Thursday 2 August 2012


ኦርቶዶክሳውያን ድረ-ገጾችን ለማዘጋት እየተዶለተላቸው ይገኛል


(አንድ አድርገን ሐምሌ 25 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- ዘመኑን ዋጁ እንዲል ቃሉ ከጊዜ ወዲህ ድረ-ገፆች መረጃን ለምዕመናን እያስተላለፉ ይገኛሉ ፤ የአምስት ዓመት እድሜ ያስቆጠረችው በእድሜ አንጋፋዋ “ደጀ ሰላም”ን ጨምሮ ፤ አንድ ዓመት በቅጡ ያልሞላት “አንድ አድርገን” ፤ ደቂቀ ናቡቴና አሐቲ ተዋህዶን የመሰሉ ገጾች የቤተክርስትያንን መረጃዎች የመናፍቃንን አካሄዶች በየጊዜው በማውጣት ይታወቃሉ ፤ ከዚህ በተቃራኒ በሌላኛው ጎራ የቆሙ የተሀድሶያውያን እና የመናፍቃን ገጾች ያለመታከት ቤተክርስትያኒቱን ለመከፋል ያለ እረፍት እየሰሩ ይገኛሉ ፤ “አባ ሰላማ”ና አውደ ምህረትን የመሰሉት ገጾች ውስጥ በሚገኙ እነሱን ከሚመስሏቸው ሰዎች ጋር በመሆን መረጃዎችን እየተቀባበሉ ምንፍቅናቸውን እና ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የሆነ አካሄዳቸውን በጽሁፋቸው እየገለጹ ይገኛሉ ፤ የነዚህን ገጾች ጽሁፍ አይቶ እነ ማን እንደሆኑ ለማወቅ የተለየ ብልሀትን የጠለቀ ምርመራ ማድረግን አይጠይቅም ፤ ቅዱሳንን የሚዘልፉና  ገድላትን የሚያንቋሽሹ ጽሁፎቻቸው ምስክሮቻቸው ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ደጀ-ሰላም እና አንድ አድርገን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበቡ ቢደረግም እነዚህን የመሰሉ የተሃድሶያውያን ገጾችን ግን የደረሰባቸው የለም ፤ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ከወደ አሜሪካ እነዚህን ገጾች እንዲታገዱ የሚጠይቅ ስብሰባ መደረጉን የአቋም መግለጫ መውጣቱን የሚያመላቱ መረጃዎች ወጥተዋል ፤ ከበስተጀር እየተዶለተላቸው ይገኛል ፤ እነርሱ አልገባቸውም እንጂ “አንድ አድርገን” እና “ደጀ ሰላም” በፌስ ቡክ ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ የማይነበቡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ፤ አንድ አድርገን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አሁን ለ3ተኛ ጊዜ እክል ገጥሟታል ፤ ከዚህ በፊት አንድ በአንድ እየተባለ ሁለት ገጾች ቢዘጉም አሁን ግን በተለዋጭነት መረጃ ለማስተላለፍ የምትተቀምባቸው 6 ገጾች በጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሩ ተደርገዋል ፤ ይህ ሁሉ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ውጭ በቀን ቢያንስ በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች እንደምትጎበኝ የብሎጉ ስታተስ ይጠቁማል ፤ ከቀናት በኋላም እነርሱ መዝጋት ካልሰለቻቸው እኛ መክፈቱ ስለማይከብደን ተጨማሪ አማራጭ ገጾች እንደምንከፍት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
እንደ “አንድ አድርገን” እምነት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የተሃድሶያውያን እና የመናፍቃንን አካሄድ መረጃዎች ሰዎች ዘንድ አድርሰናል ብለን አናምንም ፤ እስከ አሁን ከወጣው መረጃ እየሰበሰብንና እያጠናከር ያሉ ጉዳዮች ይበዛሉ ፤ የሐዋሳው ጉዳይ ዳግም ለመቀስቀስና ምዕመኑን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት በማሴር እነ ያሬድ አደመ ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ ፤ ቅዳሴ ቤተክርስትያን እያስቀደሱ ወንጌሉን ደግሞ በአዳራሽ የሚል ፈሊጥ በመያዝ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፤ ውስጦቻችን ተሰግስገው ያሉ አመቺ ጊዜ የሚጠብቁ ሰዎች ተበራክተዋል ፤ አሁንም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እና መናፍቃኑ አዳራሽ የሚመላለሱ ሁለቱም ጋር የሚያገለግሉ ሰዎች ተበራክተዋል ፤ በተመሳሳይ አንዳንድ ከተማዎች ላይ የቅባት እና የጸጋ አስተምህሮ ያላቸው ሰዎች ምዕመኑን እያመሱት ይገኛሉ ፤ ከነዚህ በተጨማሪም አሁን የማናመላክተው  በርካታ ነገሮችም አሉ ፤ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ወደፊት ጊዜውን ጠብቀው የሚፈነዱ ቦምቦች ናቸው ፡፡
ስለዚህ ማንም የድብቅ ሸንጎ በመጥራት እኛ ላይ ብሎጋችንን ለማዘጋት ቢያሴሩ ፤ ከቤተክህነት በቀጥታ ለመንግስት ብሎጎቹ እንዲዘጉ ደብዳቤ ቢጻፍ ፤ መንግስትም ከራሱ ፍላጎት በመነሳት በሌላ አይን በመመልከት ብሎጋችንን ቢዘጋ ፤ እኛ ግን ከመጻፍ ወደ ኋላ የሚገታን አንዳች ነገር አይኖርም ፤ እነርሱ ለመዝጋት ካልደከማቸው እኛ አዲስ ለመክፈት አይሰለቸንም ፤ አፍራሽ ግብረ ሃይሎችን አይተን ዝም የምንልበት አይን ሰምተን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን የምናልፍበት ጆሮ የለንም ፤  ጽሁፎቻችን ዋልድባ ከሚገኙ መነኮሳት ጀምሮ በተለያዩ ሀገሮች ድረስ ተደራሽ መሆን ችሏል ፤ ቀድሞ በቀን ከ5ሺህ ሰዎች በላይ ቢጎበኙንም አሁን ብሎጉ ተዘግቶ ቢያንስ በቀን መረጃውን ከ3ሺህ በላይ ሰዎች ጋር ስለምናደርስ ተስፋ ባለመቁረጥ እንሰራለን፡፡
ቸር ሰንብቱ