Wednesday 2 April 2014

የጎልማሶችና ወጣቶች ማኅበራት ኅብረቱ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር መዘጋጀቱን አስታወቀ፤ በወጣቶቹ ዝግጅት የተደናገጡ የለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞች የኅብረቱን እንቅስቃሴና አመራሮቻቸውን በሽብር ለመወንጀል እያሤሩ ነው

ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ሕገ ወጥ ተግባራት መካከል÷ ያልተፈቀደላቸው ሰባክያን ስምሪትና የኅትመት ውጤቶቻቸው ሽያጭና ስርጭት፣ የአስመሳይ ባሕታውያንና መነኰሳት ነውረኛ ድርጊቶች፣ ሕገ ወጥ ልመና፣ የአጥቢያ አስተዳደር ሙስናና የወጣት ሱሰኝነት ይገኙበታል፡፡
ማዕተብ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በተለይም ወጣቱ ከሱስ ነጻ መኾን አለበት፤ መስቀሉን አንጠልጥሎ በየባንኮኒውና በየዳንኪራው ከመታየት መጠበቅ አለበት፤ ዶግማውን፣ ቀኖናውንና ትውፊቱን ያወቀና የጠነቀቀ፣ በኢኮኖሚያዊና ፋይናንሳዊ አቅሙም ጠንካራና እርስ በርሱ መደጋገፍ ይገባዋል፡፡
102 ያኽል ማኅበራት አንድነት የፈጠሩበትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አቅራቢነት የቅ/ሲኖዶሱን ዕውቅና ያገኘው ኅብረቱ ከ150,000 በላይ አባላት አሉት፡፡ የኅብረቱ አመራሮችና አባላት፣ ወቅቱ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነትና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በፍቅር እስከ መጨረሻው የምንቆምበት ነው ብለዋል፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን ተጨንቃ ትጣራለች፤ የምትጣራው ወጣቱን ነው፤ ወጣት ዕውቀትና ጉልበት አለው፤ እኔ ሴቷን ጨምሮ ኹላችን እያንዳንዳችን ሓላፊነት አለብን፤ ወይ ግዴታችሁን ተወጡ ወይ ውረዱ የምንልበት ወቅት ነው!!›› /የማኅበራት ኅብረቱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን/

(ኢትዮ – ምኅዳር፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፷፪፤ መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥና ዙሪያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠርና ቤተ ክርስቲያኒቱን በማኅበረሰብ ልማት ለመደገፍ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን መንደፉን አስታወቀ፡፡

የማኅበራት ኅብረቱ መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ወደ ርእሰ አድባራት ወገዳማት ዳግሚት ጽዮን አዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያንባካሔደው የአባላት ጉዞ መርሐ ግብር ላይ እንደተገለጸው፣ ፕሮጀክቶቹ በአብዛኛው ‹‹የችግሩ ምንጮችም የመፍትሔው አካላትም እኛው ነን፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውስጣዊ ችግሮች ማጽዳትና ተጨማሪ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በር መዝጋት ላይ ማተኮር አለብን፤›› በሚል አቅጣጫ የተቀረፁ ናቸው፡፡

ሃይማኖቱን ከውስጥ በመፃረር አስተምህሮውንና ሥርዓቱን በሚቃረን መልኩ የሚፈጸሙ ተግባራትን እንዲታረሙ ማድረግና አስቀድሞ መከላከል፤ የአስተዳደር መዋቅሩን ከሙስና፣ ብኩንነትና ምዝበራ መጠበቅ፤ የአገልግሎትና የአባቶች አልባሳትን ለብሰው እምነቱን በሚያስነቅፉ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን መቆጣጠር፤ በልማት ተነሽዎች ምክንያት የምእመናን ቁጥር በመቀነሱ አቅማቸው የተመናመኑ አጥቢያዎችን መደገፍና ወደማስፋፊያ ሰፈሮች የሔዱ ምእመናንን የአገልጋዮች እጥረት መቅረፍ ከፕሮጀክቱ ትኩረቶች መካከል በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡

ማኅበራቱ በየደብራቸውና በማኅበራቱ ኅብረት በኩል በተቀናጀ ኹኔታ የቀረፁዋቸውንና ከባይተዋርነትና ብሶት ከማሰማት ይልቅ ተግባርና መፍትሔ ተኮር ናቸው ያሏቸውን እኒህን ፕሮጀክቶች÷ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያት፣ ከስብከተ ወንጌል ኮሚቴዎች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች እና ከፖሊስ ጋራ በመተባበር እንደሚተገብሯቸው ገልጸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ችግር ለመፍታት የግድ የአስተዳደር አባል አልያም ካህናት መኾን የለብንም ያሉት የማኅበራቱ አባላት፣ በፕሮጀክቶቹ ትግበራ ሒደትና ፍጻሜ መፍትሔ ያገኛሉ ካሏቸው ችግሮች መካከል÷
ቅዱሳት ሥዕላትን ከዓለማውያን ሥዕሎች ጋራ ቀላቅሎና በጎዳና ላይ አንጥፎ መሸጥ፣
በገጠር አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ስም በተጭበረበሩ ደብዳቤዎችና ሙዳየ ምጽዋትን በየሆቴሉና ሬስቶራንቱ በማስቀመጥ ሕገ ወጥ ልመናን በማካሔድ የግል ጥቅምን ማካበት፣
በሞንታርቦ ቅሰቀሳዎች ማወክና የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት ማስተጓጎል፣
የመነኰሳትን ልብስ በመልበስ በየመንገዱና በየመሸታው ቤት ነውረኛ ተግባራትን መፈጸም፣
በሚመለከተው አካል ያልተፈቀደላቸውና በእምነት አቋማቸው ጥያቄ የሚነሣባቸው ሰባክያንና ዘማርያን ስምሪትና የኅትመት ውጤቶቻቸው ሽያጭና ሥርጭት ይገኙበታል፡፡

ከ፳፻፪ ዓ.ም ጀምሮ ለጥምቀት በዓልና በወርኃዊ ክብረ በዓላት ወቅት ባንዴራ በመስቀል፣ ምንጣፍ በማንጠፍ፣ ቄጤማ በመጎዝጎዝ፣ የተሳላማዊውን ሥርዓት በማስከበርና አጠቃላይ ሥነ በዓሉን በማድመቅ የሚታወቁ ወጣቶች መንፈሳውያን ማኅበራት አንድነት የኾነው የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት፣ የተለመደው የማኅበራቱ ወጣቶች አገልግሎት እንደተጠበቀ ኾኖ በወጣቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ ላይም በጥልቀት መፈጸም ስለሚገባቸው ተግባራት የማኅበራቱ አባላት በጉዞ መርሐ ግብሩ ላይ መክረዋል፡፡

የማኅበራት ኅብረቱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን በፕሮጀክቶቹ ይዘት ዙሪያ በሰጠችው ማብራሪያ÷ ‹‹ማዕተብ ያሰረ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በተለይ ወጣቱ በሱስ ቦታዎች መገኘት የለበትም፤ መስቀሉን አንጠልጥሎ በየባንኮኒውና በየዳንኪራው ከመታየት መጠበቅ አለበት፤ ወጣቱ የሃይማኖቱን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት የተማረና የጠነቀቀ፣ በኢኮኖሚያዊና ፋይናንሳዊ አቅሙ ጠንካራና እርስ በርሱ የሚደጋገፍ መኾን ይገባዋል፤ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን ማንንም የማያሳፍር የነጠረ ትምህርት ስላላት ኦርቶዶክሳዊው ወጣት ወደ ሰንበት ት/ቤቶች ገብቶ እምነቱን፣ ሥርዓቱንና ትውፊቱን መማር አለበት፤ በኅብረቱ ታቅፎ ደግሞ ለኑሮው የሚያስፈልጉትንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚያገልግለበትን የክህሎት ሥልጠናዎች እንዲያገኝ እናደርጋለን፤›› ብላለች፡፡

