Monday, 11 June 2012

ዘመነ ጽጌ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት


እመቤታችንን ማመስገን በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ


አእላፍ መላእክት በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ


የተለካ መቅደስ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አለን? ዓላማውና ስልቱስ ምንድን ነው?


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አለን? ዓላማውና ስልቱስ ምንድን ነው?
ይህ ጽሁፍ ከማህበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ ላይ የተወሰደ ነው።


ሰኔ 11 ቀን 2003 ዓ.ም
/ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ግንቦት 2003 ዓ.ም/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “መታደስ አለባት” የሚሉ ድምፆችን የሚያሰሙ አካላት አሳባቸውን በተለያዩ መንገዶች ማሰማት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነዚህ አካላት በመጽሔቶች፣ በጋዜጦች፣ በመጻሕፍት፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ በዓውደ ምሕረት ስብከቶችና በሚያገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ይኸን ጩኸታቸውን ማስተጋባቱን ተያይዘውታል፡፡ እንዲህ እያሉ ያሉትም “ኦርቶዶክሳውያን ነን” እያሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በተለያየ ቦታና ሓላፊነት ላይ ካሉና እንጀራዋን ከሚበሉ፣ ጥቂቶች እንዲሁም ደግሞ በኅቡእና በግልጽ በተለያየ መልክና ቅርጽ ራሳቸውን አደራጅተው ቤተ ክርስቲያኗ ሳትወክላቸው እርሷን ወክለው፣ “እኛም ኦርቶዶክስ ነን” በሚል ካባ ራሳቸውን ደብቀው እምነቷንና ሥርዓቷን “ይህ ሳይሆን ሌላ ነበር” እያሉ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርትና መንፈስ የተዋረሳቸው ሰዎች ናቸው፡፡
 
ተሐድሶ የሚባል ነገር አለን? እነዚህ አካላት በአንድ በኩል ተሐድሶ የሚባል ነገር እንደሌለና ተሐድሶ የሚባለው ጉዳይ የሆነ አካል (እነርሱ እንደሚሉት ማኅበረ ቅዱሳን) ስም ለማጥፋት ሲል የፈጠረው የፈጠራ ወሬ እንጂ በሕይወት የሌለ ምናባዊ ነገር እንደሆነ ያስወራሉ፣ ይናገራሉ፡፡ ግን በእውነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ መታደስ አለበት በማለት የሚሠራ የተሐድሶ እቅስቃሴ የለምን?

ይህን ጉዳይ እነርሱው በይፋ ካወጧቸው የኅትመት ውጤቶቻቸው ለመመልከትና ለመታዘብ ይረዳ ዘንድ ራሳቸው በተለያዩ መጻሕፍቶቻቸው፣ መጽሔቶቻቸውና ጋዜጦቻቸው ካወጧቸው መካከል የተወሰኑትን ብቻ እንመልከት፡-
hohitebirhan.jpg
“እንደ እውነቱ ከሆነ በወንጌል እውነት ከታደሱ በኋላ በየጊዜው እየተመዘዙ የወጡት ምእመናኖቿና አገልጋዮቿ በውስጧ ቆይተው የተሐድሶን ሥራ እንዲሠሩ ቢደረግ ኖሮ፣ በወንጌል ተሐድሶ ያገኙ ክርስቲያኖች ለዓመታት የጸለዩበትንና የጓጉለትን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ በቅርብ ጊዜ ሊያዩ ይችሉ እንደ ነበር የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት 2002፣ ገጽ 15)


“ተሐድሶ እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ እንቅስቃሴም ውጤታማና ትርፋማ ይሆን ዘንድ ዓላማን፣ ሒደትንና ግብን የያዘ ድርጊት እየተከናወነበት ያለ ሊሆን ስለሚገባው፣ ያለፈውና እየሆነ ያለው ግብረ ተሐድሶ ተመዝግቦ ለአሁኑና ለሚመጣው ትውልድ በሥነ ጽሑፍ ዳብሮና አምሮ ሊቀርብለት ይገባዋል፡፡” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት2002፣ ገጽ 17) “በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን አረሞችን በገሀድ ካልነቀልን ተሐድሶን እንዴት ልናመጣ እንችላለን? መባሉ አይቀርም፡፡ ዳሩ ግን ስሕተቶችን ፊትለፊት ሳይቃወሙ ስሕተቶች እንዲታረሙ ማድረግ የሚቻልባቸው የተፈተኑ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌም …” (ኆኅተ ብርሃን፣መጋቢት 2002፣ ገጽ 19)
metkie.jpg

“ከ2000 ዘመናት በላይ ያስቆጠረች የእኛ ቤተ ክርስቲያንማ እንዴት አብልጦ ተሐድሶ (መታደስ) አያስፈልጋት?” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 15) “ቤተ ክርስቲያናችን በክፉ ሰዎች ሴራ ዓላማዋን ስታለች፣ የሐዋርያትንም ትምህርት ገፍታለች፣ ስለ ሆነም ይህን የሐዋርያት ትምህርት በክፉዎች ምክንያት በመጣሱ በድፍረት ተሳስተሻልና ታረሚ ልንላት፣ በድፍረትም በሥልጣንም ሕዝቡን ልናስተምር ይገባል፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 20) “ቤተ ክርስቲያናችን በየሀገሩ የተነሣውን የተሐድሶ የወንጌል እሳት በተለይ በሐረር፣ በባሕር ዳር፣ በአዲስ አበባ፣ በማርቆስ፣ በጎንደር፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በባሌ ለማዳፈን ያን ሁሉ እልፍ አእላፍ ሠራዊት የቤተ ክርስቲያን አለኝታ ወጣት ወንጌል ባልገባቸው ምእመናንና ካህናት እያስደበደበች ለሌላ ድርጅት አሳልፋ ከመስጠት ይልቅ ስሕተቷን አርማ ልጆቿን በጉያዋ ብትይዝ ኖሮ ዛሬም ጭምር ጋብ ላላለው ፍጥጫ አትዳረግም ነበር፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 16) “ሕዝባችን በልማድና በባህል ሃይማኖትን መያዙና ይህን የያዘውን ሃይማኖት ለመጣልና ለማጣራትም በቂ እውቀት ስለሚጎድለው በራሱ አንብቦ መረዳት ስለማይችል …” (የሚያሳውቁት ሃይማኖትን ለማስጣል ነው ማለት ነው) (ይነጋል፣ 1997፣ ገጽ 144)


እነዚህ እነርሱው ከጻፏቸውና አሳትመው ካሰራጯቸው መካከል ለአብነት ያህል የተጠቀሱት በግልጽ የሚያሳዩን ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ትምህርት የሚቃወሙና ሊለወጥ ይገባል የሚሉ ራሳቸውን “ተሐድሶ” የሚል ስያሜ ሰጥተው በተለየ መልክና ቅርጽ በግልጽና በኅቡእ እየሠሩ ያሉ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡ ራሳቸው እንዲህ በይፋ “እኛ አለን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ ቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል” እያሉ እየተናገሩ “አይ፣ ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም” ማለት እንዴት ይቻላል?

ዓላማቸው ምንድን ነው? ተሐድሶዎች ዋና ዓላማቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ምእራባውያን ሚሲዮናውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አጥፍቶ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ መሥራት ከጀመሩበት ከሃያኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ሦስት ስልቶችን ተጠቅመዋል፡፡ የመጀመሪያው እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ የሠሩበት ስልት ሲሆን እርሱም የራሳቸውን አስተምህሮ ማስተማር ነበር፡፡

ከ1950 ዓመት ጀምሮ እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የሠሩት የራሳቸውን እምነት መሰበክ ሳይሆን በዋናነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመንቀፍና በማጥላላት ምእመኑ እንዲኮበልል በማድረግ ነበር፡፡

ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን እየሠሩበት ያለው ሦስተኛው ስልት ደግሞ "ኦርቶዶክስ ነኝ" ብሎ ውስጧ ገብቶ “ትታደስ” እያሉ በመጮኽ ቤተ ክርስቲያኗ እንዳለች እንድትለወጥ በማድረግ ምእመናኗን ከእነ ሕንፃዋና አስተዳደራዊ መዋቅሯ መረከብ ነው፡፡ የእነርሱ ምኞትና እቅድ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ወደ ሦስተኛው ሺሕ እንዳትሻገር ማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ በዚህም ብስጭታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም ፓውልባሊስኪ (Paul Balisky) የተባለ “የዓለም አቀፍ ተልእኮ ማኅበር” የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በ1992 ዓ.ም በወጣው “የክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር” በተባለ መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ የደከሙት ድካምና ያወጡት ገንዘብ ሁሉ ወደ ጠበቁት ግብ እንዳላደረሳቸው፡-

“ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም ወንጌላውያኑ አሁን በማደግ ላይና በመካከለኛ ኑሮ ላይ ያለውን የከተማውን ኅብረተሰብ መቀየር አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የተማረና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከፍተኛ ቅንዓት ያለው የወጣቶች ኃይል ማኅበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሃያ አንደኛው መ/ክ/ዘመን ዘልቃ መጓዝ ትችል ዘንድ እየተጋደለ ነውና፡፡” በማለት ከሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በፊት የማጥፋት ሕልም እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡(The Christian Science Monitor, 8 June, 2000)

