Monday 16 December 2013

እውን ‹‹ተሐድሶ›› የለምን?

በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ

ሰሞኑን በተደጋጋሚ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው ወሬ ነው!›› የሚል ንግግር በመስማቴ ይህንን አጭር ማሳሰቢያ ለመጻፍ ተነሳሣው፡፡ በእርግጥ ንግግሩን ቀደም ሲልም ሰምቼው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን መደጋገሙ ሲበዛ በተለይም ግምት የሰጠዋቸው ሰዎች ነገሩን ተቀብለዉት ስመለከት ለካ የሚናቅ ሐሰት የለም አሰኘኝ!

‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው ወሬ ነው!›› ለሚለው ለምን ፈጠረው? ይህን ሐሳብ ፈጥሮ ምን ይጠቀማል? ቢፈጥረውስ እናንተ ተሐድሶ ካልሆናችሁ ምናችሁ ይነካል? የሚል የራሴን ጥያቄ ፈጥሮ ከመጠየቅ በቀር እኔን ስለማይመለከተኝ የማኅበሩ የቤት ሥራ ነውና ራሱ ይጨነቅበት ብዬ አልፌዋለሁ፡፡ ትንሽ ማብራሪያ ለመስጠት የምሞክረው ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም›› በሚለው አመለካከት ላይ ነው፡፡

በእርግጥ አንድን ነገር እያለ ‹‹የለም›› ማለት አንድም ሐሰት ዳግመኛም የጥፋት ስልት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአጥፊዎች ሁሉ አውራ የሆነ ሰይጣንም ይህን ስልት በተለያየ መንገድ ሲጠቀምበት ይታያል፡፡ ሰይጣን በሰዎች ልቡና ያድርና ራሱን ደብቆ ክፉ ሥራ ሲያሠራቸው ይኖራል፡፡ በወንጌል እንደተነገረው በጾም፣ በጸሎትና በመንፈሳዊ ሥራ እንዲሁም በተቀደሰ ውሃና አፈር (በጸበል) ኃይሉ ሲደክምበት ‹‹ተቃጠልኩ›› እያለ ይለፈልፋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣን መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን መንፈሳዊ ሥርዓት በማከናወን ያንን ሰው ለቆ እንዲወጣ ይገሠጻል፤ ይረገማል፤ ይገዘታል፡፡ ወዲያውም ለቆ ይሄዳል፡፡

ክርስቲያኖች ይህን የሰይጣን ክፋትና አሠራር ያውቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር መኖር የማያምኑ ከሃዲዎች በሰይጣን መኖርም አያምኑም፡፡ ሰይጣን እነዚህን ሰዎች እኔ ‹‹የለውም›› እያለ ይዘብትባቸዋል፤ ይዋሻቸዋል፡፡ እነርሱም በጸበል ሲለፈልፍ አይተው በሥራህ ተገለጥክ፤ አወቅንብህ እንዳይሉት እንኳን ይህ እኮ ጭንቀት ነው፤ ቅዠት ነው፤ ኢሉዥን ነው /illusion/፤ ኮንፍዩዥን ነው /Confusion/ ወዘተ እያለ ምክንያት በመደርደር አለመኖሩን ሊያሳምናቸው ይጥራል፡፡ በዚህም ሐሳቡን የተቀበሉት በርካቶች ናቸው፡፡ ይገርማል! ሥራው እየታየ፤ ንግግሩ እየተሰማ የለውም ማለቱ አቤት የሰይጣን ድርቅና!

