Tuesday 15 April 2014

ከአንድ ፕሮቴስታንት እህታችን የደረሰን ጥያቄ

በአሸናፊ መንግስቱ

ኦርቶዶክሶች የዳናችሁት በክርስቶስ ሞት ሆኖ ሳለ በሞቱ ታዝናላቹ፤ ክርስቶስ ባይሰቃይ አትድኑም ነበር ስለዚህ በስቃዩ መደሰት ሲገባቸሁ ለምን ታዝናላቹ?

መልሱን በአጭሩ ለመመለስ ያህል :-በመዳናችን እንዲሁም በትንሣኤው እንጂ በሞቱ አንደሰትም! ለምን የሚለውን ለማወቅ ህሊና ብቻ ይበቃልና አንድ ቀለል ያለ ምሳሌ ሰጥተን እንመልከተው፡-


እጅግ በጣም ከሚወድህ ወዳጅህ ጋር አብረህ በመንገድ ላይ እየተጓዝህ ሳለ አድብቶ ይጠብቅህ የነበረ ጠላት መሳሪያ አውጥቶ ወዳንተ ይተኩሳል ልብ በል መሳሪያው የተተኮሰው ላንተ እንጂ ለወዳጅህ አይደለም መሳሪያው ካገኘህም ያለጥርጥር ትሞታለህ ነገርግን ወዳጅህ ካንተ ቀድሞ የመሳሪያውን መተኮስ አይቶ ነበርና ደረቱን ሰጥቶ ከፊትህ ቆመ መሳሪያውም ደረቱ ላይ አረፈችና ወዳጅህ ስላንተ ሞተ፤ አንተን አድኖ ሞተ፤ አሁን አንተ በህይወት ያለኸው ወዳጅህ ስለሞተልህ ነው፡፡

እናማ አሁን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ አንተ የምትደሰተው በወዳጅህ መሞት ነው ወይስ በመዳንህ? መቼም ወዳጄ ለኔ ሲል ሞቷልና ሞቱ ያስደስተኛል ካልክ አንተ ጠላቱ እንጂ ወዳጁ አይደለህም ከምንም በላይ ደግሞ ራስ ወዳድ መሆንህን ያሳያል፡፡ እኛ ግን በወዳጃችን ሞት እናዝናለን፤ በህይወት ስለመኖራችን ደግሞ እንደሰታለን፤ ወዳጃችን ስለኛ ስለተቀበለው ህመም፤ ስላቃሰተው ማቃሰትም በዘመናችን ሁሉ እያሰብነው እናዝናለን፤ በዚህም ወዳጃችን ለእኛ የከፈለውን ዋጋ ማወቃችን ይገለጻል::

አባቶቻችን እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ይበልጣል እንዲሉ ነገሩን ቀለል አድርጎ ለማሳየት እንጂ ይህ ምሣሌ በምንም አይነት የክርስቶስን የማዳን ጥበብ አይገልፅም፡፡

እንግዲህ ለሥጋዊ ወዳጃችን እንዲህ ካዘንን አንዳች ኃጢያት ሳይኖርበት ስለተንገላታው ስለክርስቶስ ስቃይ እንዴት አናዝን? የእርሱን ግርፋትና መንገላታት እያሰበ ስለማልቀስ ፋንታ የሚስቅስ እንዴት ያለ ኃጢያተኛ ነው? የእርሱን መቸንከር እያየ ያለኃጢያቱ የማይሞተው ሲሞት እየተመለከተ ስለማዘን ፈንታ የሚደሰትስ እንዴት ያለ ክርስቲያን ነው? በስቃይ የሚደሰትስ እንዴት ያለ ሰው ነው?

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መዳኛችን እንደሆነ እናምናለን ነገር ግን ስለመዳናችን እንደሰታለን እንጂ ስለስቃዩና ስለሞቱ ግን አብዝተን እናዝናለን ዳግም ደግሞ በትንሣኤው ታላቅ ሀሴትን እናደርጋለን፡፡

እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ!!!!

‹‹ሰሙነ ሕማማት››


በዲ/ን ህብረት የሺጥላ
‹‹ሰሙነ ሕማማት›› መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የምትጓዝ አካል አድርገው ሊገልጧት ይሞክራሉ፡፡ ይህ እጅግ አላዋቂ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገኘና በሥጋዊና በደማዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት የላትም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ‹‹ከሕማማቱ በኋላ›› በማለት ስለ ሰሙነ ሕማማት የሚያወሳ ቃል ተጠቅሟል፡፡ (የሐዋ1.3) ሰሙነ ሕማማት የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፡፡ ‹‹ሰሙን›› የሚለው ቃል ‹‹ሰመነ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ስምንት ቀኖች ወይም ሳምንት ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የሚለው ቃልም እንደዚሁ ‹‹ሐመመ›› ወይም ‹‹ሐመ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መከራዎች ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የምንለው ለብዙ ሲሆን ነው፡፡ ለአንድ ወይም ለነጠላ ሲሆን ደግሞ ‹‹ሕማም›› እንላለን፡፡ እንግዲህ ሁለቱን ቃላት በማናበብ ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ስንል ‹‹የመከራዎች ሳምንት›› ማለታችን ነው፡፡

በግብረ ሕማማት ውስጥ የሚነገሩ ባዕድ ቃላት