን እየተነገረ ነው፡፡ በርካታ ዋና ዲኖች በፍጥነት በሚቀያየሩበትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሳይሆን የመቅጫ ቦታ ተደርጎ በሚታሰበው መንፈሳዊ ኮሌጅ ለስድስት ወራት የቆዩት ቀሲስ በላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውሳኔ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸው የታወቀው “በእድሳትና ለዲግሪ መርሐ ግብር መጀመር ይደረጋል በተባለው ዝግጅት” ሰበብ የመንፈሳዊ ኮሌጁ የመማር ማስተማር ሂደት ከሁለት ወራት በላይ በተስተጓጎለበት፣ ይህንንም ተከትሎ የደቀ መዛሙርቱ (በተለይም የሰሚናር ኮርሰኞቹ) አቤቱታ ጎልቶ በሚሰማበት ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