Saturday 19 April 2014

ትንሣኤ ዘክርስቶስ - የክርስቶስ ትንሳኤ

ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
እንዴት ተነሣ?
ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
መቃብሩን ማን ከፈተው?

(መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው/ PDF):- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ÷ ይኸውምበመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋምከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረትአልተቻለውም፡፡
ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለውይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎበመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ)÷ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያንሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውም)÷ በእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶበወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።

ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋታድራለች፤» የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ ፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደ ሥጋዬ በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብርአደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ነቢዩ ሆሴዕም፡- «ኑ÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስንጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነው)÷ እርሱም ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዶከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል)፤ እርሱ መትቶናል÷ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን መሆኑንአረጋግጧል፡፡ ሆሴ ፮÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናትአለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባውለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ ዕጓለ እመሕያውክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው÷ ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤»ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት በጠየቁት ጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድምልክት ይሻል÷ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ፥ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድርልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፪፥፴፰-፵።

ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
ጌታ በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ ይኽንንም ለመረዳትዕብራውያን ዕለታትን እንዴት እንደሚቆጥሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በሀገራችን የሌሊቱን ሰዓትመቁጠር የምንጀምረው ከዋዜማው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው÷ የቀኑን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረውደግሞ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ የሌሊቱ ሰዓት የሚያ ልቀው ከማለዳው አሥራ ሁለትሰዓት ሲሆን፥ የቀኑ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ የቀኑም የሌሊቱም ሰ ዓትተደምሮ ሃያ አራት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰዓት ዕለቱን ይወክላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እሑድ ዕለትከሃያ አራቱ ሰዓ ት በአንዱ ቢወለድ እሑድ ተወለደ ይባላል÷ ቢሞትም እሑድ ሞተ ይባላል፡፡ ዕለቱበሚጀምርበትም ሰዓት ሆነ፥ በሚያልቅ በት ሰዓት፥ ድርጊቱ ቢፈጸም ያ ሰዓት እንደ አንድ መዓልትናእንደ አንድ ሌሊት ይቆጠራል፡፡ አውሮፓውያን አንድ ብለው ሰዓት መቁጠር የሚጀምሩት በእኛአቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነው፡፡ እስከ ሃያ አራት ይቆጥሩና በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስትሰዓት ሲሆን ይጨርሳሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ዜሮ ይሉና እንደገና አንድ ብለው መቁጠርይጀምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከሌሊት እስከ ሌሊት ይቆጥራሉ፡፡ አሜሪካውያን ደግሞ በእኛ ከሌሊቱሰባት ሰዓት ሲሆን አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለውይጨርሳሉ፡፡ ከዚያም በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት እንደገና አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡
ዕብራውያን ግን ዕለትን መቁጠር የሚጀምሩት ከዋዜማው ማለትም በአውሮፓውያን ከአሥራሰባት ሰዓት÷ በአሜሪካውያን ከአምስት ሰዓት (P.M.) ÷ በእኛ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓትጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ሃያ አራት ሰዓት ቆጥረው አንድቀን ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው እያንዳንዱ ሰዓት የዕለቱን መዓልትና ሌሊት ይወክላል፡፡ በዚህመሠረት ጌታችን ከመስቀል ወርዶ የተቀበረው ዓርብ ቅዳሜ ከመግባቱ በፊት ነው፡፡ ዓርብ ዕለቱየሚጀምረው ከዋዜማው ሐሙስ በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታየተቀበረው በዓርብ ሃያ አራት ሰዓት ክልል ውስጥ በመሆኑ እንደ አንድ መዓልትና ሌሊት ይቆጠራል፡፡ሁለተኛው ደግሞ ዓርብ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለውነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ቅዳሜ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ቀን አሥራ አንድ ሰዓትያለው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሰኞ ምሽት ይገባል፡፡ ጌታ የተነሣው በሦስተኛው ቀን እሑድ መንፈቀ ሌሊትነው።

