Thursday 9 January 2014

ሰበር ዜና – ተቃዋሚ ነኝ ባዩ የእነኃይሌ ኣብርሃ ቡድን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ይቅርታ ጠየቀ

ተቃዋሚ ነኝ ባዩ የእነኃይሌ ኣብርሃ ቡድን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ይቅርታ ጠየቀ፤ ‹ተቃውሞው›÷ የቡድኑ መሪዎች አላግባብ ባካበቱት ሀብት በሕግ ላለመጠየቅ በመከላከያነት የጀመሩት መኾኑን ለሊቀ ጳጳሱ አምነዋል፤ ይቅርታው የሙሰኞች ሽፋን እንዳይኾን የሚያስጠነቅቁ የተቋማዊ ለውጥ ኃይሎች የአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱን በመደገፍ ነገ ዐርብ ፓትርያርኩን ለማነጋገር የሚያደርጉትን ዝግጅት አጠናክረው ቀጥለዋል


ተቃዋሚ ነኝ ባዩ ቡድን ይቅርታ ለመጠየቅ የተገደደው፣ የቡድኑ ሰብሳቢ የኾኑት የኮተቤ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ ሐዲስ ‹‹ተቃውሟችን ከመዋቅር ጥናቱ እንጂ አቡነ እስጢፋኖስ ይነሡልን የሚል ጥያቄ የእኛ አይደለም›› በሚል ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በፓትርያርኩና በስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊት በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ላይ በተሰነዘረው መሠረተ ቢስ ውንጀላ ባለመስማማት ከኹሉ ቀድመው ሊቀ ጳጳሱን ይቅርታ መጠየቃቸው በቡድኑ አባላት መካከል የፈጠረው መከፋፈል ነው፡፡

‹‹የዘካርያስ እናት ሞተው ለልቅሶ ራያ በነበርንበት ወቅት የሀ/ስብከቱ አንዳንድ የመምሪያ ሓላፊዎች [የለውጡ ደጋፊ መስሎ በርካታ አሻጥሮችን የሚፈጽመው አደገኛው ጉቦኛ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ] ደውለው÷ አቡነ እስጢፋኖስ አንተን ለመክሠሥ ከመዝገብ ቤት ሰነድ እያወጡብኽ ነው፤ ኃጢአት እየተፈለገብኽ ነው፤ ወኅኒ ሊከቱኽ ነው ስለተባልኹ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ስሜት የተናገርኹት ነው፤ የጠላ ሰው ብዙ ይናገራል፤ ብፁዕነትዎ አስቀይሜዎታለኹ፤ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሚመጥን ከእርስዎ የተሻለ ሊቀ ጳጳስ ከየት ይመጣል? በልጅነት የተናገርኹት ነው፤ የአባትነትዎ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡›› /የተቃዋሚ ነኝ ባዩ ቡድን መሪ ኃይሌ ኣብርሃ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጫማ ላይ ወድቆ ከተናዘዘው/
የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ‹‹ከሓላፊነታቸው ይነሡ፤ ከሲኖዶስ አባልነት ይሰረዙ›› የሚለው ጥያቄ ኃይሌ ኣብርሃ ከምክራቸው ውጭ ያቀረበው መኾኑን በመጥቀስ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊት ስለተናገረው የድፍረት ቃል በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እግር ላይ ወድቀው ይቅርታ የጠየቁት የቡድኑ መሪዎች፣ የሀ/ስብከቱን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት መቃወማችንን ግን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የ‹ተቃውሟቸው› ትኩረት ጥናቱን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን መሥራቱና በጥቂት አንቀጾች ላይ ብቻ የተወሰነ›› መኾኑን የተናገሩት የቡድኑ መሪዎች፣ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኝነታቸው አኳያ ጥያቄዎቻቸውን እየለጠጡ ሽፋን የሚሰጡላቸውን ብሎጎች ‹‹የመናፍቃን›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ባካበቱት ሀብትና በከባድ እምነት ማጉደል በሕግ የመጠየቅ፣ በሰነዘሩት መሠረተ ቢስ ውንጀላ ደግሞ ሥነ ምግባራዊ ርምጃ ይጠብቃቸዋል የተባሉት የተቃዋሚ ነኝ ባይ ቡድኑ ቀንደኛ መሪዎች፣ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጫማ ላይ ወድቀው ይቅርታ መጠየቃቸው በእብሪታቸው ላሞገሷቸው አቡነ ሳዊሮስና የተቋማዊ ለውጥ አመራር ንቅናቄውን በጠዋት ጤዛ ለመሰሉት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኝ ብሎጎች ታላቅ ኀፍረትና መቅሰፍት ነው፡፡
የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ ለውይይት እንዲቀርብ ሲወስን ሰነዱ እንዲተች በመኾኑ ድጋፍ ይኹን ተቃውሞ የሚጠበቅና መብትም መኾኑን የተናገሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ቡድኑ ተቃውሞውን በስሜታዊነትና መዋቅሩን ሳይከተል ያቀረበበት መንገድ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ በጥናቱ ይዘት ላይ ብቻ የተመሠረተ ትችቱን ደረጃውን በጠበቀና በተደራጀ መንገድ እንዲያቀርብ አሳስበውታል፤ በምትኩ ከሁለት ሚልዮን በላይ የሀ/ስብከቱ ካህናትና ምእመናን ተወካዮች ከፍተኛ ድጋፋቸውን ያረጋገጡለትን ጥናት በማኅበረ ቅዱሳን እያሳበቡ እቃወማለኹ ማለት እንደማያዋጣቸው መክረዋቸዋል፤ በአባትነታቸው ግን የይቅርታ ጥያቄውን መቀበላቸውንና ይቅርታ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የቡድኑ መሪዎች መዋቅሩን ባልተከተለ የተቃውሞ አቀራረባቸውና በዐመፅ በተሞላ ዘለፋቸው ከሚከተላቸው የከፋ ቅጣት ይልቅ ይቅርታ እንዲጠይቁ አግባብቻለኹ የሚለው አሸማጋይ አካል አንዳንድ አባላት (በስም ለይቶ መጥቀስ ይቻላል)÷ነገ፣ ጥር ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በ9፡00 የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ካህናትና የአብነት መምህራን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ የተያዘላቸውን የድጋፍ መግለጫ ስብሰባ መርሐ ግብር በ‹‹ይቅርታ ተጠይቋል›› ሰበብ የማኮላሸት ዓላማ እንዳላቸው ተጋልጧል፡፡ በስም ተለይተው የተጠቀሱት እኒህ ሦስት የአሸማጋይ አካሉ አባላት በተቋማዊ ለውጥ ተነቃናቂ ኃይሎች የጥንቃቄ ክትትል እየተደረገባቸው ነው፡፡