የማኅበራት መብዛት ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ችግር የሚፈጥር በመኾኑ ወደ ኅብረቱ የመግባትን አስፈላጊነት ያስረዳችው ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ፌቨን÷ ማኅበራቱን ከሰንበት ት/ቤቶችና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ለማጋጨት የሚጥሩ አካላት እንዳሉ በመግለጽ ወቅቱ ከስሜታዊነት ተጠብቆና ስልታዊ ኾኖ በርካታ የአገልግሎት ተሞክሮ ካላቸው ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋራ በፍቅርና በአንድነት እስከ መጨረሻው ቆመን የምናገለግልበት ነው በማለት አሳስባለች፡፡

የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተቃዋሚ አማሳኝ የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንደሚሉት ምእመኑ ገንዘቡን ሰጥቶ ዘወር ማለት ያለበትና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳይ የማያገባው ሳይኾን በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት በካህናትና ምእመናን አንድነት የተደራጀው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አካል ነው፡፡

ከዚኹ ጋራ በተገናኘ በተለይ የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች በጥያቄና አስተያየት እንዳነሡት የምንገኝበት ወቅት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ፣ ሙስናና በአድርባይ ፖሊቲከኝነት የታገዘ ጎሰኝነት ተሳስረውና ተመጋግበው የቤተ ክርስቲያኒቱን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ብሎም አጠቃላይ ህልውናዋን የሚፈታተኑበት በመኾኑ የምእመኑ ትኩስ ኃይል የኾነው ወጣቱ የሚጠበቅበት ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ የኅብረቱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ፌቨን ይህን የገለጸችው፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ተጨንቃ ትጣራለች፤ የምትጣራው ወጣቱን ነው፤ ወጣት ዕውቀትና ጉልበት አለው፤ እኔ ሴቷን ጨምሮ ኹላችን እያንዳንዳችን ሓላፊነት አለብን፤ ወይ ግዴታችሁን ተወጡ ወይ ውረዱ የምንልበት ወቅት ነው፤›› በማለት ነበር፡፡

[በመርሐ ግብሩ ላይ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ታሪካዊ አመጣጥ፣ ያለበትን ወቅታዊ መገለጫዎች ከዚኽም አንጻር የተወሰዱ የማጋለጥ ርምጃዎችና በቀጣይ በየደረጃው ኹሉም በየበኩሉ ሊወስድ ስለሚገባው ድርሻ በተመለከተ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦ የፓነል ውይይት ተካሒዷል፡፡ የጉዞ መርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ከየአካባቢያቸው ተጨባጭ ኹኔታ በመነሣት ያደረጉት የሐሳብና መረጃ ልውውጥ ከፍተኛ ግንዛቤ ያስጨበጠ ከመኾኑም ባሻገር ከአዳራሽ ውጭም በመልስ ጉዞ ላይ የውይይቱ ግለት በምንተ ንግበር መንፈስ የቀጠለበትን መነሣሣት ፈጥሮ ነበር፡፡]

ከ150,000 በላይ ጠቅላላ አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበራት ኅብረት ከአራት ዓመት በፊት የተቋቋሙና ከዚያም በኋላ እየተጨመሩ የመጡ 102 ያኽል የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበራት አንድነት ሲኾን በየካቲት ወር 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አማካይነት በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለት መተዳደርያ ደንብ ዕውቅና ማግኘቱ ተገልጦአል፡፡

*******************************************

የአዲስ አበባ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥና ዙሪያ ኑፋቄን፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመቆጣጠር እንዲህና እንዲህ ባለው ፍቅረ ቤተ ክርስቲያንና መንፈሳዊ ቅንዓት ላይ ብቻ ተመሥርተው የመከሩበት የአባላት ጉዞ መርሐ ግብር ዜና፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞችን ማደናገጡና ማሳሰቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አማሳኞቹ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የክሥ መግለጫ ባወጡበት የመጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ስብሰባቸው፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረቱን እንቅስቃሴና አመራሮቹን ጭምር ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ተመሳሳይ በኾነ አኳኋን በሽብር የመወንጀል ውጥን እንዳላቸው የሚያመለክቱ ንግግሮች ተደምጠዋል፡፡

