Thursday 5 July 2012

‹‹ብዙ ሃይማት አንዲት ሀገር›› ኢቲቪ የለቀቀው ውዥንብር

  •  982 ነጻ አስተያየት ወደ ኢቲቪ ከደወሉት አስተያየት ሰጪዎች ውስጥ 90 በመቶ ባዩት ነገር የተናደዱ እና የነበሳጩ ሆነው ነገኝተዋል
  • እውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መጤ ነችን?
(አንድ አድርገን ሰኔ 27 ፤ 2004 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ክብር ባህል እምነትና ስርዓት መንግስትና ቋንቋ ያቋቋመች የማትናወጥ ከመሆኗ ጋር ከሔኖክ ፤ ከኖህ ፤ ከመልከ ጼዴቅ ከነብያትና ከሀዋርያት ተላለፈውን ትምህርት ስርዓት ፤ እምነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ የኖረች በማስተላለፍ ላይ ያለች ፎኖተ ህይወት መሆኗ የተረጋጠ ነው፡፡  ቅዱሳን አበውን ፤ ኃያላን ነገስታትን ፤ ልዑላን መሳፍንትን ፤ ክቡራን መኳንንትን ፤ ዐይናሞች ሊቃውንትን በስጋ በነፍስ ወልዳ ያሳደገች የሌላ የማትፈልግ የራሷ የማትለቅ ዕጥፍ እናት ፤ ስንዱ እመቤት ናት፡፡



ከሳምታት በፊት አንድ አማርኛ ፊልም አምባሳደር ሲኒማ አዳራሽ ለመመልከት ችዬ ነበር ፤ ፊልሙ ከስክሪፕት ጽሁፉ ጀምሮ ይህ ነው የሚባል የታሪክ ፍሰት የሌለው ፤  ለሰሪውም ሆነ ለተመልካቹ  ትምህርት የማይሰጥ ፊልም ነበር ፤ በስተመጨረሻ ፊልሙ ተጠናቅቆ ከሲኒማ አዳራሹ ስወጣ የፊልሙን አርእስት ሙሉ በሙሉ መርሳቴ እጅጉን ራሴን አስገርሞኛል ፤ ሰኞ ማታ ኢቲቪ ላይ የተመለከትኩት ወቅታዊ ፊልም አምባሳደር ያየሁትን ፊልም እንዳስታውስ አስገድዶኛል ፤ ወቅታዊ ዘገባው ሲጀምር የክርስትያኖች መገለጫ የሆነውን መስቀልን ፤ የሙስሊሞች መገለጫ የሆነወን ጨረቃና ኮከብን ፤ የአይሁዶች መገለጫ የሆነውን ባለ ስድስት ኮከብ ምስሎችን አንድ ላይ አድርጎ የያዘ ነው፡፡ በመሰረቱ አዚህ ሀገር ውስጥ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ሊኖሩ ይችላሉ ነገር የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን ያህል እንኳ 0.7 በመቶ ቁጥር የላቸውም ፤ የአምልኮ ቦታቸው የት እንደሆነም ሰምቼም ይሁን አይቼ አላውቅም ፤ ታዲያ ለምን ይህን ምስል መጠቀም ፈለጉ ? ፤
የቀረበው ዘገባ በተቻላቸው መጠን ከእስልምና እና ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የእምነት አስተማሪዎችን ማካተት ችለዋል ፤ የታሪክ ምሁራንና መሰል ባለሙያዎችንም ማካተት ችሏል ፤ የቀረበው ፕሮግራም የተሰጠው አርዕስ እና የሄደበት አካሄድ ብዥታን ፈጥሮብናል  ፕሮግራሙ 2፡35 ቢጀመርም እስከ ፕሮግራሙ ፍጻሜ ድረስ ማስተላለፍ የተፈለገው ሃሳብ ከአሁን አሁን ይገባናል እያልን ብንሰማውም ዋና ነጥቡን ማግኝት ተስኖናል ፤