ስለሆነም ከዚያ በፊት ያደርጉት እንደነበረው በውጭ ሆኖ ምእመናንን ለመንጠቅ በመሥራት ብቻ ካሰቡት ቤተ ክርስቲያኒቱን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ግብ ለመድረስ ቀላል እንዳልሆነ ተረዱ፡፡ ስለዚህ አዲስ ስልት መቀየስ አስፈለጋቸው፡፡ ይህም “እናድሳለን”
በሚል ሽፋን ከውጭ ወደ ውስጥ ሠርጎ በመግባት ምእመኑን እስከ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የመረከብ ስልት ነው፡፡ ይህንም ኬንያ ውስጥ የሚታተመው “The Horn of Africa, Challe nge and opportunity” የተባለው መጽሔት “ዓላማው አዲስ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያኗን (ኦርቶዶክስን) መለወጥ (ፕሮቴስታንት ማድረግ) እንጂ - The objective is not to set up a new church as such but to introduce reforms within the church” በማለት ገልጾ ነበር፡፡ (The Horn of Africa, Challenge and opportunity, p. 6)

ስለዚህ አዲሱ ስልት “የጥንቷ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትክክል ነበረች - The ancient orthodox was the right Church” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያንን ከውጭ ከመቃወም ይልቅ ውስጥ ገብቶ ምእመን፣ ካህን፣ መነኩሴ፣ ሰባኪ … መስሎ ከፕሮቴ ስታንት እምነትና ባህል ውጭ ያለውን ነገር ሁሉ “ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት አይደለም፣ ይህን እገሌ የጨመረው ወይም የቀነሰው ነው … ’ እያሉ ቤተ ክርስቲያኗ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ በሙሉ ጠፍቶ ሙሉ በሙሉ ፕሮቴስታንት እስክትሆን ድረስ መሥራት ነው፡፡

ይህን ስልታቸውንም በኅትመቶቻቸው በይፋ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም በአንድ ስልታቸውን ይፋ ባደረጉበት መጽሔታቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡-

“ታዲያ እርሷን (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን) የማዳኑ ሥራ ከየት ይጀምር? እዳር ሆኖ አንዳንድ ምርኮኛን ማፍለሱ የሚፈለገውን የኦተቤን ተሐድሶ ሊያመጣ ይችላልን? አገልግሎቱ ከየት ወደ የት ቢሄድ ይሻላል? ማለት ከውስጥ ወደ ውጭ ወይስ ከውጭ ወደ ውስጥ? በውስጧ እያሉ የወንጌል እውነት ለተገለጠላቸው አገልጋዮቿ እንደ ውጊያ ቀጠና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ምሽግ በአሁኑ ጊዜ የማስለቀቅና የጠላትን ወረዳ ከጥቃት ነጻ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ያለው በሁለት ወገን ነው፤ … ” ይልና ቀጥሎም ወደ ግባቸው ለመድረስ መደረግ አለበት ያሉትን እንዲህ ዘርዝረዋል፡-

ውስጥ ያሉት እግዚአብሔር በሰጣቸው የውጊያ ቀጣና ውስጥ ሆነው በታማኝነት በእግዚአብሔር ቃል ምስክርነትና በጸሎት ውጊያውን መቀጠል አለባቸው፡፡ በውስጥ ላለው ለዚሁ ውጊያ በወንጌል የታደሱ ክርስቲያኖች ሁሉ እንደ ሙሴ እጃቸውን ወደ ላይ በማንሣት ታላቁን ርዳታ ማድረግና በደጀንነት መቆም ይገባቸዋል፡፡

እነዚህ በወንጌል ተሐደሶ አግኝተናል የሚሉ ሁሉ በውጭ ሆነው ወደ ውስጥ የሚያደ ርጉትን ውጊያ መቀጠላቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለውስጠኛው ውጊያ የሚያገለግል ትጥቅ ያላቸውን ወደ ውስጥ ማስገባትና የውስጠኛውን የውጊያ መስመር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡

“ … በዚህ የተቀናጀ ስልት መንፈሳዊው ጦርነት ቢቀጥል በውስጥ የተሰለፈው ሠራዊት (በተሐድሶ ስም የሚሠራው የፕሮቴስታንት ክንፍ) እያጠቃ ወደ ውጪ ሲገሰግስ፣በውጭ ያለውም (በግልጽ ፕሮቴስታንት ሆኖ የሚሠራው) ከበባውን አጠናክሮ ወደ ውስጥ ሲገፋ እግዚአብሔር በወሰነው ቀን የውስጡና የውጪው ሠራዊት ሲገናኙ በውስጧ የመሸገው ጠላት መሸነፉን በሚመለከት በአንድነት የድል ዝማሬ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡” 
(ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት 2002 ዓ.ም)

ይህ ሁሉ የሚያሳየው
ሀ) በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በይፋ የተቀናጀ ጦርነት ያወጁባት መሆኑን፣
ለ) የጦርነቱ አንዱ ስልት ውስጥ ሆኖ በውስጥ አርበኝነት መሥራትና መዋጋት መሆኑን፣
ሐ) የጦርነቱ ዓላማ ጠላት የተባለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማፍረስ መሆን ነው፡፡

የተሐድሶው ዘመቻ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

ተሐድሶዎች ያሰቡትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዳለች ፕሮቴስታንታዊ አድርጎ ለውጦ ለመረከብ ያላቸውን ምኞትና ዓላማ እውን ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ) የሐሰት ውንጀላዎችን መፍጠርና ማሰራጨት ሌባ ሲሰርቅ የሚያየውን ወይም መስረቁን ያወቀበትን ሰው ይወዳል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ እንደዚሁም እነዚህ በውጫቸው የቤተ ክርስቲያንን ለምድ የለበሱ፣ በውስጣቸው ግን ኦርቶዶክሳዊ የሆነውን እምነትና ባህል አጥፍቶ የምእራባውያን ባህል ተሸካሚ ለማድረግ የሚሠሩ ክፉ ሠራተኞች (ፊል.3÷2) ዓላማቸውንና ስልታቸውን የሚያውቅባቸውን ማንኛውንም ግለሰብም ሆነ ማኅበር አምርረው ይጠሉታል፣ ይፈሩታልም፡፡፡ በእነ ማርቲን ሉተር በአውሮፓ ተካሒዶ ምእራባውያንን ወደ እምነት አልባነትና ክህደት ማድረሱን ዛሬ በተግባር ያስመሰከረውን ተሐድሶ (ፕሮቴስታንት) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ላይ እውን በማድረግ ይሁዳ ስለ ሠላሳ ብሩ ሲል ጌታውንና አምላኩን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመሸጥ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጋር “አሳልፌ እንድሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” (ማቴ.!1÷05) ብሎ ጌታውን ለሽያጭ እንዳቀረበ፣ እነዚህም ስንቅና ተስፋ የሚሰጧቸውንና ስልት ነድፈው ከርቀት እያሳዩ የሚያሠሯቸውን የላኪዎቻቸውንና የጌቶቻቸውን ምኞት ለማሳካት እንቅፋት ይሆኑብናል የሚሏቸውን ሁሉ ማሩን አምርረው ወተቱን አጥቁረው በማሳየት ስማቸውን በማጥፋት እንዲጠሉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ከዚህ ተግባራቸው ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው ሕገ ደምብ መሠረት በአባቶች ቡራኬና ፈቃድ የተመሠረተውንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ ዓቅሙ በፈቀደ መጠን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውንና ይህን ለቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አደገኛ የሆነ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ምንነት በማጋለጥ ለሕዝብ የሚያስረዳውን ማኅበረ ቅዱሳንን ስሙን በኅትመቶቻቸውና በልዩ ልዩ መንገድ ማጥፋትና ሰይጣናዊ አስመስሎ መሳል አንዱ ስልታቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የሚከ ተሉትን እንመልከት፡-

“ማቅ (ማኅበረ ቅዱሳን) ያለ እኔ ቤተ ክርስቲያን፣ ሀገርና መንግሥት የለም ብሎ በጭፍን የሚያስብ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሌላ መንፈሳዊ ማኅበርም ሆነ ጉባኤ ለማየት ዓይኑ የተሸፈነ ነው፡፡ ራሱን የቅዳሴ፣ የቅኔና የመጻሕፍት ማስመስከሪያ ቤተ መምህራን አድርጎ በማየቱ በእርሱ እጅ ፈቃድ ያላገኙ ሰባክያንና መዘምራን ቢፈጠሩ የተለመደው የኮሚኒስቶች ፍልስፍና (የሀሰት ስም የማጥፋት ቅስቀሳውን) ያወርድባቸዋል፡፡”
 (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 1፣ርእሰ አንቀጽ)

እንግዲህ ይህን የሚለው አካል በግልጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተሐድሶ ያስፈልጋታል እያለ በዚሁ ጋዜጣ የገለጸው የተሐድሶ ድርጅት ነው፡፡ ልዩነቱ የዓላማ መሆኑን ራሳቸው ተናግረው ሲያበቁ እንደገና መልሰው ተሐድሶ መባልን የሐሰት ስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ይላሉ፡፡ አንባቢዎቻቸው ይህን እንኳን ማገናዘብ አይችሉም ብለው ይሆን?

“የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት እግዚአብሔር ፍጹም ጨካኝ ስለሆነ ስለማይሰማንና በርኅራሄ ከእርሱ የተሻሉ ቅዱሳን በፊቱ ቆመው እንዲለምኑልን የእነርሱ ልመና ግድ ብሎት ስለሚምረን በአማላጅነት እንመን ይላል፡፡” (ይነጋል፣ 1997 ዓ.ም. ገጽ 123) “ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ይህ የሰይጣን ማኅበር አሁን ወደ ነፍሰ ገዳይነት ሊገባ ራሱን እያዘጋጀ ነው፡፡” (ይነጋል፣ 1997 ዓ.ም.ገጽ 127) ይህ የስም ማጥፋት ዘመቻ በሀገር ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ዋናው የተሐድሶ ዘመቻ አርቃቂዎችና ስልት ነዳፊዎች በሆኑት በምእራባውያን ፓስተሮችም በብዛትና በዓይነት የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ዊሊያም ብላክ የተባለው አሜሪካዊ ፓስተር አናሲሞስ በተባለው የጦማር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ማፈራረስ እንደሚቻልና በአሁኑ ወቅትም የእርሱና መሰል ድርጅቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እየተዋጓት እንደሆነ “Struggle for the soul of the Ethiopian orthodox Church” በተሰኘው ጽሑፉ ላይ በሰፊው ገልጧል፡፡ የፕሮቴስታንት ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነው የተሐድሶ አንቅስቃሴ ምን ማለት መሆኑን ለዓላማቸው መሳካት እንቅፋት ሆኖብናል ያለውን ነገር ሲናገር ገልጾታል፤ እንዲህ ሲል፡-

“Working against both the ongoing creep of Western values and the attempts by Reformists to restore the church, a reactionary movement called Mahebere Kidusan and led by members of the hierarchy and priests and others, are seeking to fend off any changes and to preserve aspects of the Church which they feel are crucial to their identity and Ethiopia’s place in the world. …
በሀገሪቱ ውስጥ እየተንሰራፋና ሥር እየሰደደ ያለውን ምእራባዊ ባህልና በተሐድሶ አራማጆች ቤተ ክርስቲያኒቷን ለማደስ የሚደረገውን ጥረት ሁለቱንም የሚቃወምና ለዚህም እየሠራ ያለ አድኃሪ የሆነ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይህ ማኅበርም ቤተ ክርስቲያንን ለመለወጥ የሚደረገውን ማንኛውንም ነገር ለመከላከልና ለራሳቸው ማንነትና ኢትዮጵያ በዓለም ስላላት ቦታ አስፈላጊ ነው የሚሉትን የቤተ ክርስቲያኒቷን ገጽታ ለመጠበቅ ይፈልጋሉ፡፡”
http://www.Compassdirect.org/english/country.ethiopia/11092/ተሐድሶዎች ቤተክርስቲያናቸውን የሚወዱትንና ለእምነታቸውና ለሥርዓታቸው ተቆርቋሪ የሆኑትን ምእመናን፣ ካህናት፣ መነኮሳት … ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል ነገር መኖሩን ከነ ጭራሹ ያልሰሙ ሰዎች ቢሆኑም እንኳ “ማኅበረ ቅዱሳን (ማቅ)” ናቸው የሚል ታርጋ በመለጠፍ ለማሸማቀቅ ይሞክራሉ፡፡ በዚህም የተሐድሶ ጉዳይ የሌለና የሆኑ ቡድኖች ጠብና ሽኩቻ ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ይጥራሉ፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ለማመን የሚከብዱ የበሬ ወለደ ዓይነት የስም ማጥፋት ወሬዎችን በማኅበሩ ላይ በማሰራጨት ላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌም በቅርቡ “የማኅበረ ቅዱሳን የሃያ አምስት ዓመት ስትራቴጂ ነው” በሚል ስም አንድን ሕፃን እንኳ ሊያሳምን በማይችል መልኩ ራሳቸው የፈጠሩትን አሉባልታ የማኅበሩ አስመስለው በሐሰት ማኅተም አትመው በኢንተርኔት አሰራጭተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የፈጠራ ክሶችንና ስም ማጥፋቶችን ደህና አድርገው ተያይዘዋቸዋል፡፡

ለ) የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደርና መዋቅር መቆጣጠር ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያኒቷን ለመለወጥና ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የተመቸች ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ ለመቆጣጠር የሚመኙት አንዱ ነገር የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደርና መዋቅር መያዝ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንደበት በመናገር፣ ቤተክርስቲያን ያልሆነችውን ናት፣ የሆነችውን ደግሞ አይደለችም በማለት ያሰቡትን የተሐድሶ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይረዳቸዋል፡፡

ወደዚህ ግብ ለመድረስም በተለያዩ ጊዜያትና ስልቶች ከመሪጌቶች፣ከቀሳውስት፣ ከመነኮሳት፣ ከዲያቆናትና ከሌሎችም መካከል በተለያየ ጥቅማ ጥቅምና ድለላ የማረኳቸውንና ያሰለጠኗቸውን ሰዎች በአስተዳደር መዋቅሩ ውስጥ ለማስገባትና ቦታውን ለመያዝ ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተወሰነ ርቀት መጓዝ ችለዋል፡፡ ይህም በስልታቸው እንደ ገለጹት “መንፈሳዊ ቀውስ የደረሰበትን አስተዳደር ማረምና ማስተካከል” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት2000፣ ገጽ 16) በሚል ሽፋን የሚካሔድ ነው፡፡

ይህን ጉዳይ እስከ የት ድረስ መግፋትና ማድረስ እንደሚፈልጉ ሲገልጹም እንዲህ ብለዋል፡-
“ማቅ (ማኅበረ ቅዱሳን) ወደደም ጠላም ቤተ ክርስቲያኒቱ በእውነት በሚወዷትና የወንጌልን እውነት በሚያገለግሉ መምህራንና ሊቃውንት ይህንም እውነት ተቀብለው አምላካቸውን በንጹሕ ልብ ሆነው በሚያመልኩ፣ በተለይም መጪው ዘመን በትካሻቸው ላይ የወደቀባቸው ከመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን እየተመረቁ የሚወጡ የወንጌል አርበኞችና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው አባቶች በሚወስዱት የማያዳግም እርምጃ ቤተ ክርስቲያናችን ተሐድሶን ታደርጋለች፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2000፣ ገጽ 2) ጳጳሳት ሳይቀሩ የማያዳግም እርምጃ መውሰዳቸውና ቤተ ክርስቲያኒቱን ማደሳቸው የማይቀር መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ይህን ሕልማቸውን እውን ለማድረግ የቤተ ክርስቲያኗን የአስተዳደር መዋቅር፣ እስከ ጵጵስና ደረጃ ያለውንም መቆጣጠር ዋና ስልታቸው ነው፡፡

ዛሬ የመነኮሱበት የማይታወቅ ሰዎች የአባቶቻችንን ቆብ አጥልቀው መስቀሉን ጨብጠው ቀሚሱን አጥልቀው ካባውን ደርበው፣ ያልሆኑትን መስለው፣ ሌሎችም የነበሩ፣ ዛሬ ግን ያልሆኑ፣ ዓላማቸውን እንደ ይሁዳ ለውጠው የክፋቱ ተባባሪ ሆነው ያሉ ሁሉ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ሲጫወቱ ዝም እየተባሉ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች የነገዪቱ ጳጳሳት የማይሆኑበት እድል አይኖርም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡

ይልቁንም አሁን ሃይማኖታቸው በግልጽ ፕሮቴስታንት (ተሐድሶ) የሆኑና ብዙ ጉድ ያለባቸው፣ የምግባር ድቀት ያንገላታቸው፣ የሃይማኖት አባት ሆነው ምእመናንን ለማስተ ማርና ለመምራት ቀርቶ ተነሳሒ ለመሆን እንኳ የከበዳቸው ሰዎች ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ጵጵስና ለመሾም የሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር አፋፍ ላይ እየደረሱ እየተ መለሱ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲሁ ከቀጠለ እነዚህ ሰዎች አንድ ቀን የጳጳሳትን አስኬማ ደፍተው፣ በትረ ሙሴ ጨብጠው፣ “አቡነ” እገሌ ተብለው ላለመምጣታቸው ምን ዋስትና አለ? “ሞኝ ቢቃጡት የመቱት አይመስለውም” እንደሚባለው እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎችን ለጵጵስና እጩ አድርጎ እስከማቅረብ ደረጃስ እንዴት ሊደረስ ቻለ?

ማንነታቸው ተጣርቶ በንስሐ የሚመለሱት ቀኖና ሊሰጣቸው፣ የማይመለሱት ደግሞ ሊለዩ (ሊወገዙ) ሲገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሆነው በቤተ ክርስቲኒያቱ ህልውና ላይ ወሳኝ አካላት ሊሆኑ መታሰቡ በራሱ የሚያሳየው ከባድ ነገር አለ፡፡

እነዚህን ሰዎች በአድባራትና በገዳማት ዕልቅናና በተለያየ ሓላፊነት ከመሾም ጀምሮ ግልጽ የሆነ የአደባባይ ጉዳቸውን ዝም ከማለትና አልፎ አልፎም ከማበረታታት ጀምሮ በቤተ ክርስቲኒያቱ አስተዳደር ውስጥ እንዳሻቸው እንዲናኙበት የሚፈቅድና የሚመች የተሐድሶ ሰንሰለት አለማለት ይሆን?

እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችና አባቶች እንደ እንጀራ ልጆች እየተቆጠሩና እየተገፉ እነዚህ ተሐድሶዎች ደግሞ ባለሟሎች መስለው ከዚያም አልፎ ለጵጵስና ታጭተው ማየትና መስማት በእጅጉ ያማል፣ ልብንም ያደማል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች አናት ላይ ወጥተው የጵጵስና መዓርግ ጨብጠው ከመጡ በኋላ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሊያመጡ ያሰቡትን ስልታዊ አደጋ መገመት ውኃን የመጠጣት ያህል ቀላል ነው፡፡

ስለሆነም እነርሱ ያሰቡት ከባድ ትርምስ ሳይመጣ ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እንዲሉ በጊዜ ከጸሎት ጀምሮ ማንኛውም ሊደረግ የሚገባውን የመከላከል ሥራ ከወዲሁ መፈጸም ይገባል፡፡ ቁጭ ብሎ የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ያቅታልና፡፡ ይህም “እነ እገሌ ምን እየሠሩ ነው?” በሚለው ያልጠቀመን ፈሊጥ ሳይሆን “እኔ ምን አደረግሁ?

አሁንስ ምን ማድረግ አለብኝ?” በሚል ሊሆን ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር በቤቱ የተሰገሰጉ ይሁዳዎችን የሚያጋልጥበትንና ከመንጋው የሚለይበትን ዘመን ያቅርብልን፣ አሜን፡፡

Friday, 1 June 2012

ጅማ ኪዳነምህረት


ግራዉ ከራሴ በታች ፤ መኃ 2፤6


ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የፌስቡ ገጽ ላይ የተወሰደ
ለመምህራችን ቃለ ህይወትን ያሰማልን ያገልግሎት ዘመናቸውንም ያርዝምልን