እንዴት ተነሣ?
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይኽንንም፡- «ነፍሴን ደግሞአነሣት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሣት ዘንድ) አኖራለሁና (በፈቃዴ እሞታለሁና)፤ ስለዚህ አብይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት÷ ሥጋዬንምበመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ (ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገርየለም)፡፡ ላኖራት (ነፍሴን በገነት÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው) ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት(ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ዮሐ ፲÷፲፯-፲፰፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈ ተም፡፡» በማለት መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስበፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ ትንቢት ነበር፡፡ ኢሳ ፶፫፥፯፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከዚህየሚመሳሰል ቃል ተናግሯል፡፡ ፩ኛጴጥ ፪÷፳፴፡፡ በዚህ ዓይነት ነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለትኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ÷ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቷል፡፡እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና፡፡ ዮሐ ፲፩÷፳፭፡፡
ይህ እንዲህ ከሆነ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤» በማለትአይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ፡- «እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤» ለምን አለ? የሚልጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ «አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም፤» የሚሉአሉና፡፡ እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያው«እግዚአብሔር አስነሣው፤» ያለው «እግዚአብሔር» የሚለው ስም የሦስቱም መጠሪያ እንጂ የአብ ብቻአለመሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ወልድም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፩ ፣የሐዋ ፳÷፳፰፡፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፪፡፡ ስለዚህ፦ ሥላሴ በፈቃድአንድ በመሆናቸው፥ «አንዲት በሆነች በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ፤አንድም፦ ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ፥ መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ተነሣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስእግዚአብሔር በመሆኑ ተነሣ፤» ተብሎ ይተረጐማል፥ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም የሚያረጋግጥልንይኽንኑ ነው፡፡ «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ይላል። መዝ ፸፯፥፷፭።

ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
በእስራኤል ባሕል፥ የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት መቃብር፥ የመቀበር ልማድ አላቸው፡፡ዮሴፍ በግብፅ የእስራ ኤልን ልጆች፡- «እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተጋር ውሰዱ፤» ብሎ ያማላቸው፥ የአባቶቹ የአብርሃም እና የይስሐቅ የያዕቆብም አፅም ካረፈበት ለመቀበርፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. ፶÷፳፭፡፡ በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢ ይ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰውበተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤» ብሏል ፡፡ ፩ኛነገ ፲፫÷፴፩፡፡ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበትከአዲስ መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ «ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕበፍታ ከፈነው÷ ከዓለት በወቀረ ው በአዲሱ መቃብርም አኖረው÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይአንከባሎ ሄደ፤» ይላል ማቴ ፳፯÷፶፱፡፡ ይህም የሆነው እርሱ ባወቀ በርሱ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህምበማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው፥ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብር ተቀብሮ የነበረው ሰው፥ የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ፥ በተአምር ተነሥቷል።፪ኛነገ ፲፫÷፳፡፡ እንግዲህ ጌታችንም፥ ከአንዱ ቅዱስ መቃብር ተቀብሮ ቢሆን ኖሮ፥ ሞትን ድል አድርጐበሚነሣበት ጊዜ «በራሱ አልተነሣም፥ የቅዱሱ አፅም ነው ያስነሣው፤» ባሉት ነበር፡፡ ይኸንን ምክንያትለማጥፋት ነው፥ በአዲስ መቃብር የተቀበረው።

እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኋላ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደጲላጦስ ተመልሰው፡- « ጌታ ሆይ÷ ያ ሰው (ክርስቶስ)፥ ገና በሕይወቱ ሳለ፥ ከሦስት ቀን በኋላእነሣለሁ፥ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ÷ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም፡- ጠባቆች አሉአችሁ፥ እንዳወቃችሁአስጠብቁ፤» አላቸው፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ፡፡» ማቴ፳፯፥ ፷፫÷፷፮፡፡ በታላቅ ድንጋይ የተገጠመው መቃብር፥ ድንጋዩ እንደታተመ፥ ክርስቶስ ሞትን ድልአድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም፦ ምንም የማያግደው መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብርስለነበረ ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው፥ በተዋሕዶ፥ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለቃልበመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አይሁድ ብዙ ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ እያዩትይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣ ነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ ሲወጣ አያዩትም ነበር፡፡ ዮሐ ፰÷፶፱፤፲፥፴፱፡፡ ይህም የሆነው፥ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ፥ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡ ከትንሣኤውበኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ ሳይከፈት የገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ ፳÷፲፱፤ ፳፮፡፡በልደቱም ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና እንደታተመች የተወለደው ለዚህነው፡፡ ኢሳ ፯÷፲፬፡፡ ማቴ ፩÷ ፳-፳፫ ፣ ሉቃ ፪÷፮-፯፡