በአሁኑ ሰዓት ግን መንግስት የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ለማቀዝቀዝ ሲል የታሪክን መፋለስ የሚያመጣ ጭብጡን በተገቢው መንገድ ልተገነዘብነውን ዶክመንተሪ ፊልም በኢቲቪ አስተላልፎልናል ፤ ተጀምሮ እስከሚልቅ ድረስ ማስተላለፍ የፈለገውን ሃሳብ በቅጡ መረዳት አቶናል ፤ በአንድ በኩል የታሪክ ምሁር ተብዬ በቅጡ ባለመረዳት በግርድፉ በመተርጎም “እንዴት ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት ልትባል ትችላች?” ብለው ሲተረጉሙ ለእሳቸው ሃሳብ መልስ በሚሆን መልኩ ዲ/ን ብርሀኑ አድማስ የክርስቲያን ደሴት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲተረጉምና ሲያስረዳ እንመለከታለን ፤ ለምን ይህን ነገር ማንሳት ተፈለገ? ፤ በሌላ በኩል ይች ሀገር ላይ ያሉ አማንያን ክርስትያኑም ሆኑ ሙስሊም ማህበረሰቦች ለሀገሪቱ መጤ መሆናቸውን አስረድተው ሲያበቁ ዲ/ን አባይነህ ካሴ በዚህ ጉዳይ እንደማይስማማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰትያ መጤ ልትባል የማትችል መሆኗን ከመልከ ጼዴቅ ጀምሮ ያለውን ታሪኳን ሲያስረዳ ተመልክተናል ፤ በዚች አጋጣሚ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስን እና ዲ/ን አባይነህ ካሴን የመሰሉ መምህሮችን ለቤተክርስቲያን የሰጠን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ 

እኛን ግራ የገባን ነገር ፕሮግራሙ የተዘጋጀበት አላማ ምንድነው ? ፤ የክርስትያኑን ታሪክ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ለማጋጨት ? ወይንስ ነገሮችን በዘመናዊ አይን በመመልከት የሰዎችን እይታ ለህዝቡ ማቅረብ ? ምንም ዘመናዊ ብንሆን መኪና ባልተፈጠረበት ዘመን አይሮፕላን እንደተፈጠረ ማቅረብ መቻል ተገቢ አይደለም ፤ የዶክመንተሪ ፊልሙን ፍሬ ነገሩን እናገኛለን ብለን  ከአንድ ሰዓት በላይ ተቀምጠን ፊልሙን ብንመለከትም በስተመጨረሻ ብንጨምቀው ጠብ የሚል ነገር በማጣታችን አዝነናል ፤ ድንገት እኛ ያየንበት እይታ የጠበቅነው ነገር እና በአሁኑ ሰዓት ያለው ሁኔታ አብሮ ሊሄድልን ባለመቻሉ ከእኛ ችግር ነው በማለት ሰዎች ይህን ፊልም ከተረዱት ብለን ሶስት አራት ቦታ ስልካችንን አንስተን  ብንደውልም ከሁሉም ያገኝነው መልስ ቢኖር የተዘጋጀበት አላማ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት በቅጡ እንዳልገባቸው አስገንዝበውናል ፤ እና መንግስት ምንን ለማስተላለፍ ነው ይህን ነገር ዶክመንተሪ ፊልም ያዘጋጀው ? ፤ 