እሥራኤልን ከግብጽ እየመራ የወጣው ሙሴ ሕዝቡን ከግብጽ ይዞ መውጣት ይቻለው ዘንድ የተዛዘው ታላቁ ትእዛዝ ፋሲካን በግብጽ ማክበር ነበር፡፡ ፋሲካ የሚባል በዓል ከዚያ በፊት ኖሮም ተከብሮም አያውቅም ነበርና በዝርዝር ማድረግ የሚገባቸዉ ሁሉ ተነገራቸዉ፡፡ ቀኑ በእነርሱ አቆጣጠር በአቢብ ወር በዐሥራ አራተኛዉ ቀን ይከበራል፡፡ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት በግ ጠቦት ይመርጣሉ፡፡ በምድረ በዳ ሲመሽ ያርዱታል፡፡ ደሙን ወስደዉ የቤታቸዉን በር ሁለት ማቃኖችና ጉበኑን ይረጩታል፡፡ ሥጋውን በሌሊት በእሳት ጠብሰዉ ይበሉለታል፡፡ ጥሬውንና በውኃ የተቀቀለዉን አይበሉም፡፡ የተረፈውን ሌሊቱን በእሳት ያቃጥሉታል፡፡በፍጥነት ይበሉታል፡፡ ከዚያ በኋላ ለሰባት ቀን የቂጣ በዓሉን ያደርጋሉ፡፡ ቂጣዉም ምንም እርሾ ያልገባበት ይሆናል፤ …./ዘፍ 12፤ 1-36/፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ዓይነት መሥዋዕት ሥርዓቶችና የበዓላት አከባበሮችን ተቀበሉ፡፡ በዚሁም መሠረት በየዕለቱ በጧት አንድ በማታ አንድ ነውር የሌለበት የበግ ጠቦት ይሠዋል፡፡ በየዕለቱም የእህል ቁርባን ይቀርባል፡፡በሰንበት፣ በወር መባቻና በሌሎች በዓላት ደግሞ የበጉ ቁጥር ይጨምራል፤ የፍየልና የከብት መሥዋዕቶችም ተጨምረዉ ይቀርባሉ፤ የእህሉም ቁርባን እንዲሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሕዝቡ በበደሉ ጊዜ እንደ ኃጢኣታቸዉና በደላቸዉ መጠን የተለያዩ መሥዋዕቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡በዘመነ ኦሪት ይህ ሁሉ ነገር በሥርዓት ጸንቶ ከዓመት እስከ ዓመት በዚህ መንገድ ሲፈጸም ኖሯል፡፡
የአይሁድ ፋሲካ በእነርሱ የአቢብ ወር በወሩ በዐሥራ አራተኛዉ ቀን እንዲከበር የታዘዘ በዓል ነዉ፡፡ ይህም የሆነበት የራሱ ምክንያት እንዳለዉ ሊቃውንት አስረድተዋል፡፡ በመጀመሪያ ወሩን የዐመቱ መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ ብሏቸዋል /ዘጸ 12፤2/፡፡ ይህንንም ይዘዉ ሊቃውንቱ መጀመሪያ ያለው ጥንተ ፍጥረት በዚህ ወር ቢገኝ ነዉ፤ ወይም ፍጥረትን የጀመረዉ (ጊዜንም ጭምር ማለት ነዉ) በዚህ ወቅት ነዉ ብለዉ ያስተምራሉ፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያንም ይህ ትምህርት በትርጓሜ ሲሰጥ የኖረ ነዉ፡፡ በተለይም ጌታ ዓለሙን ለማዳን ሰዉ የሆነበት ጽንሰቱ መጋቢት 29 ቀን መሆኑንና በኋላም ጥንተ ስቅለቱን መጋቢት 27 አርብ አድርጎ ትንሣኤዉን እሑድ መጋቢት 29 ደግሞ ማድረጉ የዓለሙ ድኅነቱ የተፈጸመበት በዚህ ዕለት የሆነዉ ፍጥረቱን እም ኀበ አልቦ (ካለመኖር) ኀበ ቦ (ወደ መኖር) ያመጣዉ በዚህ ዕለት ስለሆነ ነዉ በማለት ያስተምራሉ፡፡ ከዚህም ተነሥተዉ ዓለም በዚህ ዕለት ተፈጥሮ በዚህ ዕለት ድኅነቱ እንደተፈጸመለት ሁሉ በኋላም በዳግም ምጽአት በዚሁ ዕለት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሑድ በዘመነ ዮሐንስ ያሳልፈዋል ብለዉ ይጠብቃሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛዉ ዓመት እንደሆነ እርሱ እንደ ተናገረዉ ማንም አያዉቅም ይሉናል፡፡ ለዚህ ነዉ በዘመነ ዮሐንስ የመጋቢት 29ን በእሑድ መዋል አንዳንድ አባቶች ሲፈሩት የሚኖሩት፡፡ ስለዚህ ጌታ ለሙሴና ለእሥራኤል በግብጽ እያሉ ይህ ወር የዐመቱ መጀመሪያ ይሁናችሁ ያለዉ የፍጥረት መጀመሪያ ወር እንደሆነዉ የእናንተም ከግብጽ የምትወጡበት የመጀመሪያ ወር ይሁን ሲል፣ በዚሁ አንጻርም ደግሞ ነፍሳትም በግብጽ ከተመሰለች ከሲኦል በዚሁ ወር እንደሚወጡ ሲነግራቸዉ ነዉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ዐለሙ አልፎ ጻድቃን መንግሥተ ሰማያትን ኃጥኣንም ገሃነመ እሳትን የምትጀምሩበት ይህ ወር እንደሆነ ዕወቁ ሲል ነዉ ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡አንባቢ ሆይ ርእሳችን የሆነዉ የ‹‹ግራን›› ነገር ከዚሁ ግራና ቀኝ ቁመት ጋር እያሰቡት ይታገሱ፡፡
የእኛ የትንሣኤ በዓልም በዚሁ ወር የሚከበርበት መሠረታዊ ምክንያትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነዉ፡፡ ከላይ በሰፊዉ ለማተት እንደተሞከረዉ ጌታ የፋሲካዉን በግ ብሉ ያላቸዉ በወሩ በአሥራ አራተኛዉ ቀን ነዉ፡፡ ይህም የእነርሱ የወር አቆጣጠር በጨረቃ ስለሆነ ዐሥራ ዐራተኛዉ ቀን ማለት ጨረቃ ከተወለደችበት ወይም መታየት ከጀመረችበት ቀስ በቀስ እያደገች መጥታ ሙሉ የምትሆንበት ጊዜ ስለሆነ ነዉ፡፡ በሌላ ቋንቋ በሙሉ ጨረቃ ወይም በሙሉ ብርሃን ይሁን ማለቱ ነዉ፡፡ ይህም የፋሲካዉ በግ ቅዱስ ዮሐንስ የዓለምን ኃጢኣት የሚያስወግደዉ ያለዉ የክርስቶስ ምሳሌ ስለሆነ እርሱ እዉነተኛዉና ሕጸጽ(ጉድለት) የሌለበት ብርሃን መሆኑን አሁንም በምሳሌ ሲነግረን ነዉ፡፡ የሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያናችንም በመንፈቀ ሌሊት ከገጠር እስከ ከተማ ያላትን ብርሃን ሁሉ አብርታ ምእመናኑንም በእጃቸዉ ጧፍ አስይዛ ‹‹ ትንሣኤከ ለእለ አመነ፣ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ፤ ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን›› እያለች በመዘመር መቅደሱን የምትዞረዉ ለዚህ ነዉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናገኘዉም መድኃኒታችን የተሰቀለዉ የአይሁድ የፋሲካ በዓል ሐሙስ ሆኖ አርቡን ነዉ፡፡ ያስታዉሱ፤ ጨረቃ ሙሉ ብርሃን በሆነችበት ዕለት ማለት ነዉ፡፡ በእርሱ ስቅለትም ይህችዉ ሙሉ ብርሃን የነበረች ጨረቃ ደም መሰለች፣ ሁልጊዜም ሙሉ የሆነችዉ ጸሐይም ጨለመች፣ ክዋክብትም ረገፉ፡፡ ሦስቱም በአንድነት አማናዊ ብርሃን እርሱ መሆኑን የእነርሱም ከእርሱ የተገኘ መሆኑን መሰከሩ፡፡ መድኃኒታችንም ድኅነታችን ፈጽሞ( ፍጹም አድርጎ) እሑድ ተነሣ፡፡ ስለዚህም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የትንሣኤ በዓላችን የአይሁድ ፋሲካ ከዋለ በኋላ በሚዉለዉ እሑድ ማለትም እሥራኤል ከግብጽ ነፍሳትም ከሲኦል በወጡበት ወር ጨረቃም ሙሉ ብርሃን ከሆነች በኋላ በምሥጢር አጊጦ ያለፈዉን እያስታወሰ ብቻ ሳይሆን መጪዉን ዋናዉን ትንሣኤ ሙታንንም እያሳሰበ ሲዘከር ሲከበር ይኖራል፡፡በጨረቃ አቆጣጠር ወራቱ የሚውሉበት ጊዜ ስለሚለዋወጥ በሠላሳ አምስት ቀናት( ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዚያ ሠላሳ ባለዉ ጊዜ) ዉስጥ ሁልጊዜም ከአይሁድ ፋሲካ በዓል በኋላ ባለዉ እሑድ ጥንተ ታሪኩንና ምስጢሩን እንደጠበቀ ሲከበር ይኖራል ማለት ነዉ፡፡
