..... ተወለደ ............
ሰማያትን አለማገር አቆመ
የአብ ቃል ከሰማይ ቀደመ
አቢይ ..
ደቂቅ ወረቂቅ ….. በሱ ተፈጠረ
"ሰውን እንስራ" ሲሉ ሲል ነበረ!
ያ 'እፍ' ያለበት የእጁ ሥራ
አዳልጦት .. ከገደል ሲጣራ
"ኦ አምላክየ.... ስለምን ረሳኸኝ?
እሳት በዝቶብኝ ሲቆላ አሳረረኝ!”
ቃል ጠባቂ ……. ቃል መጣ ከሰማይ
ከድንግል ሰው ሆኖ ድኅነቱን ሊያሳይ
የአዳም ፈገግታ ፈገግታዬ
.......... ፌሽታው ፌሽታዬ
በለስ ገምጬ...
የሸፈንሁት ጥርሴ ........... ዛሬ ተሰነነ
የሰለጠነብኝ .. የሰየጠነብኝ የሱ ተከደነ
ከጥልቁ...
ግልገሉን ሊያወጣ ….. ቃል ሥጋ ሆነ!
ሰውን ወዷልና...
በክብር ያሸበረቀ ውርደቱን ተመኘ
ዙፋን 'ማይወስነው በግርግም ተገኘ
.............. ባለውለታዬ ..............
.................. =//= .................
በልዑል ገ/እግዚአብሄር
(ታህሳስ27/2005ዓ.ም.)
…………. ስንቅነሽ …………
ጠዘጠዝ ተብዬ ፣ካለም ተገፍቼ፣
የማታ ሹመቴን፣ በጧት ተቀምቼ፣
ዱካዬን ወልውዬ፣ ሌላ ዓለም ልዘውር፣
መጣፉን ቀድቼ ፣ቃሉን ልወረውር፣
ሆዴ ባዶ ቢሆን፣ በስደት ፈለጌ፣
ውስጤ ሲርገበገብ፣ በዋይታ በርግጌ ፣
ለሰው አይን ባልሞላ፣ቢያሰለኝ ማጣቴ፣
በረከት የሞላው ፣ቋርፌ ነሽ ህይወቴ፤
በበረሃው ስደት፣ ከክፋት አምልጬ፣
አዲሲቱን መንግስት ፣ልዋረስ ቋምጬ፣
ጦር ሰብቆ ሲፎክር፣ ያ ’መንገድ ደንቃራ፣
በግርማሽ ደንግጦ ፣‘ሚክሎል’ ሆነሽ ፈራ፤
በእሾህ ላይ ልራመድ፣ኃይልን ተጫምቼ፣
ስደቱን ልድፈረው ፣ ስምሽን ተመክቼ፣
ማር ፍቅርሽ ቀለቤ ፣ ውዳሴሽ ሙዳዬ
ከወይኑ እርሻ ልግባ፣ “ሰአሊ ለነ” ብዬ፤
ውሃን አልደነብቅ፣ ባ’ሩሩ ተበልጦ ፣
መናን አልቀፈድድ፣ ጀርባዬ ተልጦ፣
ጧቱን አጥግቦ፣ ተሰ’ያት ንቆ የጣለኝ ፣
ሆዴን ክጄዋለሁ ፣ስምሽ ስንቅ ይሁነኝ፤
………………. =//= …………..….
በልዑል ገ/እግዚአብሄር
(መጋቢት21/2005ዓ.ም.)