በአንድ በኩል የሙስሊሙን እይታ ሲገልጽ በሌላ በኩል ደግሞ የክርስትያኑን እይታ ያስቀምጣል ፤ ማንም የፈለገው እምነት የመከተልና ያለመከተል መብት የተሰጠው በንጉሱ ጊዜ ሆኖ ሳለ አሁን ግን መንግስት ያሳየን ፊልም ህዝቦች የማመን መብታቸው የተከበረላቸው ኢህአዴግ ስልጣኑን እንደተረከበ ሆኖ ሲናገሩ ተመልክተናል ፤ በንጉሱ ዘመነ መንግስት ሙስሊሞች ስራ ለመቀጠር ሃይማኖታችሁን ቀይሩ እንደሚባሉም ለመጀመሪያ ጊዜ ሰምተናል ፤ “አስሬ ከመታጠብ አንድ ጊዜ መጠመቅ” የሚል ለተናጋሪውም ሆነ ለሰሚው ጸያፍ የሆነ ነገር ጆሯችን አስተናግዷል ፤ ይህ ከአንዳድ ሰዎች የሰማነው ታሪክ ስለሆነ ለማመመን ትንሽ የምንቸገር ይመስለናል ፤ በንጉሱ ዘመን የነበሩ አንድ አባት የኖሩባቸውን መንግስትታት ኃይለስላሴን ፤ ደርግን ፤ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለህሊናቸው ብለው አነጻጽረው ቢያቀርቡልን የተናገሩትን ለማመን አንቸገርም ነበር ፤ የትኛውም መንግስት ሙሉ ጻድቅ ፤ የትኛውም መንግስት ሙሉ እርኩስ ሊሆን አይችልም ፤ ኢህአዴግ ከደርግ እና ከኃይለስላሴ የሚሻልባቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው ሳለ የሚብስባቸው እና የሚዘቅጥባቸው ነገሮች እንዳሉም መዘንጋት የለብንም ፤ ስናመሰግንም ሆነ ስንነቅፍ መጠንቀቅ አለብን ፤ 

ይች ሀገር ሙስሊም አማኞችን በእንግድነት የተቀበለችው ከ1500 ዓመት በፊት መሆኑ ይታወቃል ፤ አሁን ደግሞ ይህን እውነት እኛም እንሁን እነርሱ ለዚች ሀገር መጻኢ(መጤዎች) ነን ወደ ማለት ተቀይሯል ፤ ይህን ያሉት ግን ሙስሊም ወንድሞቻችን አይደሉም ፤ ይህን ሃሳብ በጥያቄ መልክ ያቀረበው የኢቲቪ ጋዜጠኛ ነው ፤ ታሪክ በቃለ መጠይቅ ይለወጥ የሚመስላቸው ሰዎች ታሪክን ለማደብዘዝ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ ፤ አይደለም ያለፈው ታሪክ ይቅርና አሁን እነርሱ እየሰሩት የሚገኙት ስራ በታሪክ መልክ እንደሚቀመጥ የሚያውቁም አይመስሉም ፤ 

በጣም የገረመን ነገር በነገስታት ጊዜ ሙስሊም ማህበረሰቦች በጣም እንደተጨቆኑ አድርጎ ፕሮግራሙ ላይ በመመልከታችን ነው ፤ እኛ ግን እንላለን አሁንም ይች ሀገር የክርስትያኖች ብቻ ማለት አይደለችም ፤ የክርስትያን ደሴት ማለት ሌላው አይኖርባትም ማለትም አይደለም ፤ ለዚህ ጥያቄ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ በቂ  መልስ የሰጠ ይመስለናል ፤ ባይሆን የዛሬ 50 ዓመት የተፈጠረን ታሪክ ተውትና አሁን የጠየቃችሁትን ጥያቄ ዳር ብታደርሱት መልካም ነው  ፤ በ1923 ዓ.ም ከ80 ዓመት በፊት የተጻፈውን ህገመንግስት መሰረት አድርጎ ለዚያ ነገር ተጠያቂ በሌለበት ሁኔታ ላይ የሌላው የፖለቲካ ግብአት በመሆን  ተጨቁነን ነበር ብሎ መቅረብ መፍትሄ የለው ፤ የዛሬ ጥያቄያችሁ ሳይመለስ  ከ50 ዓመት በኋላ እንደማትደግሙት አሁን ላይ እርግጠኞች ሁኑ ፤ ከተጨቆናችሁም የጨቆናችሁ በጊዜው የነበረው መንግስት እንጂ አሁን ያለችው ቤተክርስትያን አይደለችም ፤ ያለፈውን እንዳለፈ ቆጥራችሁ አሁንስ በዚህ አገዛዝ የእምነት ነጻነታችንን አግኝተናልን? በማለት ራሳችሁን ጠይቁ ፤ 