መቃብሩን ማን ከፈተው?
ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል ከሆነ፥ «መቃብሩንማን ከፈተው? ለምንስ ተከ ፈተ?» የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፤ በወንጌል እንደተጻፈው፥ የአይሁድሰንበት ቅዳሜ ካለፈ በኋላ፥ እሑድ በማለዳ፥ ፀሐይ ሲወጣ፥ መግደላዊት ማርያም÷ የያዕቆብም እናትማርያም ሶሎሜም ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበር፡፡ ትልቁ ጭንቀታቸው «ድንጋዩንከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?» የሚል ነበር÷ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውምአይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ ነው፡፡እርሱ ግን፡- «አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፤ ተንሥቷልበዚህ የለም፡፡» አላቸው፡፡ ማር ፲፮÷፩-፮፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ በኋላ ባዶ የነበረውንመቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክ ነው፡፡ የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶችያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩ ነው፡፡ አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ፥ መግደላዊትማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለወረደታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፡፡ እንደ ሞቱም ሆኑ፡፡መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፥ እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹአውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ ፳፰÷፩-፮፡፡ ደቀመዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ ወደ ከፈተው መቃብር ገብተው መግነዙን ካዩበኋላ ነው። ዮሐ ፳፥፯።

በኲረ ትንሣኤ፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለባሕርይ አባቱ፥ ለአብ ለእናቱ ለድንግልማርያምም የበኵር ልጅ ነው፡፡ ዕብ ፩÷፮፣ ሉቃ ፪÷፯፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር በመሆኑ የትንሣኤያችንምበኵር እርሱ ነው፡፡ «አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው(በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳምበተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋንይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤» ይላል፡፡ ፩ኛቆሮ፲፭÷፳-፳፫፡፡ በተጨማሪም፡- «በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና፥ ከፍጥረት ሁሉበፊት በኵር ነው፡፡ (ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ ነው)፤ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል ፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብናከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በህልውና የነበረ ነው)፤ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉማለት የቤተ ክርሰቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኵርነው፡፡» የሚል አለ፡፡ ቈላ ፩÷፲፮-፲፰፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም÷በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታትገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» ብሏል። ራእ ፩፥፭።
በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት አስነሥተዋል፡፡ ፩ኛነገ ፲፯፥፳፪ ፣ ፪ኛነገ ፬÷፴፪-፴፰፡፡ በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ÷ አልዓዛርንም ከሞትአንሥቷቸዋል፡፡ ማቴ ፱÷፳፭፣ ሉቃ ፯÷፲፭ ፣ ዮሐ ፲፩÷፵፬፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎበሰጠም ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉ ተነሥተዋል፡፡ ማቴ ፳፯÷፶፫፡፡ እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤአልተባሉም፡፡ ምክንያቱም፦ አንደኛ፥ በራሳቸው ኃይል የተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ ሦስተኛ፥ ፍጡራን ናቸው፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡ ዳግመኛምአይሞትም፡፡ ይኽንንም፡- «ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት፥ ሞትም ወደፊትእንዳይገዛው እናውቃለንና ÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና፡፡» በማለት ሐዋርያውገልጦታል፡፡ ሮሜ ፮÷፱፡፡ ጌታችንም፡- «ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁእነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤» ብሏል። ራእ ፩፥፲፰።

ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?
ጌታችን በተዘጋ ቤት ገብቶ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ ጊዜ፥ መንፈስ የሚያዩ መስሏቸውኅሊናቸው ደንግጦ÷ ልባቸውም ፈርቶ ነበር፡፡ እርሱም፡- «ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለምንስ አሳብበልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት÷ መንፈስ ሥጋናአጥንት የለውምና፥ እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤» ካላቸው በኋላ እጆቹንና እግሮቹን አሳይቷቸዋል። እነርሱምከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- «በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?» አላቸው። እነርሱምከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ፥ ይላል። ሉቃ ፳፬÷፴፮-፵፫። ለሦስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ በተገለጠላቸውም ጊዜ አብሯቸው ተመግቧል፡፡ ዮሐ ፳፩÷፱-፲፬።ይኽንንም ያደረገው ከትንሣኤ በኋላ መብላት መጠጣት ኖሮ አይደለም፡፡ አለማመናቸውን ለመርዳትነው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በተዋሐደው ሥጋ ለመነሣቱ እርግጠኞች እንዲሆኑ ነው፡፡ ከወንጌሉእንደምንረዳው ደቀመዛሙርቱ ይበልጥ እርግጠኞች የሆኑት ስላዩት ሳይሆን፥ ያቀረቡለትን በመብላቱናበመጠጣቱ ነውና፡፡

