ገብረ ኪዳን
የፓትርያርክ ጳውሎስን ሞት ተከትሎ ፣ ታዋቂው ደራሲና ሰባኪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ለምጣዱ ሲባል አይጧን ” በሚል ርእስ ፣ አጭር ግን ጠንካራ መልእክት ለመላው ኢትዮጵያውያን አስተላልፎ ነበር ።
የጽሁፉም ዋና ጭብጥ አንድና ግልጽ ነው— ለቤተ ክርስትያኒቱ ክብር ሲባል ለተወሰኑ ቀናት ስለፓትርያርኩ ክፉ ስራና ደካማ ጎኖች የሚያትቱ ጽሁፎችምሆነ ውይይቶች አንዲዘገዩ “ የሚማጸን ነበር ። ለቤተ ክርስትያኗ ክብር ሲባል መራሄ ቤተ ክህነቱ አቡነ ጳውሎስ ከበቂ በላይ የሀዘን ( ይገባቸዋል ብዬ ባላምንም) ስርአት ተካሂዷል ። እነሆ አሁን በዘመናቸው ስለተከናወኑ አሰቃቂና አስጸያፊ ወንጀሎች እናውሳ።
ሟች ፓትርያርክ ጳውሎስ ይወቀሱበትና ይከሰሱበት የነበሩት ወንጀሎች ብዙ ናቸው። በሃይማኖት ጉዳይ አለቃ አያሌው በመፍቀሬ ካቶሊክነት ሲወቅሷቸው ፣ አቡነ አብርሃምና ሌሎች በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ጥንተ አብሶን በተመለከተ ፓትርያርኩ በመመረቂያ ጽሁፋቸው ላይ በጻፉት ኢ – ኦርቶዶሳዊ ትምህርት አንቀው ይዘዋቸው ነበር። በገንዘብ አባካኝነትና በሙስና ሲወቀሱ የነበሩት ፓትርያርክ ጳውሎስ ፣ ህይወታቸው ሲያልፍ በዘመዶቻቸው አካውንት አስከፍተው ያስቀመጡት 22 ሚሊዮን ብር መገኘቱ በሙስና የሚቀርብባቸውን ወቀሳ እውነተኛነት ያመላክታል። ሌሎችም ብዙ መረጃና ማስረጃ የተገኘባቸው ክፉ ስራ ቢኖራቸውም እኔ ግን የትኩረት ነጥቤ የሳቸውን ስልጣን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ በምስጢር የተገደሉትን የሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን ህይወት ይመለከታል።