እኛ ግን በቅርቡ መጽሀፍ ስናገላብጥ ያገኝነው ነገር እናንተ ከምታወሩት ተገላቢጦሽ ሆኖ እግኝተነዋል ፤ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ለመቃኝት በወቅቱ የተጻፉ ጽሁፎችን ማገላበጥ ተገቢ ነው ፤ ከእነዚህ በላይም እማኝ ሊሆን የሚችል ነገር አናገኝም ፤ በጊዜው ስላልነበርን በወቅቱ የተጻፉትን ጽሁፎች ማመን ግድ ይለናል ፤ ከ50 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ቁርአን ከአረብኛ ወደ አማርኛ የማስተርጎም ስራ ሲሰራ ትልቁን ሚና የተጫወቱት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ነበሩ ፤ ከየመስጅዱ ያሉትን በእምቱ ላይ የጠለቀ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በመሰብሰብ ቁርአኑን ወደ አማርኛ እንዲቀየር ባደረጉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና ከእምነቱ መሪዎች በቁርአን የመጀመሪያ ገጽ ላይ ሰፍሮ በመመልከታችን በጣም ተገርመናል ፤ ይህን ነገር እኛ ተመልክተናል ፤ ይህን ጥያቄ የሚያነሱት ሙስሊም ወንድሞቻችን ግን የሚያውቁት አይመስለንም ፤ ኃይለስላሴ በጊዜው ይህን በመስራታቸው ምን ያህል የሃይማኖች እኩልነት እንደገባቸው የሚሳይ ህያው ማስረጃ ነው ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በወቅቱ ያለውን ሃይማኖታዊ ፤ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሁኔታዎችን በመመልት “ሃይማኖት የግል ነው ሀገር የጋራ ነው” ያሉ መሪ ቢኖሩ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ነበሩ ፤ አሁን ግን በጊዜው የተፈጠረው ነገር ወደ ኋላ በማለት ሙስሊሞች ሌላ አለም ውስጥ ገብተው ሌላ ነገር እንዲያስቡ መንግስት እያደረጋቸው ይገኛል ፤ እኛ ሳንናገር አንዳንድ ክርስትያኖች “አንዲት ሀገር አንዲት እምነት” ይላሉ በማለት ስማችንን በአደባባይ ያጠፋል ፤ 

አይደለም ከ50 ዓመት በፊት አሁንም አይኑን ያፈጠጠ ችግር በእምነት ተቋማቶቹ መካከል ተጋርጦባቸው እናያለን ፤ ነገር ግን ይህን ችግር መፍታት ያለባቸው በአሁኑ ወቅት ያሉ የሃይማኖት አባቶች መሆናቸው ማወቅ አለብን፤ አሁን ያልተፈታን ችግር ለትውልድ በማቆየት ተወቃሽ የሚያደርግ ስራ መሰራት የለበትም ፤ መንግስት ከማስማማት ይልቅ ሲጣሉ ማስታረቅ ደስ የሚለው ይመስለናል ፤ ክርስትያን ማህበረሰብ ሙስሊሙን መቶ በመቶ አክራሪ ነው የሚል እይታ የለውም ፤ ከስንዴ መካከል እንክርዳድ እንደማይጠፋው ሁሉ የእምነቱን አስተምህሮ ከሚከተሉ  ሙስሊም አማኞች መካከልም የአክራሪነት መንፈስ የተጠናወተው ሰዎች አይታጡም የሚል እምነት አለን ፡፡   
  
