Wednesday 14 August 2013

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ?

ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)(የመጨረሻ ክፍል)
 
ታዲያ ሠለስቱ ደቂቅን ያወጣቸው ማን ነው?ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ 


መጀመሪውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ገብርኤል ነው አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ አማካሪዎቹንም፤ ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ ›› /ዳን 3 ፤ 24 -25/ ፡፡ በዚህ ገለጻ መሠረት አራተኛውን ያየው ንጉሡ ናቡከደነጾር ነው፡፡ እርሱም አየሁ ያለው አራተኛ ሰው ነው፡፡ የጨመረበት ቢኖር አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል የሚለውን ነው፡፡ ለመሆኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየ ? ሌሎቹ ለምን አላዩም ? አንደኛው የጥያቄው ቁልፍ ምስጢር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሣት የጣለው ራሱን ምስል አቁሞ ለምስሉ ሕዝቡን በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አምላክ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ የሚያየውን አራተኛውን  ሰው ‹‹ የእኛን ልጅ ይመስላል ወይም እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹ የአማልክትን ልጅ›› ይመስላል ያለበት ምስጢር ምንድን ነው ? ይህን ያለበት ምክንያቱ ያየው ነገር አራተኛው አካል ከህልውና ያለው በዘር በሩካቤ የተወለደ ሰው እነርሱ ሳያዩት እሳቱ ውስጥ ገብቶ ሳይሆን ነገሩ መገለጥ ስለሆነ ነው፡፡

ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ

ሰሞኑን በተለይ በርከት ባሉት በመጽሐፈ ገጽ ወዳጆቼ በኩል  ‹‹ ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው? ›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኛል፡፡ በተሐድሶዎች በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል ፤ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል ፤ በድርሳነ ራጉኤል ላይ ደግሞ ራጉኤል አዳናቸው ተብሎ ስለተገለጸ ትክክሉ የቱ ነው፤ በርግጥ ያዳናቸውስ ማን ነው የሚል ነው፡፡ በዚያም ጊዜ ሆነ ዛሬ ከአንዳንዶቹ መልእክት እንደተረዳሁት የድንጋጤ ስሜትም የተሰማቸው አሉ፡፡ ይህን ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችንም ስመለከት ለጉዳዩ ቢያንስ አንዲት ትንሽ መጣጥፍ እንዳአቅሜ  እንኳ ለጊዜው መስጠት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ጥያቄውን ለላካችሁልኝ ሁሉ ይህችን መቆያ እንካችሁ ብያለሁ፡፡ ዋናው ወይን ሁልጊዜም ወደ ኋላ መምጣቱ አይቀርምና እርሱን አብረን ከወይን አዳዩ እንጠብቃለን፡፡