Monday 7 October 2013

ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?

FACT Weekily Magazine cover story


(ፋክት መጽሔት፤ ቅጽ 2 ቁጥር 14 መስከረም ፳፻፮ ዓ.ም.

ተመስገን ደሳለኝ

የኢሕአዴግ ታጋዮች የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር መቆጣጠር ችለዋል፤ ወደ አዲስ አበባም የሚያደርጉት ግሥጋሴም ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ሳይቀር ዕንቅልፍ ነስቷል፡፡ በአንዳች ተኣምር ግሥጋሴውን መግታት ካልቻሉ በጥቂት ወራት ውስጥ ሁሉም ነገር ታሪክ እንደሚኾን በማወቃቸው መላ በማፈላለጉ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር(የሐሳቡ አመንጪ ተለይቶ ባይታወቅም)፣ ‹‹ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አጭር ሥልጠና ሰጥቶ ከሀገሪቱ ሠራዊት ጎን ማሰለፍና የ‹ወንበዴውን ጦር› መድረሻ ማሳጣት›› የሚለው ሐሳብ እንደ መፍትሔ የተወሰደው፡፡

እናም መንግሥቱ ራሳቸው ተማሪዎቹን በዩኒቨርስቲ አዳራሽ ሰብስበው እንዲህ ሲሉ አፋጠጧቸው፡- ‹‹እነርሱ (ኢሕአዴግና ሻዕቢያን ማለታቸው ነው) ለእኵይ ዓላማቸው ከእረኛ እስከ ምሁር ሲያሰልፉ እናንተ ምንድን ነው የምትሠሩት? በሰላማዊ ሰልፍና በስብሰባ ብቻ መቃወም ወይስ ወንበዴዎቹ እንዳደረጉት ከአብዮታዊ ሠራዊታችነ ጎን ቆማችኹ የአገሪቱን ህልውና ታስከብራላችኹ?››

ይህን ጊዜም አስቀድሞ በተሰጣቸው መመሪያ ከተማሪው ጋራ ተመሳስለው በአዳራሹ የተገኙት የደኅንነት ሠራተኞችና የኢሠፓ ካድሬዎች ‹‹ዘምተን ከጠላት ጋራ መፋለም እንፈልጋለን›› ብለው በስሜትና በወኔ እየተናገሩ በሠሩት ‹ድራማ› ተማሪው ትምህርት አቋርጦ እንዲዘምት ተወሰነ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተዘጋ፤ ተማሪዎቹም ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው የብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛከተቱ፡፡

ከመላው ዘማቾች [የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የኾኑ ሠልጣኞች በማሠልጠኛው ባዶ ድንኳን] በየጊዜው እየተሰበሰቡና በመጨረሻም ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ከመዐቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በጸሎት መማጠን የሕይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት. ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው የሠየሙትን የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡ . . . ይኹንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም በፓዌ መተከል ዞን የተደረገውን የመልሶ ማቋቋም ሠፈራ ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የጽዋ ማኅበራት ጋራ በመዋሐድ የዛሬውን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የኾነው ግን እንዲያ ነበር፡፡