በቅዱስ መጽሀፍ ስለ ቅድስናዋ እግዚአብሔር ደጋግሞ የመሰከረላት አገራችን ኢትዮጵያም ቅድስት ክብርት ሐገር ናት ፡፡ ሰይጣን በእባብ አድሮ አዳምንና ሔዋንን እንደተዋጋቸው ሁሉ በልዩ ልዩ ሥጋውያንና መንፈሳውያን የውጭ ጠላቶች አድሮ ኢትዮጵያን ሲዋጋ ኖሯል፡፡  ዛሬም በመዋጋት ላይ ነው ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ትጥቋን አጥብቃ ከቆመች ሳታርፍ ፤ ከዘረጋች ሳታጥፍ በኖረችበት ዘመን ሁሉ ኢትዮጵያ ሳትደፈር ኖራለች፡፡ በ10ኛው መቶ ዓመት የጉዲት ወረራ ፤ የ16ኛው መቶ ዓመት የግራኝ ወረራ ፤ ከ17ኛው -20ኛው መቶ ዓመት ተደጋግሞ የደረሰው የካቶሊክ ፤ የፕሮቴስታንት ፤ የቱርክና የግብጽ እስላማዊ ወረራ(አክራሪዎች) ተደጋግሞ የከሸፈው ባልተበረዘውና ባልተከለሰው የኢትዮጵያ  ቤተክርስትያን  የእምነት ኃይል ነው፡፡ ይህ ሊታወቅ የሚገባው እውነት ነው ፤ ይችን ቤተክርስትያን ከኢትዮጵያ ጋር እንዴትም መለየት አይቻልም ፤  የአምስት ዓመት የፋሽስት ወረራም ጉዳት ማድረሱ የታወቀ ቢሆንም ከስሩ የተነቀለው ፤ ቁጥቋጦው የተመለመለ ፤ እንደ አንበጣ በዝቶ የመጣው የፋሽስት ሰራዊትም የውሀ ሽታ ሆኖ የቀረው በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የእምነት ኃይልና በልጆቿ ደም ነው፡፡ በጊዜው የቁም ፍትሃት በማድረግ ህዝቡ ለሃገሩ ዘብ ሆኖ እንዲቆም ያደረገችው ይች ቤተክርስቲያን ናት ፤ 

ዛሬ ሁሉ ባለ ሀገር ነኝ በማለት ለአገሪቱ ባለ ውለታ መስሎ ይታይ እንጂ ለ3000 ዓመታት ለኢትዮጵያ ቆማ የኖረች የሰላም ፋና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ብቻ ናት፡፡ ታሪክን መለስ ብለን ስንመለከት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሌላ ሃይማኖት(ካቶሊክ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ፤ ነገስታት ሙስሊም የሆኑበት ጊዜ በታሪክ ስላልተጻፈ) ፤ ከኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሌላ የሃይማት ክፍል ለመሻት ፤ ለመጠጋት ነገስታቱ ወይም ህዝቡ በሞከሩ ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣና ቅጣት አለ፡፡ ሲመለሱ ይመለሳል ፡፡ ይህም ዝንባሌ ከስጋዊ ወገን እንጂ ከኢትዮጵያ ቤተክርስትያን አበው በኩል የታየበት ጊዜ የለም፡፡

የነብያት ፤ የሐዋርያት እምነት ከተሰበከበት ጊዜ ጀምሮ በሐዋርያት ዘመንም ሆነ በተከታታዩ ዘመን በውጭ የታየውና የተነገረው የመናፍቃን ትምህርትና ግብር በኢትዮጵያ የታየበት ጊዜ የለም፡፡ ይልቁንም በ444 ዓመተ ምህረት በኬሌቄዶን በተደረገው ጉባኤ ምክንያት በውግዘት መለያየት ከተደረገ ወዲህ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ከሮምና ከቁስጥንጥንያ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳታደርግ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ኖራለች፡፡ 