የተሐድሶ አራማጆች ሥራ ዓይኑን አፍጥቶ ጥርሱን አግጥጦ በሚታይበት በዚህ ዘመን ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የፈጠራ ወሬ ነው እንጂ በእውን ያለ ነገር አይደለም›› ማለት አንድም አይኔን ግንባር ያድርገው ከማለት ይቆጠራል፡፡ ወይም ደግሞ ከላይ በምሳሌ እንደተጠቀሰው አቅጣጫ የማስቀየር የቅሰጣ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ሌላው ቢቀር ፊደል የለየና ማንበብ የሚችል ሰው ከአንድ አሥር ዓመት ወዲህ የወጡትን በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳዮች የተጻፉትን የሕትመት ውጤቶች ከሁሉም አቅጣጫ ቢከታተል ‹‹ተሐድሶ›› በቀናች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማ ቀኖና እና ትውፊት ላይ ያነጣጠረ በጥናት የተቀነባበረ የጥፋት ስልት እንጂ ጭራቅን የመሰለ የፈጠራ ወሬ አለመሆኑን በቀላሉ ይረዳል፡፡

‹‹ተሐድሶዎች›› ራሳቸው የቁርጥ ቀን መድረሱን እያወጁ ወደ አደባባይ ሲመች በቃልና በጽሑፍ ሳይመች ደግሞ በጉልበት ጭምር እየተጋፉ ለመውጣት በሚሽቀዳደሙበት በዚህ ጊዜ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር›› የለም ማለት ከ‹‹ተሐድሶነት›› የከፋ የሐሰት ምስክርነት ነው፡፡

በአገራችን የከተማና የገጠር ጎዳናዎች ላይ ሲመላለስ ‹‹…የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን›› የሚል ጽሑፍ እያነበበ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም›› የሚል ሰው ምን ሊባል ይችላል? የማያውቅ ሰው የዚህኛው ከዛኛው ልዩነቱ ምንድር ነው? አንድ ናቸውን? እያለ ይጠይቃል እንጂ በማያውቀው ነገር ደፍሮ ምስክርነት አይሰጥም፡፡ በዛሬ ጊዜ ‹‹ተሐድሶአዊ እንቅስቃሴ የለም›› ማለት በሚቃጠል ቤት ውስጥ ጭስ አፍኖት እየሳለ በር ዘግቶ እንደመቀመጥ ይቆጠራል፡፡

ዛፍ በፍሬው እንደሚታወቅ ‹‹የተሐድሶ እንቅስቃሴም›› መገለጫዎች አሉት፡፡ እነዚያን እየመረመሩ ‹‹እንግድዳ ትምህርት›› (ዕብ13.9) ሲያገኙ መለየት እንጂ ‹‹ተሐድሶ የት አለ?›› ‹‹ተሐድሶዎቹስ እነማን ናቸው?›› የሚል ዓይነት ያልበሰለ አጠያየቅ ከእውነታው እንድንርቅ ሊያደርገን ይችላል፡፡

በየመንፈሳዊ መድረኮች ላይ ሁለት ዓይነት ልሣን ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል፡፡ የቱ ‹‹እንግዳ ትምህርት›› እንደሆነ የእረኛቸውን ድምፅ የሚሰሙ እውነተኛ በጎች ለይተው ያውቁታል፡፡ የሴት ድምፅ ከወንድ እንደሚለይ ልዩነቱ ጉልህ ነውና፡፡ ዕረፍት የማይሰጡ፤ የቃላት ድርደራዎችና ጩኽቶች ከማሳመን እና ጥያቄን ከመመለስ ይልቅ ሌላ ጥያቄ የሚያጭሩ፣ የሚያጠራጥሩና የሚያስጨንቁ ስብከቶችና ‹‹መዝሙሮች›› የምን ነጸብራቅ ናቸው? ከአንድ የተሰወረ ምንጭ ካልቀዱትስ በቀር ብዙ ሰዎች አንድ ዓይነት ዘይቤ፣ ቃላት፣ ድምፅና እንቅስቃሴ ሊኖራቸው እንዴት ይችላል? በዚሁም ላይ ይህ ሁሉ ደግሞ ከመናፍቃኑ ጋር አንድ መሆኑ ምን ይጠቁማል?