ለትንሣኤያችን ምሳሌ ሆኖ የቆየዉ ይኸዉ የፋሲካዉ በዓል መሥዋዕቱን በተመለከተም የራሱ ሕጎች ነበሩት፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴንናአሮንን አለ። ይህ የፋሲካ ሕግ ነው ከእርሱ እንግዳ ሰው አይብላ። በብር የተገዛ ባሪያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ። መጻተኛናሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ።በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ አጥንትም አትስበሩበት። የእስራኤልምጉባኤ ሁሉ ያድርጉት።እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ከዚያም ወዲያ ይቅረብ፣ ያድርግ፣ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ። ለአገር ልጅ በእናንተ መካከልምለሚቀመጡ እንግዶች አንድ ሥርዓት ይሆናል። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁአደረጉ››/ዘጸ 12፤ 43-50/ ተብሎ አንደተጻፈ ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ በሕግና በሥርዓት ይፈጽሙ ነበር፡፡
እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ እያዳንዱ ሰዉ ለኃጢኣትና ለበደል ከሚያቀርበዉ መሥዋዕት ጀምሮ ሁሉም ለሐዲስ ኪዳን አገልግሎታችንና መሥዋዕታችን ብዙ መልእክቶችን የተሸከሙ ነበሩ፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና›› /ሮሜ 2፤28/ ሲል እንደ ገለጸዉ እነዚያ የመሥዋዕት ዓይነቶች ሁሉ ሌላ ትርጓሜ እንዳላቸዉ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡
የፋሲካዉ በግ ስለእኛ ስለሁላችን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበዉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና›› /1ኛ ቆሮ 5፤ 7/ ሲል እንደ ገለጸዉ ፋሲካችን እርሱ ነዉ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም›› /ኢሳ 53፤7/ ሲል የተናገረለት፣ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› /ዮሐ 1፤ 29/ ሲል ያረጋገጠልን አማናዊዉ የፋሲካችን በግ እርሱ ነዉ፡፡የፋሲካዉን በግ ደሙን የቀቡት ሁሉ ሞት ወደ ቤታቸዉ አልገባም፡፡ እንዲሁ ከፋሲካችን ከክርስቶስ ሥጋና ደም በልተዉ በደመ ማኅተሙ የታተሙትን ሁሉ ሞት አያገኛቸዉም፡፡ እነርሱ የበራቸዉን ጉበንና መቃን በሚታይ ቦታ ላይ እንደቀቡት በእኛም በግንባራችን ላይ እርሱ ያስቀባዉና  የሚያነብበዉ ማኅተም አለ፡፡ነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹ እግዚአብሔርም፦ በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው። እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ ›› /ሕዝ 9፤4-6/ ሲል እንደገለጸልን ምልክቱን እርሱ ያስቀረጸባቸዉ ብቻ ከዘላለም ሞት ይድናሉ።
በነቢዩ እንደተገለጸዉ ግን ፍርድ ከቤቱ መቅሰፍቱም በቤቱ ከተገኙ ሽማግሌዎች የጀመረዉ በቤቱ ከምንኖረውም ውስጥ ከሞት የማናመልጥ እንዳለን ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ የሚከሰተዉ የፋሲካዉን በግ ባለመብላት ብቻ ሳይሆን ከላይ የተጠቀሱትን ሕጎቹን አክብሮ ባለ መብላት ምክንያት ነዉ፡፡ስለዚህ እንዲህ ያለዉ ነገር እንዳይገጥመን አስቀድመን ሕጎቹን አንድ በአንድ እንመልከታቸዉ፡፡
1.      ባዕድ አይብላዉ
ከላይ በሰፊዉ እንደተዘረዘረው ሦስት አካላት እንዳይበሉት ታዝዟል፡፡ መጻተኛና እንግዳ( ከእሥራኤል ወገን ያልሆነ) እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ ባሮች ካልተገዘሩ ( አሁንም ባዕዳን የሆኑ) አይብሉ ተብሏል፡፡ ምክንያቱም የመንጻቱንም ሆነ ሌላዉን የቅድስና ሕግ አያውቁትም፡፡ ይህን ሳያውቁ ቢበሉት ደግሞ ‹‹ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል›› /ምሳ 13፤13/ ተብሎ እንደተጻፈ ጥፋትና መቅሰፍትን እንጂ ሥርየትና ሕይወትን አያገኙም፡፡ ይህም ልክ እንደ ይሁዳ ማለት ነዉ፡፡ ይሁዳ ራሱን ከአይሁድ የተንኮል ምክር አስተባብሮ ልቡናዉንና መንፈሱን ከሐዋርያት ኅብረት ሲያወጣ ባዕድ ሆነ፡፡ በዚሁ የባዕድ ልቡናዉ ሆኖ ከሥጋዉና ከደሙ ቢቀበልም ሳይጠቅመዉ ቀረ፡፡ በደኅንነት መሥዋዕቱም ጊዜ በግና ፍየል ለመሥዋዕት የሚቀርብበት ምክንያት ይህንኑ በምሳሌ ለማስረዳት ነበር፡፡ ምክንያቱም ጌታ የመሥዋዕት በግ ቢሆንም ተቀባዮቹ ወይም ቆራቢዎች ግን እንደ ይሁዳና ሐዋርያት የተገባቸዉና ያልተገባቸዉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የጌታ ሥጋና ደም ለተገባቸዉ (ሐዋርያትን ለመሰሉት) የበግ መሥዋዕት ሲሆንላቸዉ ላልተገባቸዉ (ይሁዳን ለመሰሉት) ደግሞ የፍየል ይሆንባቸዋል ማለት ነዉ፡፡ ይህም ማለት ግን ጌታ በፍየል መሥዋዕቱ ተመስሏል ማለት አይደለም፤ አይመሰልምም፡፡ ነገር ግን በኦሪቱ ፍየል ለደኅንነት መሥዋዕት የሚቀርበዉ ላልተገባቸዉ ሰዎች የጌታ ሥጋና ደም እንሚለወጥባቸዉ ወይም እንደማይጠቀሙበት ለማጠየቅ (ለማስረዳት) ነዉ፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴዉ ‹‹ እሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ፤ እሳት በላዒ ለዓማጽያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ፤ ትእዛዙን ለሚፈጽሙ ቅኖች የሚያድን የሕይወት እሳት ነዉ፤ ስሙን ለሚክዱ ለዓማጽያን ደግሞ የሚያቃጥል የሚያፍገመግም እሳት ነዉ›› እንዳለ እንደሚበሉት ሰዎች ሕይወት ይለወጥላቸዋል ወይም ይለወጥባቸዋል፡፡ አሁን ‹‹ስሙን ለሚክዱ›› ሲል እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰወች ሊቆርቡ ይመጣሉ ብሎ ሳይሆን ስሙን እየጠሩ እንደ ይሁዳ ልቡናቸዉ በፍቅረ ንዋይና በተንኮል ከተያዘ የማያምኑና አማጽያን የሚባሉትእነርሱ መሆናቸዉን ለማስረዳት ነዉ፡፡ ስለዚህ ባዕዳን አይብሉት የተባለዉ ሕጉን የማያከብሩ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር የማይኖሩ አይብሉት ለማለት ነዉ፡፡ ሊበሉት ከፈለጉ ግን ‹‹ወንዶቹ ይገረዙ፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናሉ›› የተባለዉ ለዚህ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ምድራዊ ዘራቸዉ ሳይሆን አለማመናቸዉ ነበርና፡፡ ስለዚህ አሁንም ፋሲካችንን ስናከብር እንደ ይሁዳ አካላችንን ቤተ ክርስቲያን ዉስጥ ሆኖ ሐሳባችንና ዓላማችን ግን ቤተ ክርስቲያንን መጠቀሚያ ሊያደረጓት ከሚሹ ከጠንቋዮች፣ ከክፉ ፖለቲከኞች፣ ሊለዉጧት ከተነሡ መናፍቃንና ተሐድሶዎች ወይም ይህን ከመሰለና ለቤተ ክርስቲያን ባዕድ ከሆነ ማንኛዉም ሐሳብ ጋር ያለን ከሆነ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ያሉ ሰዎች ፋሲካውን ሊቀበሉ አይገባቸዉም ይለናል፡፡ሊቁ አባ ሕርያቆስ ‹‹ በአማን ቁርባን ውእቱ ዘኢይክሉ ይጥዐሙ እምኔሁ ግሙናነ መንፈስ፤ መንፈሳቸዉን ያረከሱ ሰዎች ከእርሱ ሊቀበሉት የማይቻላቸዉ በእዉነት ቁርባን ነዉ›› /ቁ. 5/ እንዳለዉ ባዕዳን የተባሉት እነዚህ በአገልግሎትም ሆነዉ ነገር ግን በሐሳብና በውስጣቸዉ መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ናቸዉ፡፡ መብላት ከፈለጉ ይገረዙ የተባለዉም የሥጋ ሸለፈትን ማስወገድ ምሳሌነቱ የኃጢኣት ሸለፈትን ማለትም መንፈሳቸዉን ያረከሰዉን ነገር በንስሐ ቆርጠዉ ጥለዉ ይምጡ ማለት ነዉ፡፡ በዚህ ጊዜ ይቻላል፤ ቢቀበሉትም ሕይወት ይሆናል፡፡ በኦሪቱ ‹‹ እንደ አገር ልጅም ይሆናል›› ማለትም ለሰማያዊት ሀገር ለገነት ለመንግሥተ ሰማያትም የተገባ ይሆናል ማለት ነዉና ጽድቁን ገንዘብ ያደርጋል፡፡   
