Friday 31 August 2012


ቤተ ክርስቲያንና የፓትርያርክ ምርጫ (ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ)

ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት መሆኗን ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ይቀበላሉ፤ በመሠረተ እምነታቸው ውስጥም አካትተው በጸሎትና በአስተምህሮ ይጠቀሙበታል፡፡የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ይህ ትምህርት ቢኖርም ነገር ግን መልእክቱን በአግባቡ ካለመረዳት የተነሣ እነ አርዮስና መቅዶንዮስ
በትውፊት ከሐዋርያት ጀምሮ የመጣውን የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መሠረት መቀበልን ቸል ብለው በራሳቸው መንገድ ሔደው ስለሳቱ በጉባኤ ኒቅያ በማያሻማ መንገድ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ቅድስት፣ ሐዋርያዊት እና ኩላዊት መሆኗን አስቀመጡ፡፡ በኋላ በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ደግሞ ሁላችንም እንድንጸልይበት በተዘጋጀው አንቀጸ ሃይማኖት ላይ (ጸሎተ ሃይማኖት) ‹‹ ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› የሚለው የጸሎታችን መፈጸሚያ እንዲሆን ተደነገገ፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት የሚቀበሉ ሁሉ የሚቀበሉትና የሚመሩበት መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት /doctrine/ሆነ፡፡

‹‹የጎንደር ምንቸት ውጣ … የትግሬ ምንቸት ግባ›› በቤተ ክህነት (ነመራ ዋቀዮ ቶላ )

ይህ የቤተ ክክነታችን ችግር እውነታን የዳሰሰ ጡመራ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ደጀ ሰላም ብሎግ አስነብባን ነበረ:: አሁንም በተለምዶ ስደተኛ ሲኖዶስ እየተባለ የሚጠራው ቡድን “መንበሩ ለእኔ ይገባኛል” እያለ ነው::ስደተኛው ሲኖዶስ የመሰረቱት በስደት ላይ ያሉት የጎንደር ተወላጅ የሆኑት ብፁዓን  አበው “በትግሬዎቹ/በወያኔ ተገፍተን መንበራችን ተቀማን” እያሉ ለ20 ዓመታት ያህል ምእመናን ሲያምሱ ኖረዋል:: በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቷ በፍቅር መስፋፋት ሲገባት በውጩ ዓለም በጥላቻ እና በጎጠኝነት ለቁጥር በሚያስቸግር ሁኔታ ተከፋፍላለች:: እውነት የጎደሬዎቹ ወደ መንበር መምጣት የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ይፈታ ይሆን??? አሐቲ ተዋሕዶ በአባቶች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል አጥብቃ ትቃወማለች:: ጎጠኝነትን ግን ታወግዛለች::  በስደት ላይ የሚገኙት ብፁዓን አባቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ታርቀው ወደ አገራችው እንዲመለሱም እንፈልጋለን:: የአባቶች መታረቅ የሚመጣው ግን እውነታዎች ሳይደባበቁ በግልጽ አውጥተው ሲነጋገሩ ብቻ ነው ብላ አሐቲ ተዋሕዶ ታምናለች:: የሚከተለውን የነመራ ዋቀዮ ቶላ ጽሑፍ አንብቡት:: መልካም ንባብ::

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተዘረጋባትን የተሐድሶ ወጥመድ ይፋ አድርጓል የተባለ “ሰነድ” ይፋ ሆነ

(ደጀ ሰላም፤ ፌብሩዋሪ 5/2011፤ ጥር 29/2003 ዓ.ም)፦ 

ከ1920ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እና ትውፊት በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እና መዋቅሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ የተሐድሶ ኑፋቄ ማኅበራት እና ድርጅቶች በተለዋዋጭ ስልቶች ሲማስኑ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ጥረታቸው ያሰቡትን ያህል ያልተራመደላቸው የተሐድሶ መናፍቃኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹ከውስጥ እያጠቁ ወደ ውጭ በመገስገስ እና ከውጭ ከበባውን አጠናክሮ ወደ ውስጥ በመግፋት›› ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አልያም ውጥንቅጧን አውጥቶ ለሁለት ለመክፈል ስልት ቀይሰው፣ በተለይም የቤተ ክርስቲያኒቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማእከል አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ስለመሆናቸው የሚገልጽ ሰነድ ሰሞኑን ለደጀ ሰላም ደርሷል፡፡