በዚህ ዘመን ሁሉ የአበው ስርዓት ሳይፈርስ ፤ ህጉም ውግዘቱም ሳይጣስ ተጠብቆ ኖሯል ፡፡ ልዩ ልዩ የሃይማት ተከታዮች የመንግስት መልዕክተኞች እየሆኑ ጠብ እየቀሰቀሱ ፤ ጦርነት እያስነሱ ቢፈታተኗትም የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን አበው ግን በመስቀልና በሰንደቅ አላማቸው ስር ሆነው ደማቸውን ሲያፈሱ ኖሩ እንጂ የመላላት ግንባር አላሳዩም፡፡ ከዚህም የተነሳ በ1928 ዓ.ም የዘመተው የፋሺስት ሰራዊት ኢትዮጵያን ሲዋጋ ስንቅና ትጥቁን አዘጋጅታ ባርካ ያዘመተችው የልዮን መንበር ስትሆን በዚህም ጦርነት ሁለቱ ታላላቅ አባቶች አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ፤ በደብረ ሊባኖስ ፤ በዝቋላ ፤ በዲማ ፤በዋሸራና በሌሎች አብያተ ክርስትያን ብዙ ካህናትና ምዕመናን መስዋዕት ሆነዋል ፡፡ 

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ከኢትዮጵያ ጋር ለመለያየት በማሰብ መጤዎች ናችሁ የሚል ነገር እየሰማን እንገኛለን ፤ ታሪክን አለማወቅ ከሆነ ወደ ኋላ ዞር ብሎ ታሪክን ማንበብ ተገቢ ነው ፤ ታሪክን አለማወቅ ከሆነም ከሚያውቁት መጠየቅ መልካም ነው ፤ እናንተ ግራ ተጋብታችሁ ህዝቡን ግራ አታጋቡት ፤ ያልተደረገን ነገር እንደተደረገ በማድረግ አታቅርቡልን ፤ አሁን በክርስትያኑም ሆነ በሙስሊሙ መካከል ችግር እንዳለ እናውቃለን ችግሩን የሚሰሙ መፍትሄ የሚያመጡ አባቶችን በማጣት እንጂ የተፈጠረው ችግር የማይፈታ ሆኖ አይደለም ፤ ብዙ ቦታዎች ላይ የክርስትያኑን ቤተክርስትያን አብረው እንደሰሩ ሁላ ክርስትያኑም መስኪዳቸውን የሰራበት አጋጣሚዎች ነበሩ ፤ 