2.     በአንድ ቤትም ይበላ
ሌላዉ ስለፋሲካዉ የተሰጠዉ ትእዛዝ በአንድ ቤት የመበላቱ ጉዳይ ነዉ፡፡ በዚያ ጊዜ በግብጽ እያሉ እንኳ ከአንዱ ቤት ወጥቶ እንዲሔድ አልተፈቀደም፡፡ ይህም ከላይ እንደገለጽነዉ ሥጋዉና ደሙ በአንድ ቤት በቤተ ክርስቲያን ብቻ ልንቀበለዉ እንደሚገባ የተሠጠ ትዕዛዝ በመሆኑ ነዉ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።›› / መዝ 68፤ 5-6/ ሲል እንደገለጸው ምድረበዳዉ የሌሎች ነዉ፡፡ እኛ እንደተጻፈው እግዚአብሔር በቤቱ እንዲያሳድረን የእርሱንም ሥጋና ደም (የፋሲካዉን በግ) እንዲመግበን አስቀድሞ ነግሮናልና ሌላ ቦታ እንበላዉ ዘንድ ክብሩንም ከአማናዊነት ወደ ምሳሌነት እናወርደዉ ዘንድ አንገዳደረዉም፡፡ ይህ ፋሲካ የሚበላባት ቤቱም ቤተ ክርስቲያን አንዲት ብቻ ናት፡፡ የተረፈው ሥጋ እንኳ ከቤት ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ አይጣል የተባለዉ የክርስቶስ ሥጋና ደም ከቤተ ክርስቲያን ዉጭ ሌላ ቦታ ሊጣልም ሊበላም ስለማይገባ ነዉ፡፡ አባ ጄርም ይህን በተረጎመበት ድርሳኑ የኖኅ መርከብ ዉስጥ የገቡት ብቻ ከጥፋት ዉኃ እንደዳኑ ፤ዳግመኛም በረዓብ ቤት የነበሩ ብቻ ከኢያሪኮ ጥፋት እንዳመለጡ በአንዲት ቤተ ክርስቲን ተሰባስበዉ ሥጋዉንና ደሙን የበሉ ብቻ ይድናሉ ይላል፡፡
3.     አጥንቱ መሰበር የለበትም
ስለ መሥዋዕቱ ከተሰጠዉ ትእዛዝ አንዱ አጥንቱ አይሰበር የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህም ስለ እኛ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበዉ በግ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርፋቱና እየተገፋ በወደቀ ጊዜ፣በችንካሩም ሆነ ለንጊኖስ በጦር በወጋዉ ጊዜ ከአጥንቱ አንድም እንኳ አንደማይሰበር አስቀድሞ የተነገረ ምሳሌያዊ ትንቢት ነዉ፡፡ ይህንንም ወንጌላዊ ዮሐንስ ‹‹ ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ።… ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነዉ›› /ዮሐ 19፤ 32-36/ በማለት አረጋግጦልናል፡፡
በግብጽ የነበሩት ሕዝቡም ሙሴ እንደነገራቸዉ አድርገው ለእግዚአብሔር እንደታዘዙ ሁሉ እኛም እንዲሁ ለእግዚአብሔር በሐዋርያትና በተከታዮቻቸዉ እንደ ሰማነዉ አድርገን ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የምትፈጽመው ሥርዓተ አምልኮ በሙሉ እንዲህ የታዘዘውንና የተተረጎመውን (ጌታ አማነዊ ያደረገውን) ብቻ ነዉ፡፡ በርእሳችን እንደተቀመጠዉ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ከተለዩት በተለየዉ ቅኔያዊ መዝሙሩ በመኀልየ መኀልይ ላይ ግራዉ ከራሴ በታች ናት የሚለን ይህችን ኦሪት ነዉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍተ ኦሪትን ዕቃ ቤት እንደተቀመጠ መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን ተርጉማ አማነዊ በሆነ መንገድ የምትፈጽማት ስለሆነ ከራሴ በታች ናት አለቻት፡፡ እንዲህ የምትለዉ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ራሷ ደግሞ ክርስቶስ ነዉ፡፡ ስለዚህ ኦሪትን ‹‹ከራሴ በታች›› ስትል ሥጋዌን አስቀድማ በምሳሌ ያሳየች የትንሣኤ በዓላችንን በፋሲካ በዓሏ፣ ለመሥዋዕተ ሐዲስ ለክርስቶስ ሥጋና ደምም ምሳሌዉን ስታሳይ የቆየች ቀድማ የተላከች መመሪያና በዚያም መሠረት እንድንፈጽም እንደ ካርታ ሆና ያገለገለች ስለሆነ ከራሴ በታች ጉዝጓዜ ትራሴ ትላታለች፡፡ በሰሙነ ሕማማቱም ስትነበብ የምትሰነብተዉ ለዚህ ነዉ፡፡ መሠረትና መደላድልነቷን ትራስነቷን ልንረሳዉ አንችልምና፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን የሚያሰኛትም ይህ ሐዲስ ኪዳንን በብሉይ ኪዳን ላይ ብሉይን ከሥር ሐዲስን በላዩ ማነጽ መቻሏ ነዉ፡፡ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስም ‹‹በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤›› /ኤፌ 2፤ 20/ ሲል እንደገለጸዉ መሠረታችን የነቢያትም የሐዋርያትም ነዉ፡፡ ኦሪትና ነቢያትን ፈጽሞና ተርጉሞ ከሐዲስ ኪዳን ጋር ያገናኘ የማዕዘኑ ራስም እንደተባለዉ ጌታችን ነዉ፡፡ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሉቃስና ቀልዮጳ በእርሱ ትንሣኤ አላምን ብለው ከኢየሩሳሌም ወጥተዉ ወደ ኤማሁስ ሲጓዙ መንገደኛ መስሎ እየተከተለ ኦሪትንና ነቢያትን ተርጎሞላቸዋል፡፡ ወንጌላዊዉ ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው›› /ሉቃ 24፤27/ ሲል እንደገለጸው በርግጥም  ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ግራው ኦሪትን አንተርሷታል፡፡ ቀኙ ወንጌልም አቅፋታለች፡፡ እውነተኛይቱና አንዲቱ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ተጠብቃ ጸንታ ትኖራለች፤ የሰሎሞን ልዩ የዝማሬ ቃልም የሚያስረዳዉ ቤተ ክርስቲያንን ግራው የተባለች አሪትን አንተርሶ ቀኙ በተባለች ወንጌል አቅፎ (በዕቅፉ ዉስጥ አድርጎ) ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቃት ክርስቶስ ነዉ ሲለን ነዉ፡፡ ስለዚህም በነፍስ የዕውቀት ገንዘብ የበለጸጉ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አካልነታቸዉን አውቀዉ በእንደዚህ ያለዉ በዓል ግራህ ከራሴ በታች… እያሉ አሪት የወንጌሉን ባለቤት ሙሽራውን ክርስቶስን ያመሰግኑታል፡፡ እነርሱም ራሳቸዉም የሚኖሩት በክርስቶስ የማዳን ዕቅፍ ዉስጥ ነውና፡፡ ነፍስ ኅርይት ሁሉ ለራሷም ግራ ሥጋዊነትን ከራሴ (ከሃሳቤ) በታች ጥለህልኛልና ቀኝ መንፋሳዊነትንም በትንሣኤህ አጎናጽፈኸኛልና እያለች ታመሰግነዋለች፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ስለ ጥበብም ተገብቶ ግራ ሓሳርና ውርደት( በግራ መቆም) እና ቀኝ የተባለ ክብር ሽልማትም (ቁመተ የማን) ከአንተ ዘንድ ነዉና እያለም ያመሰግናል፡፡ስለዚህም በዓላችን ግራው ፋሲካን ተንተርሣ በቀኝ ትንሣኤ ክርስቶስ ታቅፋ የምትከበር የእውነተኛ ፍቅር በዓላችን ናት ማለት ነዉ፡፡
ክርስቲያኖች ሆይ በዓላችንን በዓለ ፋሲካም በዓለ ትንሣኤም የምንለዉ በእነዚህ በኦሪቱና በሐዲሱ፣ በምሳሌዉና በአማናዊዉ፣ በንባቡና በትረጓሜዉ በአጠቃላይ  በሁለቱም እጆች በግራና በቀኝ የታቀፈችና የተያዘች ስለሆነ ነዉ፡፡ በአይሁድ ፋሲካ የክርስቶስን ማዳን እንደተነገረንና በዚያ በብሉይ የነበሩት አበዉ ሁሉ ሲጠባበቁት እንደኖሩት በክርስቶስ ትንሣኤም ትንሣኤ ሙታንና (የክብርና የውርደት) ዘለለማዊ ሕይወት እንዳለ ተነግሮናል፡፡ ስለዚህም ለራሳችን የክብር ትንሣኤም እየተዘጋጀን በቀኝ ለመቆም እንዲያበቃን እየተማጸንን በደስታና በመንፈሳዊ ሐሴት እናከብረዉ ዘንድ የእርሱ ቸርነት የድንግል እናቱ አማላጂነት አይለየን፤ አሜን፡፡

