Wednesday 22 August 2012

Tewodros Yosef Mariam mariam biye

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓሮቴስታንታዊ መሪ አስተናገደች

ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መቼም የማይነጣጠሉ ነበር ዛሬ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያናችን ተሰሚነቷ እየቀነስ አመራሩ አካል ጫና እያሳደረባት እና ቤተ ክርስቲያኗ እንኳን ሲቃጠሉ ሀይ ባይ እያጣች መጥቶ ዛሬ ደግሞ ይህ አልበቃ ብሎ ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክስ ተፋተው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ መሪ ለማስተናገድ በቃች፡፡

መቼም ሁላችሁም እንደምትገምቱት ሐይለማርያም ብሎ ፓሮቴስታንት አይኖርም አይደረግም ብላችሁ ተገምቱ ይሆናል ነገር ግን በደቡቡ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንሰራፍ ያለው የፕሮቴስታንት እምነት ወደድንም ጠላንም አሁን መሪ የተባሉትን ጠቅላይ ሚንስቴር ሀይለ ማርያም ደሳለኝን ሳይቀር  ሰለባ አድርጓቸዋል፡፡ ወላይታና አካባቢውም ቢሆን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተኩረት ባለመስጠቷ ብዙዎቹ ካደጉባት ቤተ ክርስቲያን   አስተምህሮዋን ባለመረዳት ኮብልለዋል፡፡ እግዚአብሔር ወደ እናት ቤታቸው እስኪመልስልን ልንፀልይ ይገባልእኛ የምንሰራቸው የቤተ ክርስቲያናችን ስራዎች ግን በዝተዋል ፡፡


የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አስከሬን ሽኝት


  • ግርግሩ መልክ ይያዝ::
  • ሥርዐተ ቀብሩ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ይተላለፋል::
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 16/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 22/ 2012/READ THIS NEWS IN PDF)፦  የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አስከሬን፣ ተጠብቆ ከቆየበት ሃያት ሆስፒታል ዛሬ፣ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም፣ 5፡00 ላይ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ደርሷል፡፡

በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎችና መላው ሠራተኞች፣ የየድርጅትና የየኮሌጁ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ አገልጋዮችና ምእመናን ታጅቦ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ከገባ በኋላ በቅድስቱ ውስጥ ዐርፎ ጸሎተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ማቲያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከንጋቱ 12፡00 ላይ በመላው ኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት የደወል ድምፅ ተሰምቷል፡፡

በወጣው መርሐ ግብር መሠረት የቅዳሴው ሥነ ሥርዐት እንዳበቃ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አስከሬን በልዩ ሠረገላ ኾኖ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሚኒስትሮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ በፖሊስ ሠራዊት ባንድ፣ በምእመናንና ምእመናት ታጅቦ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዞ የፖሊስ ሠራዊት ግራና ቀኝ በሰልፍ አስከሬኑን ያጅባል፡፡ የቅዱስነታቸው አስከሬን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዳረፈ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ይዘጋል፡፡ ረቡዕ ለኀሙስ አጥቢያ ከምሽቱ 2፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ሙሉ ጸሎተ ማሕሌቱ ሲከናወን ያድራል፡፡

በዛሬው የመርሐ ግብሩ ክንውን ሐዘንን ከመግለጽ ባሻገር በተለይም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን አስከሬን ይዞ ለማስገባት ከተመደቡት አባቶች ውጭ በአንዳንድ መነኰሳት ዘንድ የታየው ከፍተኛ ግርግር ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ነው፤ በቀጣይ የሥርዐተ ቀብሩ ሂደት ቢያንስ ከሚገኙት እንግዶችና በቴሌቪዥን ከሚሰጠው የቀጥታ ሥርጭት አንጻር ፈር መያዝና መስተካከል እንደሚገባው አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡

እስከ አሁን በሥነ ሥርዐቱ ላይ የቅብጥ፣ የሶርያ፣ የአርመንና ሕንድ /ማላባር/ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ልኡካን እንዲሁም የግሪክ ኦርቶዶክስ ተወካዮችና የመሳሰሉት እንግዶች እንደሚገኙ ማረጋገጣቸው ተገልጧል፡፡
ቀሪውን የቀብር ሥነ ሥርዐት ክንውን ከመርሐ ግብሩ ይመልከቱ፡፡

የቅዱስነታቸውን ነፍስ በአብርሃም ዕቅፍ ያኑርልን
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡


የአቡነ ጳውሎስ የቀብር ስርዓት እና የመለስ ዜናዊ አስከሬን አቀባበል



  • የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬናቸው ቢያንስ ለአንድ ሳምንት በብሔራዊ ቤተመንግስት ይቆያል ፤ ህዝቡም በቦታው በመገኝት ይሰናበታቸዋል ተብሎ ይጠበቃል

(አንድ አድርገን ነሐሴ 16 ፤ 2004 ዓ.ም) ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አስከሬን ከባልቻ ሆስፒታው ወደ ሐያት ጠቅላላ ሆስፒታል መሸጋገሩ ይታወቃል ፤ ቀድሞ የታሰበው ብጹእነታቸው አስከሬን ረቡዕ ከሰዓት ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ከተወሰደ በኋላ ጸሎት ተደርጎለት ከመንበረ ፓትርያርክ ወጥቶ ወደ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን በሰረገላ በመውሰድ ለሊቱን ሙሉ ጸሎት በማድረግ ጠዋት ቅዳሴ በማድረግ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ግድም ወደ ውጭ አውጥቶ ስርዓቱን ለማከናወን ታስቦ ነበር ፤ ነገር ግን አሁን በደረሰን መረጃ የብጹእነታቸው አስከሬን ዛሬ ጠዋት 3 ሰዓት ከሐያት ሆስፒታል ወደ መንበረ ፓትርያርክ በመውሰድ የከሰዓት በኋላ ቅዳሴውን በማድረግ አመሻሹ ላይ ወደ ቅድስት ስላሴ እንደሚሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በነገው እለት የቀብር ስነስርዓታቸው እንደሚፈጸም ይታወቃል ፤ 


ከዚህ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ  ሞት ብዙዎችን አሳዝኗል ፤አቶ መለስ ግንቦት ልደታ 1947 ዓ.ም እንደተወለዱ የህይወት ታሪካቸው ይናገራል ፤ በ57 ዓመታቸው  ነሐሴ 15 2004 ዓ.ም ቀን የሱባኤው ቀናት ሊጠናቀቅ አንድ ቀን ሲቀረው ከዚህ ዓለም በህይወት ተለይተዋል ፤ በትላንትናው እለት ማታ 4 ሰዓት አስከሬናቸው ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሰበት ጊዜ የመንግስት ባለስልጣናት ፤ ቤተሰቦቻቸው ፤ ከየክፍለ ከተማው በቅጥቅጥ አይሱዙ ተጭነው የመጡ ሰዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል ፤ አስከሬናቸው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በመልበስ ከአውሮፕላን ወርዷል ፤ ኢትዮጵያ ቴሊቪዥን በቦሌ አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ እና በቦሌ መድኃኔአለም ቤተክርስትያን ጊዜያዊ ስቱዲዮ በማዘጋጀት ስርዓቱን በቀጥታ ማተላለፍ ችሏል ፤ 

ስርዓቱን ግማሹን በቴሌቪዥንም  ቀሪውን በአካልም ስርዓቱን መታደም ችለን ነበር ፤ አስከሬናቸውን የክብር ልብስ በለበሱ 8 አባላት በማስሳ ወደተዘጋጀለት ቦታ ማስቀመጥ ችለዋል ፤ ዘወትር እጃቸውን ወደ ላይ በማንሳት ከውሮፕላን ሲወርዱ የምናቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዛሬ እለተ ቀናቸው ደርሶ ፤ የእግዚአብሔር ጥሪ ሆኖ በሳጥን አስከሬናቸው ከአውሮፕላን ላይ ወርዷል ፤ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ይመስለናል ፤ ህዝቡ መሪ አስታሞም ሆነ መሪ ሲሞት ቀብሮ አያውቅም ፤ ቴዎድሮስ ለጠላት እጅ ላለመስጠት ራሳቸውን በአንዲት ጥይት አጠፉ ፤ አጼ ዮሀንስ በደርቡሽ ተገደሉ ፤ እምዬ ሚኒሊክ አስከሬናቸው 4 ዓመት ሀገሪቱን ገዛ ፤ ይህ የሆነው ሀገሪቱ ውስጥ ችግር ይፈጠራል በማለት ነበር ፤ አጼ ኃይለስላሴ በደርግ አመራሮች በትራስ ታፍነው እዛው ቤተመንግስት ተቀብረው ከዘመናት በኋላ ሬሳቸው በማውጣት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን እንዲያርፉ ተደረጉ ፤ ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያር የዚችን ሀገር መጨረሻ አሳየኝ ብሎ የጸለየ ይመስል ከስልጣን ከወረደ በኋላ ይህው 21 ዓመት በዚምባብዌ ሰላማዊ ህይወቱን እያሳለፈ ይገኛል ፤ አራት ኪሎ ቤተመንግስቱን ለአቶ መለስ ቦታውን ለቆ እሱ በህይወት እያለ የእሳቸው ሞት ቀደመ ፤ ስለዚህ አሁን ላይ አቶ መለስ ዜናው ስልጣኑን እንደያዙ ከአሁን አሁን ስልጣኔን አስረክባለሁ እያሉ መልአከ ሞት ቀድማቸው ፤ ህዝባችን መሪ ሞቶ ቀብሮ አያውቅም ፤ ኢቲቪም መሪ ሞቶ ምን አይነት የሀዘን ካሴቶችን መክፈት ስለማያውቅ ትላንትና እስከ 2 ሰዓት ድረስ በፒያኖ በጃዝ እና በጊታር የተሰራ የቆዩ ክላሲካሎችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል ፡፡


የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን በመከላከያ ባንድ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ጥቁር መኪና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የለበሰች መኪና ውስጥ ተከቷል ፤ ለዚች ሀገር ለዛውም በአሁኑ ሰዓት መሪ ማጣት እጅጉን ያሳዝናል ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “እንወድሀለን” ፤ “እናከብርሀለን” ፤ “ታላቁ መሪያችን” ፤ “አባይ ይገደባል መለስ ይታወሳል” ፤ “አፍሪካ ታላቅ መሪዋን አጣች” የሚል መፈክር ይዘው በመንገድ ዳር ታይተዋል ፤ ዝናቡን በመቻል ሳይታክቱ ከ1 ሰዓት አንስተው አስከ 5 ሰዓት ድረስ አስከሬኑን ጠብቀውታል ፤ ከከተማዋ መብራቶች በተጨማሪ ብዙዎች ጧፍ በማብራት ተስተውለዋል ፤ የጧፍ ሽያጭ ባልታሰበ ሰዓት እጅጉን ደርቷል ፤ አንዳንድ ሰዎችም አስከሬኑ እስኪመጣ የእንግሊዝን ፕሪምየር ሊግ የሚቃኙ አልጠፉም ፤ በቅርቡ ከአርሰናል ወደ ማንችስተር ስለተዘዋወረው ተጨዋች የደራ ክርክርም ይዘው ነበር ፤ ኡራኤል አካባቢ ያለው ሰው በማታ እጅግ ብዙ ነበር ፤ ፌደራል ፖሊስ ከቦሌ አንስቶ እስከ መድረሻው ብሔራዊ ቤተመንግስት ድረስ እጅጉን በዝተው ሰላም የማስጠበቅ ስራ ላይ ተሰማርተዋል ፤ ወደፊት እጣ ክፍሉ ያልታወቀው በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን የቆመውን የአቡነ ጳውሎስን ሀውልት ደግሞ ደጋግሞ ቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ተመልክተናል፡፡


በቴሌቪዥን አንዲት እናት “ለማነው አደራው?” እያሉ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል ፤ ትክክል ናቸው አደራ የሚቀበል ሰው ያስፈልጋል ፤ እኛ ለምዶብን ቅብብሎሽ ስላለመድን እኛው ጀምረን እኛው ሁሉን የምንጨርስ ይመስለናል ፤ ነገር ግን ሀገርን በቅብብሎሽ ነው የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ የምንችለው ፤ አባቶቻችን ሀገሪቷን ነጻነቷን አስጠብቀው ለእኛ አስረክበውናል ፤ እኛም የራሳችንን ስራ በመስራት ለልጆቻችን ማስተላለፍ ነው ስራችን ፤ በእኛ ዘመን ጀማሪ እንጂ ፈጻሚ አለመሆናችንን ማወቅ መቻል አለብን ፤  የሀገራችን መሪዎች ትልቁ ችግራቸው መሪ ማፍራት አልፈጠረባቸውም ፤ ወንበሩ ዘላለማዊ ይመስል ሞታቸውን አስበው በተመረጡበት ጊዜያት አያገለግሉም ፤ አሁን ህዝቡን ያሳሰበው ነገር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ሞት በተጨማሪ የእሳቸውን ቦታ ማን ሊይዝ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ነው ፤ በ21 ዓመታት ከእሳቸው ጎን ለጎን የሚሰሩትን ተመልክቶ የሚተካቸው ሰው አልተመለከትንም ፤ በመሰረቱ መሪ እና ስልጣን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ፤ አሁንም ለሐገራችን ጥሩ አመለካከት ያለው ፤ ጎጠኝነት ያላጠቃው ፤ ዘረኝነት ያልደረሰበት ፤ የተማረና በእውቀት የዘመነ ፤ ከግለሰብ አንስቶ የህዝብን መብት የሚያስጠብቅ ፤ ህዝብን የሚያከብር ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ፤ ሞቱን አስቦ የሚያገለግል ፤ አሁን ያለውን ጭላንጭል ወደ ትልቅ ብርሐን የሚለውጥ አስተዋይና ቅን መሪ ይስጠን እንላለን ፤ በተለይ ለቤተክርስትያናችን ደግሞ  በእግዚአብሔር የተመረጠ ፓትርያርክ ያድላት ፡፡ 


ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል።”ትንቢተ ዳንኤል 4፤26በአሁኑ ሰዓት በተለያየ የቤተክርስትያን እና የመንግስት የስልጣን ቦታ ላይ የምትገኙ ሰዎች የያዛችሁትን ስልጣን ከላይ እንደሆነ አውቃችሁ እና አምናችሁ በቅን ልቦና ልታገለግሉ ይገባችኋል ፤ በራሳችን መንገድ ተንጠላጥለን ያለ እግዚአብሔር መልካም ፍቃድ የምንቀመጥበት ስልጣን የለም ፤ በተቻለን መጠን ለራሳችን ለእምነታችን ለተሰጠን ኃላፊነት ቦታ ታማኝ ሆነን ማገልገል መቻል አለብን ፤ “ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤” ወደ ሮሜ ሰዎች 13፤1 ስልጣን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ፤ የሚነሳም እሱ ነው ፤ እርሱ ከእርሱ ካልሆነ ስልጣን የለም ፤ የሰለሞንም የዘውድ ስርዓት አልፏል ፤ ሞት ትምህርት ሊሆነን ይገባል ፤ ሰው ነን እንወለዳለን እንኖራለን በመጨረሻም እንሞታለን ፤ ይህን አስበን በንስሀ ህይወት እየተመላለስን ልንኖር ያስፈልጋል ፤ 2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታላላቅ ጸሀፍትን ፤ አለማቀፋዊ እውቅና ያለው ሰዓሊን ፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶን ፓትርያርክ ፤ አሁን ደግሞ የሀገሪቱን ስመ ጥር መሪ መለስ ዜናዊን ያጣችበት ዘመን ነው ፤ አሁንም እግዚአብሔር በቃችሁ እንዲለን ልንጸልይ ያስፈልጋል ፤ ቤተክርስትያን ስለ ሀገር ሰላም እንድትሆን ፤  መሪዎችን ማስተዋልና ጥበብን እንዲሰጣቸው ፤ ስለ ህዝበ ክርስትያን  ፤ ዘወትር በቅዳሴ ላይ ጸሎት ታደርጋለች ፤ እኛም እስኪ ሱባኤው በእንዲህ አይነት ሁኔታ አልፏል ፤ ቀሪዎቹን የአዲስ ዘመን መቀበያ ቀናት ሌላ እንዳይጨምርብን ተግተን እንጸልይ ፤   

ስለ ቤተክርስቲያን ጸልዩ
ስለ ሀገር ሰላም ጸልዩ
ስለ ህዝበ ክርስቲያን ጸልዩ
ለሁላችን እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጠን

የአቡነ ጳውሎስ አስከሬን እንደ አቡነ ሺኖዳ በመስታወት ሬሳ ሳጥን ቤተክህነት ደርሷል


ከአንድ አድርገን ድህረ ገጽ ላይ የተወሰደ
Photographer:- LAMBDA



























አቡነ ዮሀንስ ከዚሀ ዓለም በሞት ተለዩ ፤



አቡነ ዮሀንስ የከሳቴ ብርሀን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ መሆናቸው ይታወቃል
  • ስለ ቤተክርስትያን ጸልዩ
  • ስለ ህዝበ ክርስትያን ጸልዩ
  • ስለ ሀገር ሰለም ጸልዩ

አሁንስ ፈራን!!! 


ይህን ጊዜ ያሳልፍልን ፤ ይህንም ዓመተ ምህረት በሰላም ያሻግረን