Sunday, 3 November 2013

ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

ሰሞኑን በተለይ በርከት ባሉት በመጽሐፈ ገጽ ወዳጆቼ በኩል  ‹‹ ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው? ›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኛል፡፡ በተሐድሶዎች በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል ፤ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል ፤ በድርሳነ ራጉኤል ላይ ደግሞ ራጉኤል አዳናቸው ተብሎ ስለተገለጸ ትክክሉ የቱ ነው፤ በርግጥ ያዳናቸውስ ማን ነው የሚል ነው፡፡ በዚያም ጊዜ ሆነ ዛሬ ከአንዳንዶቹ መልእክት እንደተረዳሁት የድንጋጤ ስሜትም የተሰማቸው አሉ፡፡ ይህን ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችንም ስመለከት ለጉዳዩ ቢያንስ አንዲት ትንሽ መጣጥፍ እንዳአቅሜ  እንኳ ለጊዜው መስጠት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ጥያቄውን ለላካችሁልኝ ሁሉ ይህችን መቆያ እንካችሁ ብያለሁ፡፡ ዋናው ወይን ሁልጊዜም ወደ ኋላ መምጣቱ አይቀርምና እርሱን አብረን ከወይን አዳዩ እንጠብቃለን፡፡

ከላይ ያነሣሁትንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የሚረብሹን ለምንድን ነው ብየ ሳስብ ብዙዎቻችን ወግ ባለውና ለእኛ በሚሆን መንገድ አለመማራችን የመጀመሪያውን ስፍራ ሊይዝ ይችላል፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  ደግሞ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንመለከተውን የመሰሉ ጥያቄዎች እያነሡ ገድላትን፤ ድርሳናትንና ሌሎች አዋልድንም የሚነቅፉና የሚያጸይፉ ሰዎች ቁጥራቸው በርከት እያለ መጥቷል፡፡ ከዚህም የተነሣ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ወድምፅ ስብከቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚህም ስለቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ወይም ምሥጢራት ግንዛቤያችን አነስተኛ የሆነብንን ሰዎች በትንሹም ቢሆን ሊረብሸን ይችላል፡፡እኔም ዝም ብየ በአንዲት ብጣሽ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲህ ነው ወይም እንዲያ ነው ከማለቴ በፊት ነገሩን ከመሠረቱ ለመረዳት እንዲያመቸን ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን የማንጠየቃቸውንም በአግባቡ ተረድተን እንድንጠቀም የሚረዳውን መንገድ ጠቆም ላድርግ፡፡ ስለዚህ አስቀድመን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት ልንረዳ እንደምንችል ላቅርብና በሚቀርበው ጥያቄ ሁሉ ሳንረበሽ መልሱን እንድንጠብቅ ለማመላከት ልሞክር፡፡