Wednesday, 2 April 2014

የጎልማሶችና ወጣቶች ማኅበራት ኅብረቱ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር መዘጋጀቱን አስታወቀ፤ በወጣቶቹ ዝግጅት የተደናገጡ የለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞች የኅብረቱን እንቅስቃሴና አመራሮቻቸውን በሽብር ለመወንጀል እያሤሩ ነው

ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ሕገ ወጥ ተግባራት መካከል÷ ያልተፈቀደላቸው ሰባክያን ስምሪትና የኅትመት ውጤቶቻቸው ሽያጭና ስርጭት፣ የአስመሳይ ባሕታውያንና መነኰሳት ነውረኛ ድርጊቶች፣ ሕገ ወጥ ልመና፣ የአጥቢያ አስተዳደር ሙስናና የወጣት ሱሰኝነት ይገኙበታል፡፡
ማዕተብ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በተለይም ወጣቱ ከሱስ ነጻ መኾን አለበት፤ መስቀሉን አንጠልጥሎ በየባንኮኒውና በየዳንኪራው ከመታየት መጠበቅ አለበት፤ ዶግማውን፣ ቀኖናውንና ትውፊቱን ያወቀና የጠነቀቀ፣ በኢኮኖሚያዊና ፋይናንሳዊ አቅሙም ጠንካራና እርስ በርሱ መደጋገፍ ይገባዋል፡፡
102 ያኽል ማኅበራት አንድነት የፈጠሩበትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አቅራቢነት የቅ/ሲኖዶሱን ዕውቅና ያገኘው ኅብረቱ ከ150,000 በላይ አባላት አሉት፡፡ የኅብረቱ አመራሮችና አባላት፣ ወቅቱ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነትና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በፍቅር እስከ መጨረሻው የምንቆምበት ነው ብለዋል፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን ተጨንቃ ትጣራለች፤ የምትጣራው ወጣቱን ነው፤ ወጣት ዕውቀትና ጉልበት አለው፤ እኔ ሴቷን ጨምሮ ኹላችን እያንዳንዳችን ሓላፊነት አለብን፤ ወይ ግዴታችሁን ተወጡ ወይ ውረዱ የምንልበት ወቅት ነው!!›› /የማኅበራት ኅብረቱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን/

(ኢትዮ – ምኅዳር፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፷፪፤ መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

የይሁዳ ክህደት ለ30 ዲናር፣ የእነዚህ ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳንን ሀብት ለመዝረፍ

(ደጀ ሰላም፣ መጋቢት 22/2006 ዓ.ም፤ ማርች 31/2014. PDF)፦ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ሰጠው። ምህሩንና ጌታውን ክዶ፣ ስሞ ለግርፋት እና ለመስቀል ሞት ተስማማ። ይህንን የጌታን ሕማማት፣ ስቅላት፣ ሞትና ትንሣኤ በምናስብበት በአሁኑ ወቅት ማኅበረ ቅዱሳንን ለሕማም፣ ለስቅላት እና ለሞት አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገው ትርምስ ተጀምሯል። ይሁዳ ለ30 ዶላር እነዚህ የዘመናችን ሰቃልያን ደግሞ “ማኅበሩ ያፈራውን ሀብት በሙሉ ለመዝረፍ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል። በዚህም በዚያም ክህደት እና ስቅለት።