Tuesday, 29 May 2012

በዓለ መከር(በዓለ ሠዊት)-በዓለ ኀምሳ - ከዲ.ብርሃኑ አድማስ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ


በዓለ መከር(በዓለ ሠዊት)-በዓለ ኀምሳ






በብሉይ ኪዳን ፋሲካ ከተከበረ ከሰባት ሱባኤ (ዐርባ አጠኝ ቀናት ካለፉ) በኋላ በሃምሳኛዉ ቀን በዓለ መከር ወይም በዓለ ሠዊት ይከበራል፡፡/ዘጸ 23፣16 ዘኁ 28፣ 26/ ይህ በዓል ከስሙ እንደምንረዳዉ አማኞች ወይም እሥራኤል ከአዝመራቸዉ ቀድሞ የደረሰዉን (ቀዳምያቱን) ይዘዉ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበትና እርሱንም የሚያመሰግኑበት በዓል ነዉ፡፡ ምሳሌነቱም ከእግዚአብሔር ርቆ ከኖረዉ የሰዉ ዘር የሚጠበቀዉን ቀዳሚ ፍሬ ማመላከት ነበር፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር ከአዳም ዘር ለርሱ የሚሆን ትዉልድን መፈለጉን ያሳይ ነበር ማለት ነዉ፡፡ በዚሁም መሠረት እርሱ ወደ ምድራችን መጥቶ የሰዉን ዘር ለድኅነት በትምህርትና በተአምራት ሲያዘጋጅ ቆየ፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ‹‹አዝመራዉ እንደ ነጣ ዐይናችሁን አንሱና ተመልከቱ››// በማለት ገልጦታል፡፡ጊዜዉ ሲደርስም ድኅነታችን ይፈጽም ዘንድ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፡፡ ፋሲካችን ክርስቶስ ታረደ፤ /1ኛ ቆሮ 5፣7/ ኃይሉንም በትንሣኤዉ ገለጸ፡፡ ይህ በሆነ በኀምሳኛዉ ቀንም መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸዉ፡፡ በዚህም ዕለት ቀድሞ ይከበር የነበረዉ ምሳሌያዊ በዓል አማናዊነቱን አግኝቶ ‹‹የነጣዉ አዝመራ ›› ሲል ጌታ ከገለጸዉ የሰዉ ዘር ቀዳምያቱ ለጌታ ቀረቡለት፡፡ መጽሐፍ እንደሚል‹‹ ከሰማይ በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉት›› /ሐዋ 2፣5/ በዚያ ቀዳምያት ሆነዉ ቀረቡ፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ሀብት ሰማያዊንም ተቀበሉ፡፡ከእነርሱም በኋላ ሌሎች አምስት ሺሕ ሰዎች ተከታይ ቀዳምያት የሁለተኛዉ መሥዋዕት(ከጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበዉ) ሆነዉ እንደ ጥሩ የእህል ቁርባን ለአምላካቸዉ ተሰጡ፡፡ እነዚህ ስምንት ሺህ ነፍሳትም ለአምላካቸዉ የቀረቡ መሥዋዕቶች ስለነበሩ ፈቃደ ሥጋቸዉን ገደሉ፡፡ ስለዚህም ‹‹ ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸዉ፣ ገንዘባቸዉንም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለዉ አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም››/ሐዋ 4፣32/ ተብሎ እንደተጻፈ ሁለንተናቸዉ የእግዚአብሔር ሆነ፡፡ አንድ ሰዉ አንድ ነፍስ (አንድ ፈቃድ) መሆን ባልቻለበት በዚህ ዘመን ብዙዎች ሰዎች ‹‹አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸዉ›› የሚለዉን መረዳትም ሆነ መስማት ምን ያህል ይከብድ ይሆን? በርግጥም ከባድ ነዉ፡፡ ለእነርሱ የተቻለዉ ሁሉም ፈቃደ ሥጋቸዉን ገድለዉ ልቡናቸዉን ለእግዚአብሔር ስለሰጡ በሁሉም ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔር አደረች፤ ስለዚህም በእነርሱ ባደረዉ በአንዱ በእግዚአብሔር አንድ ሆኑ፡፡ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን ቀዳምያቶች እነርሱ ሆኑ፡፡ እነርሱንም ተከትሎ ሌላዉ አዝመራ ተሰበሰበ፡፡ እነ ልድያን ፣ ቆርነሌዎስን፣ የመሰሉ ልቡናቸዉ ለቃለ እግዚአብሔር እና ለእዉነት የተከፈተላቸዉ ሰዎች በየዕለቱ በሐዋርያት አዝመራ ሰብሳቢነት ወደ ወንጌል ጎተራ ይከማቹ ጀመረ፡፡ ‹‹እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ››? /ዮሐ 4፣38/ ሲል ጌታ የተናገረዉም ይፈጸም ጀመረ፡፡ ‹‹ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ››/ሐዋ 5፣14/ ተብሎ እንደተጻፈ የቤተ ክርስቲያን አዝመራ ተከማቸ፡፡ ስለዚህም ከቀዳምያቱ ወደ እህል ቁርባኑ ከዚህም በላይ የመሥዋዕት በግ እየሆኑ ለአምላካቸዉ ቀረቡ፡፡ቤተ ክርስቲያንም በአገልግሎት እየሰፋች በሰማዕትነት እያበበች ቅድስናን እያፈራችና እየሰፋች ሔደች፡፡
የክርስቲያኖች በዓለ ኀምሳም አከባበር በዚሁ ቢቀጥልም እኛ ዘንድ ግን በዚሁ መንፈስ ተጠብቆ አልደረሰም፡፡ ደርሶንማ ቢሆን ኖሮ በዓለ ኀምሳችን እንደዚያ ዘመን ሰዎች ፈቃደ ሥጋችንን ገድለን የመንፈስ ፍሬ አፍርተን ለእግዚአብሔር ቁርባን የሚሆነዉን ቀዳምያት የምናቀርብበት በዓል ሊሆን ይገባዉ ነበር፡፡ ነገር ግን የዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበዉ እንደ ሐዋርያት ያመኑ ምእመናን ነዉ ወይስ ሌላ ብለን ስንጠይቅ ኅሊናችን የሚነግረንን መልስ እናዉቀዋለን፡፡ የሐዋርያት ታዛዦችና በሥራ የሚላላኳቸዉ በጸጋ የከበሩ ሀብተ ፈዉስና ተአምራት የተሰጣቸዉ አርድእትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በእኛ ዘመን ባለችዉ በእኛ ቤተ ክርስቲያንስ? እነዚያ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይማከሩ ነበረ የእኛስ ዘመን መሪዎች ከየትኛዉ መንፈስ ይማከራሉ? የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች በርግጥም እንደ ጥንቱ ሰዉን ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሚያበቁ አባቶችና መምህራን ናቸዉ ወይስ ለገንዘብ፣ ለክብርና ለዝና እንዲሁም ለሌሎች ጥቅሞች የሚራኮቱ ስግብግቦች? በልሳኖች እስኪናገሩ ድረስ በጸጋ የከበሩ አገልጋዮች ወይስ ሁሉንም ነገር ለገነዘብ ማግኛ ሊያዉሉት የሚሯሯጡ ሲሞኖች? በርገጥ አሁን ለክርስቶስ እያቀረብነዉ ያለዉ ምንድን ነዉ? የመንፈስ ፍሬዎችን ወይስ የሥጋ ፍሬዎችን? ሺዎችን አንድ እናደርጋለን ወይስ ጥቂቶቹንም እንከፋፍላለን? ሌሎች የዘሩትን በእነርሱ ተገብተን እንደ ሐዋርያት እናጭዳለን ወይስ የሰበሰቡትንም እንበትናለን? የሚያቀርቡትና የሚያማክሩትስ እነማንን ነዉ? እንደ ጳዉሎስ ሲላስን ወይስ እንደ ባላቅ በለዓምን? እንደ ሐዋርያት እመቤታችንን ወይስ እንደ አክዓብ ኤልዛቤልን?ፈርዖን በዮሴፍ ናቡከደነጾርም በዳንኤል ሲጠቀሙ እነ ሳዖል ወደ ምዋርተኛዋ ሴት መሔዳቸዉ ለምን ይሆን? ወይ ተገላቢጦሽ!!!በርግጥም ያሳስባል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ባወቀ ከኤልያስ እንኳ የተሰወሩ ቅዱሳን እንደነበሩ ሁሉ አሁንም በየ አጥቢያዉ እንደ አልባሌ የሚቆጠሩ እንደ ደንቆሮም የሚታዩ ንጹሐን አገልጋዮች በየገዳሙና በየመናብርቱም አባቶች አይጠፉም፡፡
አብዛኛዉን ስናየዉ ግን በርግጥም ቤተ ክርስቲያን በዓለ ኀምሳን እያከበረች ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡ በዓለ ኀምሳ የፍሬ በዓል እንጂ የገለባ በዓል አይደለም፡፡ የአንድነት እንጂ የመለያየት በዓል አይደለም፡፡ የትሕትናና የጸጋ በዓል እንጂ የዐመጻና የኃጢኣት በዓል አይደለም፡፡ ወንጌልና የምሥራች የሚታወጂበት እነጂ ደባና ተንኮል እንደ ዘሃ የሚዘጉበት በዓል አይደለም፡፡ የቅንነትና የጽድቅ በዓል እንጂ የመሠርይነትና የወንጀል በዓል አይደለም፡፡ እዉነቱን እዉነት ሐሰቱን ሐሰት በሉ ተብለናልና እስኪ በእዉነትና በቅንነት ቤታችንን እንመርምረዉ፡፡በከበረዉ መንፈሳዊ ሀብታችን ማኅሌቱ ቢቆምም ኪዳኑ ተደርሶ ቅደሴዉ ተቀድሶ ብንመለስም የጸጋ ፍንጣሪ ቀርቶ የእርቅ ወሬ አይሰማም፡፡ ከቶ ለምን ይሆን ይህ ሁሉ የሐስትና የአስመሳይነት ሕይዎት እንዲህ የነገሰዉ?
ታዲያ እኛ ያቀረብንለት እሸት የምንድን ነዉ? ‹‹የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ›› /ዘጸ 34፣ 22 / ተብሎ እንደ ተጻፈዉ ስንዴ ነዉ ወይስ ኩርንችት? እኛ እጂ ላይ የሚታየዉ ፍሬ የወይኑ ዘለላ፣ ወይም የገብስ ዛላ ወይም የባቄላ ነዶ ወይስ እሾህና አለብላቢት? ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰዉ የሚዘራዉን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል›› /ገላ 6፣7/ ይላል፡፡ ስለዚህ እኛም ሁላችን የምናጭደዉ የዘራነዉን ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በእዉነት እንዴት ይህን ሁሉ ዐመጻና ጥፋት እናጭዳለን? ይህ የአሁኑ ሌብነትና ዝርፊያ ማንአለብኝነትና ሥርዓት አልበኝነትስ ደግሞ ምን ያፈራልን ይሆን? ለቤተ ክርስቲያን ተቆረቆርን የምንለዉስ ከእዉነት ይሆን ወይስ በሥጋ ገበያ ስለተበለጥን? መጽሐፍ ‹‹ ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ›› /ኤር 4፣ 4/ በማለት ቅናታችን ሥጋዊ ሀሳባችንም ምድራዊ እንዳይሆን፤ ይልቁንም በብልጣብልጥነትና በተጥባበ ነገር ፣ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳሉ በምንላቸዉም መጥፎ ነገር እንኳ ሳንመኝ እንድነፈጽመዉ ያዝዘናል፡፡ ክፉ በምንላቸዉ ሁሉ ላይ ክፉ የምንመኝ አንዳች መጥፎ ነገር በመፈጸም መልካም የሚመጣ የሚመስለን እንዳንኖርም ያሰጋል፡፡ ሐዋርያዉ ‹‹ በገዛ ሥጋዉ የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳል›› /ገላ 6፣8/ እንዳለ መዓቱን እየጨመርን የመከራችንን ዘመን እናረዝመዉ እንደሆን እነጂ ዕርቅና ሰላምን፣ በረከትና ጸጋን ልናገኝ አንችልም፡፡ በተቀመጥንበት ቦታና በሚመስለን ነገር ልናጠቃዉም በምንፈልገዉ ሰዉ ተለያየን እንጂ በክፉ ሀሳብ አልተበላለጥንምም ማለት ነዉ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ለሰዉ ፊት አያዳላምና መቅሰፍቱን በጋራ ያካፍለናል፡፡
እኛ ምእመናኑም ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እነዚያ የጥንቶቹ አማኞች ቀዳምያታቸዉ ምን ነበር? መጽሐፍ ስለ እነርሱ ‹‹ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸዉ›› /ሐዋ 4፣33/ ይላል፤ እኛስ? ፍሬያችንስ ከመንፈስ ነዉ ወይስ ከሥጋ? እስኪ ራሳችንን እንመርምረዉ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነዉ የምንቀርበዉ ምንድን ነዉ? ጥል፣ ክርክር፣ ቁጣ፣ አድመኛነት ወይስ በጎነት፣ የዉሃት ፣ ራስን መግዛት? ወሬና ሐሜት ወይስ ፍቅርና መተሳሰብ? ….. ከቶ ምንድን ነዉ? የመንፍስን ፍሬዎች ወይስ የሥጋን ፍሬዎች? የቤተ ክርስቲያንን ሥራ በእልህና በዐመጻ እሠራለሁ ብሎ መነሣት ለኣማኝ በእሳት እንደ መጫዎት ያለ ነዉ፡፡ በተሳሳተ መንገድና በሥጋዊ ሃሳብ አሸናፊ በመሆን እግዚአብሔርን ለማገልገል መነሣትም አንተ ያሳየኸን መንገድ የተሳሳተ ነዉ ብሎ ጌታን እንደመዉቀስ ያለ ነዉ፡፡ መንፈሳዊ ነገርን በሥጋዊና ግልፍተኛ በሆነ ስሜት ለመሥራት እንደመነሣት ያለም ጎጂ ነገር የለም፡፡ ይህማ ቢቻል ኖሮ ቅዱስ ጴጥሮስ የ ማልኮስን ጆሮ በመቁረጡ አይወቀስም ነበር፡፡ እግዚአብሔርን በጉልበት እናግዝህ ማለት ነዉና እጂግ ጸያፍ ነዉ፡፡ይህን ለሚያደርጉ ‹‹ኃይል የእግዚአብሔር ነዉ እያሉ›› መዘመርም አይቻልም፡፡ ለእኛ ከሚያስፈልገዉ ዉጭ የኃይል እርምጃ የሚያስፈልጋቸዉ ካሉም እግዚአብሔር መንገድ አለዉ፡፡ ሐዋርያዉ ስለ ባለ ሥልጣን ሲጽፍ ‹‹በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቁጣዉን ለማሳየት ክፉ አድራጊዉን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነዉና›› /ሮሜ 7፣4/ ያለዉ ይህንኑ ያመለክታል፡፡
እንግዲህስ እግዚአብሔር ይቀበልልን ዘንድ ሰዉነታችን የተቀደሰ አድርገን እናቅርብ፡፡ በእዉነት ሁላችንም ተመሳሳይ ባንሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ነገር ሊፈጸም አይችልም ነበር፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በዐመፃ ተካከልን፤ በበደልም ተመሳሰልን፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር የሚያስፈርድ ሊገኝ አልቻለምና በሥጋ የዘራነዉን በሥጋ ለማጨድ ተገደድን፡፡ ስለዚህ ፈጥነን እንመለስ፡፡ ልቡናችንን አለስልሰን ፣ ንጹሑን ዘር ቃለ እግዚአብሔርን አብቅለን ለፍሬ እናብቃዉ፡፡ ያን ጊዜ እኛም በዘመነ ሐዋርያት እንደነበሩት ሰዎች ለመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የምንቀርብ ቀዳምያት ለሰማዕትነትም የምንመረጥ ባለመቶዎች ለመሆን እንበቃለን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