ማንነቱ በሐራውያን ምንጮች በመጣራት ላይ የሚገኝ አንድ የስብሰባው ተሳታፊ ሲናገር እንደተደመጠው፣ የማኅበራት ኅብረቱ እንደ አዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ኹሉ ዕውቅና ተሰጥቷቸው በክፍላተ ከተሞች የተደራጁት በማኅበሩ[በማኅበረ ቅዱሳን] ተንኰል ነው፤ በጀትም በማኅበሩ ተመድቦላቸዋል፡፡

የማኅበራት ኅብረቱ ውይይት በአዲስ ዓለም ከተማ እንደተካሔደ የጠቀሰውና ሙሉ ውይይቱ የተቀረፀበትን ካሴት ቅጂ እንደሚያቀርብ የገለጸው ተናጋሪው፣ ‹‹በአዲስ አበባ ለምን አንድ ነገር አናደርግም፤ ቢሞትኮ ሦስትና አራት ሰው ነው›› የሚሉ የዐመፅ ዕቅዶች በመርሐ ግብሩ ላይ ተመክሮበታል ብሏል፡፡

በዩኒቨርስቲዎች መንግሥት ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንዳይካሔድ በተማሪዎች የአምልኮ፣ የአመጋገብና የአለባበስ ሥርዓት ረገድ ያስተላለፈውን መመሪያ አድንቆ በቃለ አጋኖ የተናገረው ይኸው የመረጃ ሰው ነኝ ባይ ግለሰብ፣ በዚኽ መመሪያ ምክንያት የማኅበሩ[የማኅበረ ቅዱሳን] የግቢ ጉባኤያት እንቅስቃሴ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ገልጦአል፡፡

በአኹኑ ወቅት በሠራተኛ ጉባኤ ስም እንቅስቃሴው የሚካሔድባቸው ተቋማት ‹‹ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፣ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ እና ኮርያ ሆስፒታል››መኾናቸውንና እነዚኽም እንቅሰቃሴዎች ተደርሶባቸው ክትትል እየተደረገባቸው በመኾኑ ውጤቱን በቀጣይ እንደሚገልጽላቸው፣ እስከዚያው ድረስ ማኅበረ ቅዱሳንን እስከ ሞት ደርሰው እስከ ወዲያኛው ለመቃወም ያሰቡበትንና በመቃወማቸውም ሳቢያ ችግር የሚደርስበትን አባላቸውን በገንዘብ ይኹን በአስፈላጊው ነገር ለመደገፍ ወሳኝ ነው ያሉትን ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ማኅበር በአዲስ አበባ›› ምሥረታን እንዲያፋጥኑ አማሳኞቹን በተደጋጋሚ ሲያሳስብ ተሰምቷል፡፡

የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተቃዋሚዎች በስብሰባቸው ማኅበራቱን እንዲኽ ባለ አሥቂኝ፣ ዓይን ያወጣና ፍጹም የፈጠራ በኾነ ክሥ ለመወንጀል ውጥን እንዳላቸው ከመጋለጡ በፊት የማኅበራቱን ወጣት አባላት በመጀመሪያ ማርከው ከጎናቸው ለማሰለፍ ሞክረው የነበረውየአማሰኑትን የምእመናን ገንዘብ ማማለያ በማድረግ እንደነበር የጉዳዩ ተከታታዮች ይገልጻሉ፡፡ ይህም አልሳካ ሲላቸው በአንዳንድ አጥቢያዎች ወጣቶቹን ከሰንበት ት/ቤት አባላት ጋራ የማጋጨት ሙከራ ማድረጋቸውን፣ እስከ መታሰር የደረሱ ወጣቶችም መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኾነው ኾኖ ያልተሳካው የገንዘብ መደለያም ይኹን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በማገናኘት ሊሰነዘር የተፈለገው የሽብር ፈጣሪነት ውንጀላ የአማሳኞቹን ዓላማ ፍንትው አድርጎ ከማሳየቱም ባሻገር የማኅበራቱ አባላትና የኅብረት አመራሮቹ አካሔድ ለአንዲት እናት ቤተ ክርስቲያን ዕድገት በመሥራት ማህቀፍ ውስጥ ክፍተት ሳይፈጥሩ እርስ በርስ በመደጋገፍ በቅርበት መጠባበቅና መከታተል በእጅጉ እንደሚያስፈልግየሚያጠይቅ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment