Friday 19 October 2012

የቤተክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ዕውቅና እንዲያገኝ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ


በታምሩ ጽጌ(reporter)


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት መንፈሳዊ ጉዳዮችን የምትከታተልበት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የሚያገኝበት ሁኔታ መመቻቸቱንና ለተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ እየተመረመረ መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያለው ግንኙነትና እንዴት ማጣጣም እንደሚቻል ረቂቅ ሕጉ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ በትናንትናው ዕለት የተጀመረውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ 31ኛ መደበኛ ስብሰባን አስመልክቶ የቤተክህነቱ የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረክርስቶስ፣ ‹‹ቤተክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አላት፡፡ መንፈሳዊ ቦታ በመሆኗ ግን እስር ቤት የላትም፡፡ ፖሊስም የላትም፡፡ ፍርድ ቤቱ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው መንፈሳዊ ተግባራትን ነው፤›› ብለው፣ የተጋጩ ሰዎችን በእርቅና በስምምነት እንዲፈቱ ማድረግ ነው፣ ከመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ውጭ የሆነ ጉዳይ ካጋጠመ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