* * *

የፓትርያርኩ አማካሪ በሚል ይፋ ባልተደረገ የሥራ ድርሻ የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት በቅርበት እንደሚቆጣጠሩ የሚነገርላቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የተቃዋሚ ነኝ ባይ ቡድኑን በኅቡእ የሚያስተባብሩ እንደኾኑ ከቡድኑ አፈንግጠው የወጡ አባላት አጋልጠዋል፡፡ ንቡረ እዱ፣ አባላቱ የቻሉትን ያህል አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ሠራተኞች ቀስቅሰው እንዲያሰልፉ እንዳግባቧቸው የሚናገሩት እኒህ ወገኖች፣ ንቡረ እዱ የሚያስተባብሩት እንቅስቃሴ ዓላማ ‹‹ተቋማዊ ለውጡን በመቃወም አድርጎ ማኅበረ ቅዱሳንን በማጋለጥ በመንግሥት ማስመታት፤ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ከሓላፊነታቸው ማስነሣት፣ አንድ ባራኪ ጳጳስ (አቡነ ሳዊሮስ?) ብቻ አስቀምጦ ሀ/ስብከቱን መቆጣጠር›› መኾኑን አስረድተዋል፡፡

ንቡረ እዱ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱበት የተነገረውና በፓትርያርኩ የስም ዝርዝር አቅራቢነት ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖ አቋቁሞታል የተባለው ‹‹የሊቃውንት ጉባኤ››÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ሰነድ ለመገምገም ያለው የሕግ ተቀባይነትና ሞያዊ አግባብነት የጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ካሳለፈው ውሳኔ አንጻር እየተጤነ ነው፡፡
በብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ሰብሳቢነት የሚመራውና ዘጠኝ አባላት አሉት በተባለው ‹‹ሊቃውንት ጉባኤ›› ተካተው የነበሩት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንና ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ‹‹ማኅበረ ቅዱሳኖች ናቸው›› በሚል እንዲወጡ ተደርጎ በምትካቸው እነአባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል መተካታቸው፣ በይቀጥላልም እነኃይሌ ኣብርሃ መላውን ገዳማትና አድባራት ሳያወያዩ መርጠናቸዋል ያሏቸውን ወኪሎች በሊቅነት ስም ለማስረግ መዘጋጀታቸው‹‹ሊቃውንት ጉባኤ›› የማቋቋሙን ዓላማና ቅንነት አጠያያቂ አድርጎታል፡፡

የጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ፣ የአደረጃጀትና አሠራር ሰነዱ ‹‹ወደታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም ዓይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል›› በመኾኑ፣ ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው 2700 የገዳማትና አድባራት ልኡካን የተወያዩበትና 96 በመቶ ድጋፋቸውን ያረጋገጠውን ጥናት በተሰበሰበው ግብዓት አጠናክሮ ለቋሚ ሲኖዶሱ በማቅረብ አጽድቆ የትግበራ ዕቅድ ወደሚወጣበት ምዕራፍ መግባት ብቻ ነው፡፡

የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለጥናቱ በሰጠው ይኹንታና የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት ጥናቱን እንዲተገብር የማድረግ ውክልና የተላለፈለት ቋሚ ሲኖዶስ በውሳኔው መሠረት የተጣለበትን ከፍ ያለ አደራ በመወጣት የእነንቡረ እድ ኤልያስን መሠሪ ዓላማ እንደሚያከሽፍና የቤተ ክህነታችንን ተቋማዊ ለውጥ ውጥን እውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

* * *
በይቅርታ ሥነ ሥርዐቱ ላይ መልአከ ገነት ኃይሌ ኣብርሃ (ፊት መልአከ መንክራት) በበርካታ ሚልዮን ብር ጉድለት ከሚጠየቁበት የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እልቅና መነሣታቸው አግባብ እንዳልነበር መናገራቸው ከስሕተታቸው ለመታረም እንዳልተዘጋጁ አመልካች ኾኗል፡፡ ከኦጋዴን እስከ አዲስ አበባ በአያሌ የምግባርና የሙስና ቅሌቶች የሚታወቁት ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ ሐዲስ ደግሞ የአዲስ አበባው አልበቃ ብሏቸው ድሬዳዋ ሀ/ስብከት ድረስ እየደወሉ ‹‹ተነሡ! ለውጡ ወደ እናንተም ሊመጣ ነው›› በሚል የአድባራት አለቆችንና የአስተዳደር ሠራተኞችን ለማነሣሣት እየሠሩ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡
ተቃዋሚ ነኝ ባይ ቡድኑ በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ላይ የተነሣው የ‹‹ዘወር አድርጓቸው›› ጥያቄ የማይወክለው መኾኑንና በአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ ላይ ግን ‹ተቃውሞውን› እንደሚቀጥል ቢያረጋግጥም በውስጡ ግን ጥያቄያቸውን ‹‹ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ውጭ ለመንግሥት ማቅረብ አለብን›› የሚል አቋም የሚያራምዱ፣ እንደ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ ያሉ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡

እነሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ ሐዲስንና መልአከ ገነት ኃይሌ ኣብርሃን ‹‹ጃኬት ለባሾች›› እያሉ የሚያጣጥሏቸውና እንደማይመጥኗቸው የሚናገሩት እነሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በቡድኑ ውስጥ መነኮሳት አስተዳዳሪዎች ባለመካተታቸው መከፋታቸውንና ከእናንተ ጋራ አልሳተፍም በሚል ሌላ አንጃ ለመፍጠር እየሞከሩ መኾኑም ተጠቁሟል – ‹‹ወደ መንግሥት የምትሰለፉ ከኾነ ንገሩኝ፤ እሔዳለኹ፡፡››

የሀ/ስብከቱን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ያካሔደውን የባለሞያ ቡድን (በእነርሱ አነጋገር የአንኮበርን ሥርዐት ለመመለስ የሚሠራውን ማኅበረ ቅዱሳንን) በትጥቅ በተደገፈ የኃይል ርምጃ በሀ/ስብከቱ ከተሰጠው ቢሮ አስለቅቃለኹ፤ ለዚኽም እስከ አፍንጫዬ ታጥቄአለኹ፤ ካስፈለገም በረሓውን ዐውቀዋለኹ እያለ ፓትርያርኩንና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ለማሸማቀቅ ሲሞክር የሰነበተው ተቃዋሚ ነኝ ባይ ቡድኑ በዋናነት አምስት ሙሰኛና ጎጠኛ የአድባራት አስተዳዳሪዎችየሚመሩት ነው፡፡
አስተዳዳሪዎቹን በመናጆነት የተባበሯቸውና በቁጥር ከ110 የማይበልጡት ተሰላፊዎችም ጥቂት ጸሐፊዎችና ሒሳብ ሹሞች በሥራ ዋስትናቸው ያስፈራሯቸው የጥበቃና ጽዳት ሠራተኞች፣ ሀ/ስብከቱ ያጸደቀውን የደመወዝ ጭማሪ አንከፍላችኹም እያሉ ያስገደዷቸው አገልጋዮች፣ በለመዱት የድለላ ሰንሰለት እናስቀጥራችኋለን እያሉ ተስፋ የሰጧቸው ሙዳየ ምጽዋት አዟሪዎችና ደጅ ጠኚዎች ብቻ መኾናቸው ተረጋግጧል፡፡

መነባንብ በአርቲስት ሽመልስ አበራ "ጆሮ ያለህ ስማ"