‹‹ከተሐድሶ›› ስልቶች አንዱ በስውር መንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ በጥናትና በዓላማ የሚተገበር በመሆኑ በማስተዋል ካልሆነ በፍጥነት ለመለየት ያስቸግር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን ተክል ምንነት ለይቶ ለማወቅ ቅጠሉንና ፍሬውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለዚህም ገበሬ መሆን አይጠይቅም፡፡ ይህ ኮክ ነው፤ ይህ ወይን ነው፤ ይህ በለስ ነው! ለማለት ቆፍሮ ሥሩን የሚያይ የለም፡፡ ሥሩ በምክንያት ከመሬት ውስጥ መቀበሩ ይታወቃልና፡፡ ሥሩ ምንም ይሁን ምን የተክሉን ዓይነት ለይቶ ለማወቅ ቅጠሉንና ፍሬውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ እንደዚሁም የ‹‹ተሐድሶ እንቅስቃሴ›› መራራ ፍሬው በስሎ አዝመራውም ነጥቶ እየታየ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል! ‹‹ተሐድሶ የሚባል የለም›› እያሉ ስለማያውቁት ነገር ምስክርነት ከመስጠት፤ ለጥፋትም ሥራ ተባባሪ ከመሆን፤ ራስንና ሌሎችንም ከመጉዳት የሚቀድመው አፍን መሰብሰብና ራስን መመርመር ነው፡፡ ‹‹የተሐድሶ›› ሴራ ስውር እንደመሆኑ መጠን የዚህ የጨለማ ሥራ ሰለባ ከሆኑና ያላመኑበት ጉዳይ ከሆነ ይህንንም እውነት ዘግይተው ከተረዱ የሚሻለው ቶሎ መመለስ ነው፡፡ ‹‹ተሐድሶ የሚባል የለም›› ማለት ራስን የሚያድን መንገድ ስላልሆነ ከወዲሁ ንስሐ መግባት ይገባል፡፡ እንዲያውም ሌሎች እንዳይጠፉ መረጃ መስጠትና ካገኙት ልምድ በማካፈል አካሄድን ማሳመር እንጂ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ዓይነቱ ድርቅና የሚበጅ አይሆንም፡፡ ነቢዩ እንደተናገረ ‹‹ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉና›› (1ሳሙ2.10)

ስንዴ ከእንክርዳድ ጋር በመመሳሰሉ እንደ አረም ተቆጥሮ አብሮ ቢነቀል እህል ስለሆነ ግዕዛን የለውምና አይፈረድበትም፡፡ ማለትም ማን ከእንክርዳድ ጋር ተሰለፍ አለህ? አይባልም፡፡ ክርስቲያን ግን ከመናፍቃን ጋር ቢሰለፍና አብሮ ቢቆጠር ራሱን አልለየምና ወቀሳ አይቀርለትም የሚገባው ነውና፡፡ ከክፉዎች ጋር አብሮ እንዳይፈረድበት የፈለገ እንደሎጥ ተለይቶ መውጣት ይገባዋል፡፡

በነገራችን ላይ ‹‹ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም›› የሚለውን ሐሳብ ይዞ ሙጭጭ ማለት ምእመናንን እንዳይነቁ የማደናገሪያና የማዳከሚያ ስልት ካልሆነ በቀር ለምን ይጠቅማል? እንኳን ኖሮ ባይኖር እንኳን የሰባኪና የካህን ድርሻው እንዲህ ያለ ፈተና ሊከሠት ወይም ሊኖር ይችላልና ተጠንቀቁ እያሉ ምእመናንን ማንቃት እንጂ ‹‹ምንም የሚመጣ ችግር የለም›› እያሉ ማስነፍ አይደለም፡፡ ስለዚህ በገሃድ የሚታየውን እንቅስቃሴ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ አይደለም፡፡

‹‹ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ›› ዕብ13.9

ይቆየን!



በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
hibretyes@yahoo.com

3 comments:

  1. ቃለ ሂወት ያሰማልን መምህር! ከዉጭ የሚገኙ ሁለት እህቶቸ አስተሳሰባቸዉ ከ ፕሮቴስታንት አይለይም! ታህድሶ የሚባል የለም ከሚሉ ወገኖች መሆናቸዉ ሁሌም ይደንቀኝ ነበር!