ለምን አትንኪኝ አላት?
መግደላዊት ማርያም ገና ሰማይና ምድሩ ሳይላቀቅ፥ በማለዳ፥ ሽቱ ልትቀባው ከመቃብሩአጠገብ ተገኝታ ነበር። እንደደረሰችም ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተፈንቅሎ አየች። ይህች ሴት በሦስተኛውቀን እንደሚነሣ ከባለቤቱ ብትሰማም፥ « እንደተናገረ ተነሥቶ ነው፤» ብላ አላመነችም። ላለማመኗምምክንያት የሆነው፥ «እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት ሰረቁት፤» የሚለው የጭፍሮች ወሬነው። ጭፍሮቹ እውነትን በሐሰት ለውጠው ይኽንን ያወሩት፥ በገንዘብ ተደልለው ነው፡፡ ማቴ፳፰÷፲፩-፲፭፡፡ ለዚህ ነው ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ፡- «ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፥ ወዴትምእንዳኖሩት አላውቅም፤» ያለቻቸው፡፡ ዮሐ ፳÷፪፡፡ ከመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት መላእክትተገልጠውላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?» ባሏት ጊዜም፥ «ጌታዬን ወስደውታል፥ ወዴትምእንዳኖሩት አላውቅም፤» ብላቸዋለች፡፡ ዮሐ ፳÷፲፫፡፡ በመጨረሻም ጌታ ራሱ ተገልጦላት፡- «አንቺ ሴትስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?» ሲላት አላወቀችውም፡፡ ለዚህ ነው፥ አትክልት ጠባቂመስሏት፡- «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ፥ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፥ እኔም ወስጄ ሽቱእንድቀባው፤» ያለችው፡፡ ዮሐ. ፳÷፲፭፡፡ በዚህን ጊዜ፥ «ማርያም»፥ ብሎ በስሟ ቢጠራት በድምፁአወቀችውና «ረቡኒ ( መምሕር ሆይ)» አለችው፡፡ መልኩን አይታ፥ ድምፁን ሰምታ÷ ትንሣኤውንአረጋግጣ፥ «አምላኬ» አላላችውም፡፡ ስለዚህ «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ አትንኪኝ፥ ነገር ግን ወደወንድሞቼ (ወደ ደቀመዛሙርቴ) ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ÷ ወደ አምላኬና ወደአምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል፥ ብለሽ ንገሪያቸው፤» አላት፡፡ እንዲህም ማለቱ የእርሱ የእግዚአብሔር ልጅመባልና የእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች መባል ፍጹም የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ፥ «አባቴ» ቢልየባሕርይ ልጅ በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ግን የጸጋ ልጆች ናቸው፡፡ እርሱ፥ «አምላኬ» ቢል ስለተዋሐደውሥጋ ነው፡፡ የተዋሐደው የፈጠረውን ሥጋ ነውና ፡፡ እነርሱ ግን «አምላካችሁ» ቢባሉ ፍጡራን ስለሆኑነው፡፡ በዚህም እርሱ ፈጣሪ እነርሱ ፍጡራን መሆናቸውን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ቶማስን ግን፡- «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህአትሁን፤» ብሎታል፡፡ ዮሐ ፳፥፳፯ ፡፡ ምክንያቱም አይቶ፥ ዳስሶ፥ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ የሚያምንነውና፡፡ አንድም ሥጋውንና ደሙን ለመዳሰስ÷ ለመፈተት፥ የተጠራ የተመረጠም ካህን ነውና፡፡

ተስፋ ትንሣኤ፤
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደሲኦል ይወርዱ ነበር ። ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪፡፡ «ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩትላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ( እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤» የተባለው ለዚህ ነው፡፡ሮሜ ፭÷፲፬፡፡ ከዚህ የተነሣ እነ አብርሃም እንኳ ሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲኦል ነው፡፡ እነ ኢሳይያስ፡- «ጽድቃችንም ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፷፬ ÷፮፡፡ እነ ኤርምያስም፡- «ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል፡፡ ኤር ፲፪÷፲፫። በዚህምክንያት የብሉይ ኪዳን፥ ዘመን ዘመነ ፍዳ÷ ዘመነ ኵነ ÷ ዘመነ ጽልመት ተብሏል፡፡ በዚህ ዘመን እነቅዱስ ዳዊት፡- «አንሥእ ኃይለከ÷ ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልህን አንሣ÷ እኛንም ለማዳን ና ፤ (በሥጋተገልጸህ÷ ሰው ሁነህ አድነን)፤» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡ መዝ 79÷ 2 ፡፡ «ፈኑ ብርሃነከወጽድቀከ፤ ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤ (ብርሃን ወልድን÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን ላክልን) ፤እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ÷ (ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት)ይውሰዱን »፤ እያሉም አብን ተማጽነዋል፡፡ መዝ ፵÷፫፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚያ በጨለማዘመን ሆነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብርአጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያንጊዜ ከሲኦልእንደሚወጡ፥ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁአድርጓቸዋል፡፡ ይህም ተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል፡፡ ምድራዊውንእንዲንቁ፥ ሰማያዊውን እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል፡፡ « ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርእንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛ ጴጥ ፫÷፲፫፡፡ ቅዱሳን በሃይማኖት አይተዋታል፡፡ «አዲስሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና÷ ባሕርም ወደፊትየለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡» ይላል፡፡ ራእ ፳፩÷፫፡፡ እግዚአብሔርም፡- «እነሆ÷ አዲስሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም አይገቡም፡፡ ነገር ግንበፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ፥ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት÷ ሕዝቧንምለደስታ እፈጥራለሁና፡፡» ብሏል፡፡ ኢሳ ፷፭፥፲፯።

ሙታን እንዴት ይነሣሉ?
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ማንቀላፋቱ የሞት፥ መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩምየትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፬÷፲፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፭÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣትየመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን እንደሚነሡ በቃልም በተግባርምአስተምሯል፡፡ በቃል ፡- «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምምያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡» ሲልአስተምሯል፡፡ ዮሐ ፭÷፳፱፡፡ በተግባርም የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል፡፡ ዮሐ ፲፩÷፵፫፡፡ቅዱሳን ነቢያት፡- እነ ኢሳይያስ «ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡» ብለዋል። ኢሳ፳፮÷፲፱፡፡ እነ ዳንኤልም፡- «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች (ሁሉም) ይነቃሉ፤እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷ እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስቊልና፡፡» ብለዋል፡፡ ዳን፲፪÷፪፡፡ በተለይም ለነቢዩ ለሕዝቅኤል፥ እግዚ አብሔር፦ በአፅም የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ፥«እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩ ይመስ ልሃልን?» ሲል ጠይቆታል፡፡ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ ታውቃለህ፤» የሚል መልስ ሰጥቶቷል፡፡ በመጨ ረሻምእነዚህ ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡- «እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ÷ ትንፋሽምገባባቸው፥ ሕያዋንም ሆኑ÷ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ፡፡» በማለት ገልጦታል፡፡ሕዝ ፴፯፥፩-፲፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር«ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡»ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህምአያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደትይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካልይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳምሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገርግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም።የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊውእንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞእንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞእንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡ በፊልጵስዩስ መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውንእንደሚስል የተዋረ ደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል ፫÷፳፩። ሐዋርያው ቅዱስዮሐንስም፡- «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፤» ብሏል፡፡ ፩ኛ ዮሐ ፫÷፪።

የትንሣኤ ጸጋ፤
በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል÷ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል ። ሙታን የነበርን ሕያዋን÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን÷ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድልመንሣትህ የት አለ?» የምንል ሆነናል፡፡ ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፣ ፩ኛቆሮ ፲÷፶፭፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «እኛአገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስንእንጠ ባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውንእንዲመስል የተዋረደውን ሥጋች ንን ይለውጣል፡፡» የምንል ሆነናል፤ ፊል ፫፥ ፳-፳፩፡፡ ናፍቆታችን ሁሉበትንሣኤ ያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው፡፡ «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ፥በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለንእናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና÷ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛቆሮ ፭፥፩-፪፡፡ ሐዋርያው ቅዱስጴጥሮስም፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ»ብሏል፡፡ ፩ኛጴጥ ፩÷፫፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- «በሚመጡ ዘመ ናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለውቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነ ሣን፤ በክርስቶስኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።» ብሏል። ኤፌ፪÷፮-፯።


የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment