Tuesday 22 January 2013

ይድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል አንድ)



ይህንን ደብዳቤ ላንቺ የምጽፈው የገናን በዓል ከልቤ የምወደው በዓል ስለሆነ ነው፡፡ የምወደው ደግሞ የገና ዛፍ ተተክሎ፣ በጥጥ ተውጦ፣ በከረሜላ ተከብቦ፣ በመብራትም አሸብርቆ ስለሚያስደስተኝ አይደለም፡፡ እንዲያውም እንዲህ 
ያለው ነገር ብዙም አይመስጠኝም፡፡ ቤተ ልሔም ዋሻ ውስጥ ለተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛፍ ማሸብረቅ፣ በረዶ አይታ በማታውቅ ሀገር ውስጥ የበረዶ ምሳሌ የሆነውን ጥጥ ማግተልተል፤ ልጇን የምታለብሰው አጥታ የበለሶን ቅጠል ላለበሰች እናት ከረሜላና ኳስ ማንጠልጠል ለእኔ ትርጉሙ አይገባኝም፡፡ መቼም ፈረንጅ መሆን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ እርሱ ሲያብድ የሠራውንም ቢሆን ፋሽን ነው ብሎ የሚከተለው አለማጣቱ ነውና ምን ይደረግ፡፡

ይድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም (ክፍል ሁለት)


ድንግል ማርያም ሆይ 


ለፈው እንደሰማሽኝ ዛሬም ትሰሚኛለሽ ብዬ ነገሬን እቀጥላለሁ፡፡ 


አንቺ በቤተልሔም ከተማ ማደርያ አጥተሽ እንደተንከራተትሽው ሁሉ ነፍሰ ጡር ሆኖ ቤት መከራየትማ የማይታሰብ ነው፡፡ አከራዮቹ የልጁን የሽንት ጨርቅ ማጠቢያ፣ የገንፎውን ማብሰያ፣ የጡጦውን መቀቀያ፣ የእንግዳውን ማስተናገጃ ሁሉ አስበው የቤት መሥሪያ ያስከፍሉሻል፤ ያለበለዚያም አንቺን እንዳሉሽ ‹ማደርያ የለም› ይላሉ፡፡ 


እኔማ ሳስበው አሁን አሁን ሕዝቡ መጥኖ መውለድ የጀመረው የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት ገብቶት አይመስለኝም፡፡ አከራዮች ናቸው የሕዝባችንን ቁጥር እየቀነሱት የመጡት፡፡ ልጅ ካለሽ፣ ያውም ከሦስት በላይ ከሆኑ፣ ማን ያከራይሻል፡፡ ብትከራይም ልጆችሽን እንደ ጥጃ ስትጠብቂ መኖርሽ ነው፡፡ ‹ይህንን ነኩ፣ ያንን ሰበሩ፣ ይህንን ቆረጡ፣ ያንን አበላሹ፣ እዚህ ገቡ፣ እዚያ ወጡ› እየተባለ በየቀኑ ሮሮ ነው፡፡ ልጅ ደግሞ በተገዛና በተከራየ ቤት መካከል ያለው ልዩነት አይገባውም፡፡ እና በዚህ ምክንያት ቤት ሳይሠራ ላለመውለድ፣ ከወለደም ከሁለት በላይ ላለመውለድ ስንቱ ወስኗል፡፡