መንግስት ስራው ሊሆን የሚገባው በአማኞቹ መካከል ክፍተት ለመፍጠር የእምነቱ አስተምህሮ ሳይገባቸው አብያተክርስትያናት ላይ ክብሪት የሚለኮሱትን ሰዎች በማደን ፍርድ ፊት ቢያቀርባቸው ያለው ነገር የተፈጠረው ነገር በረገበ ነበር ፤ ይህን ማድረግ ሲገባው ይህን ያደረጉት ሰዎች የኢህአዴግ አባላት ፤ ሰርገው የገቡ ኢማሞች ፤ ከውጭ በብር የሚረዱ ሰዎች እንደሆኑ ደርሶባቸው ሳለ ችግሩን ለህዝቡ ገልጾ ውጤቱን ግን መግለጽ ሲሳነው ተመልክተናል ፤ አሁንም መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው መንግስት ከእምነት ተቋማት ላይ እጁን ሙሉ በሙሉ በማንሳት የጠባቂነት ስራውን ብቻ ይስራ ፤ ለእኩይ አላማ የቆሙትን ሰዎች አጋልጦ ፍርድ ቤት  በማቅረብ ትክክለኛ ቅጣታቸውን ሲያገኙ ለማህበረሰቡ ያሳይ ፤ ሙስሊሙም ሆነ ክርስትያኑ የውስጥ ችግሩን በራሱ አካላት እንዲፈታ ያድርግ ፤ በሁለቱም ወገን ተከሰቱ የተባሉ ችግሮች ህዝብ ፊት በማቅረብ ማህበረሰቡን በማወያየት የመፍትሄ አቅጣጫዎቹን ህዝቡ ራሱ እንዲያመላክት ያድርግ ፤ ያለፉትን መልካም ተሞክሮዎች በመውሰድ የማዳበር ስራ የሃይማኖት አባቶች እንዲሰሩ መንገዱን ያመቻች ፤ ከዘመናት በፊት የተደረጉ የእምነት ነጻነት ገፈፋዎችን ነገ እዳይፈጠሩ የማድረግ ስራ ይስራ ፤ እንደ እስልምና ታሪክ አጥኝው ለዚች ሀገር ኃላፊነት ያለበት በዓለም ላይ ያለው 1.6 ቢሊየን ሙስሊም ማህበረሰብ ሳይሆን እዚው ሀገር ውስጥ የምንገኝ 33 ሚሊየን ኦርቶዶክሳውያን እና 26 ሚሊየን ሙስሊም ማህበረሰብ መሆኑን አንዘንጋ ፤ የውጭ ጣልቃ ግብነትን እስከ አሁን ለሶሪያ ቀውስ ያመጣላት ነገር አለመኖሩን እንመልከት ፤ ሀገሪቱን የሰላም ማድረግ የምንችለው እኛው ነን ፤  ታሪካችን አክብሩልን እኛም ታሪካችሁን እናከብርላችኋለን ፤ ከክርስትስ ልደት በፊት የኦሪት መስዋትን ስታቀርብ የነበረች ቤተክርስትያን መጤ ብሎ ከመናገር እና ከማሰብ ውጪ ምንም የሚያበሳጭ ነገር የለም ፤ ሙስሊሞችን መጤ ናቸው ብለን ያልሆነ ስም አልሰጠናቸውም ፤ ነብዩ መሃመድ ወደ ኢትዮጵያ በላካቸው ጊዜ ለእንግዳ የሚሰጠውን ክብር ሰጥታ የተቀበለች ሃገር ናት ኢትዮጵያ ፤ መንግስት አውቆ ቢያጠፋ ተባባሪው ከመሆን እጃችሁን ሰብስቡ ፤ የሰለሞን ንግስናም ዘመኑ ሲደርስ ተቋጭቷል ፤ ነገ ይህ መንግስት እንዳመጣጡ ይሄዳል ፤ ህዝቦች ግን አብረው ይኖራሉ ፤ አማኞችም ወደፊት ይዘልቃሉ ፤ ዛሬ በሌላው አለም የምናየውም የአንዱ ላንዱ ጥላቻ ለልጆቻችን ለልጆቻችሁ አስቀምጠን ማለፍ የለብንም ፤  ከመንግስት ጎን በመሆን የመንግስት ሁለተኛ ልሳን ሆኖ መናገር ተገቢ አይደለም ፤ 

በስተመጨረሻ የደረሰን ዘገባ እንደሚያስረዳው ይህ ህዝብ ላይ ውዥንብርን የፈጠረን ፊልም ከተመለከቱት 90 በመቶ የሚሆኑት  በጣም የተናደዱ ስሜታቸውን መቆጣጠር ያቃታቸውን ሰዎች 982 ላይ በመደወል ቀኑን ሙሉ ኢቲቪ ላይ የስድብ ውርጅብኝ ሲያወርዱ እንደዋሉ ከቦታው የደረሰን ታማኝ ምንጭ ገልጾልናል  ፤ በቅርብ ጊዜ የህዝቡ አስተያየት በማለት ጥሩ ጥሩውን መርጠው ብቻ ለማቅረብ ደፋ ቀና እያሉም መሆኑን ተነግሮናል ፤ በተጨማሪ በክፍለ ከተማ እና በቀበሌ ደረጃ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ የፌደራል ጉዳዮች መስሪያ ቤት እና የአቶ በረከት ስምኦን ቢሮ አብረው እየሰሩ መሆኑንም ጭምር ለማወቅ ችለናል፡፡
ቸር ሰንብቱ

No comments:

Post a Comment