    ReplyDelete
  2. እኔ መጠየቅ እምፈልገው ዝም ብሎ አንድን አገልጋይ ያለ ማስረጃ ተሀድሶ ነህ ማለት ግን ጥሩ አይደለም
    እንደውም በጣም የሚገርመኝ ስብከቱ ውስጥ ከተጠቀመባቸው ምሳሌወች ውስጥ ማንሳት ተሀድሶ ነው ለማለት
    አያስደፍርም ምክንያቱም ምሳሌ ሰወች እንዲረዱ ነገርን ቀለል አድርጎ ማቅረቢያ መንገድ ስለሆነ፡፡ ሌላው በእርግጥ ተሀድሶ ነው
    እሚባል አገልጋይ ካለ በትክክለኛ ማስረጃ ማቅረብ እና ማስረዳት አንጂ የግል ጸብን ሽፋን ማድረግ ጥሩ አይመስለኝም ምክንያቱም አምነት የብዙሀኑ ስለሆነ፡፡
    እኔ በአገኘሁአቸው አጋጣሚ እውነት እነእንተና ተሀድሶ ናቸው ብየ ብዙ ሰው ጠየኩኝ ግነ ሁሉም ሠምቼ ነው ነው እሚለው እና እባካችሁ እውነት ከሆነ በቤተክርስትያን ደረጃ ይነገረን ካልሆነ ደግሞ ግራ አታጋቡን፡፡
    እውነተኛ ክርስትያን ደሞ እሚተጋው የጠፉት እንዲመለሱ፤ ያሉት እንዲጸኑ በፆም በፀሎት ፤በስብከት ፤…..ነው እንጂ በማባረር በመደባደብ በመሳደብ አይደለም፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. TTT በእርግጥ አንድን ግለሰብ ወይም የግለሰቦችን ስብስብ ተሃድሶ ነው ለማለት በቂ መረጃ በመያዝ መነጋገርን የመሰለ መልካም ነገር የለም። ነገር ግን የተሃድሶ ርዕሰ ጉዳይ መነጋገሪችን መሆን ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በተለያዩ መንገዶች የተበተኑትን መረጃዎች የተመለከቱ አይመስለኝም። እንደውም በዚህ ርእሰ ጉዳይ ለመውቀስ ሲነሱ ብዙ ሰዎችን ጠይቀው መልስ ስላጡ እንደሆነ ነግረውናል።
      በእርግጥ እርስዎ የጠየቋቸው ግለሰቦች እነማን እንደሆኑና በርእሰ ጉዳዩም ላይ ምን ያክል እውቀት እንዳላቸው አላሳወቁንም። ይህን ያልኩበት ዋነኛ ምክንያቴ ቀድሞውንም ብዙ የቤተክርስቲያናችን ምእመናን እና አባቶች እንዲሁም አገልጋዮች በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀት ስለሚጎድላቸው ነው የቤተክርስቲያናችን መነጋገሪያ ርእስ እስከመሆን የደረሰውም። አብዛኞቻችን ምንነቱን ብናውቀው ኑሮማ ችግራችንም መሆን አይችልም ነበር። ሳይቃጠል በቅጠል ብለን እናጠፋው ነበር ቀድመን።
      ሌላው በተለያየ ወቅት የተበተኑ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማድመጥ እንዲሁም በመመልከት በራስዎ መንገድ ለመገምገም ይሞክሩ። ቀጥሎም ከቤተክርስቲያል ልጆች ጋር ይወያዩበት። በተለይም ተሃድሶ አለ የለም ከሚሉ ግለሰቦች ጋር። ያኔ ነገሮች በደንብ ይጠራሉ ብዬ አስባለሁ። ያለበለዚያ ሰዎችን ጠይቄ መልስ አላገኘሁም ማለት በቂ አደለም። መልስ ቢያገኙም እውቀትዎ በአሉባልታ ላይ የተመሰረተ ሰለሚሆን ጥንካሬ አይኖረውም።
      ቸር እንሰንብት።

      Delete