*መፍቻ:-
'ጠዘጠዝ': የማይሞላለት.. ተንከራታች
'ቋርፍ': የመናኝ ምግብ
'ሚክሎል': የአርበኛ ጌጥ
'ደነበቀ': አብዝቶ ቀዳ
**ልጅሽ ልጅ ተብሎ**
በደስታሽ…
ከመሶብሽ ቆርሶ
ከወጭትሽ ጠቅሶ
ከማድጋሽ ተጎንጭቶ
ከመደብሽ ተኝቶ
… እንዳልኖረ
በሐዘንሽ…
እንባሽን በእጁ ካላበሰ
የሐዘንሽን ምሬት ካልቀመሰ
ከማጣትሽ ማጣት ነሥቶ
ከረሐብሽ ማዕድ ካልቆረሰ
ምነዋ ከጽንሱ በጨነገፈ
ምነዋ ሳይፈጠር ባረፈ
ምነዋ ሳይወለድ በቀረ
ውሀ ሆኖ በፈሠሠ።
በልዑል ገ/እግዚአብሄር
.... በእንተ አርሴማ ……
የጥበብ ንድፍ መለዮ ደምግባትሽ…
አይቶ በማይጠግብ በንጉስ ቀልዋጭ አይኖች ተፈተነ
…ሀብት ገንዘብ ሰይፍ እሳት አማርጦ ከፊት ተደቀነ!
አንቺ ብርቱ…
ውበት ንግድ አልሆነሽ ንጉስ ማማለያ
መልክን በረብጣ ቀይሮ…
የባለጠጋ ናት መባል ፍቅር ማስመሰያ!
ወጣትነት አልረታሽ!
ከጦምና ከራቡ…….….መብል ማመላለስ
ከድንጋይ ባዶ እግሩ ምንጣፍ መመላለስ
አማን አማን……..ሰማዕታት ይህን ዓለም ናቁ
ስለ እግዚአብሔር መንግስት…
ደማቸው ፈሶ ስለ ስሙ አጥንታቸውን አደቀቁ!
አፍላነት እሳት ነው እንኳ ገዢ ታክሎበት
ያቺ መልከ መልካም……...ተለየች
ከአላፊ ከእዳፊ ዘላለሙን መረጠች
እንደ ጣይ ማብራቱ
………ደመና ላይ መውጣቱ ሐቀኛ ውበት!
አንገትሽ….
ወርቅ ብር አወዳድሮ……….በሀብል አላጌጠ
ስለ ክርስቶስ ሰንሰለት ሰይፉን መርጦ
……………………..….ሞቶ መዳኑን መረጠ!
አርሴማ….
የአትኖስያና ኮከብ በአርመን ከፍ ከፍ አለች
ልዕልናዋ በዓለም መልቶ
……..……የቴዎድሮስ ፍሬ በሰማይ አበራች !
ያንቺ ሞትሽ ሰይፍ ምትራትሽ እልፍ ህይወት ዘራ
ቃሉ ፍፁም ነውና…
ያ አዶናይ ቃልን ሰጥቶሽ ባመኑብሽ በልጆችሽ በራ!
ሂድልኝ እስኪ…
ለካ ወጣት ሆኖ የእሳት ልብስ ይወለቃል
በሥልጣነ ነፍስ ተቀጥቶ
በጠሎት በጦም ተመትቶ
እውነት ሲያዝ በበረዶ ብርድም ይሞቃል!
ያቺ ቅድስት….ፀረ አጋንንት…
ዙፋን…ሽቱ…ምንጣፍ…….…..ቤቱን ናቀች
በዱር ከትማ
ቀን ሌት ቆማ
ሰው የመሆኗ ትርጉም መጠራቷን አወቀች!
ከእንግዲህ…
………....ሰይፍ የመዘዙ በሰይፍ ያልቃሉ
ቅጣት ለበዳይ
ባነደዱት እሳት በሳቡት ወላፈን ይፈጃሉ!
እኔማ….. እኔ ምን አለኝ እናቴ?
ነግህ ሰርክ ሀጢኣት በርትቼ ሰርቼ
…………………….……….ያ’ጢያት ባለጠጋ ሆኛለሁ
ግና…
በነጻ ቃልኪዳንሽን አምኜ በስምሽ ውሃ አጠጥቻለሁ
ደጅሽን ተሳልሜ …....…‘’በእንተ አርሴማ’’ ብያለሁ!
ምን በጎ አለኝ…?
ስለ አንቺነትሽ ስለከፋው ስቃይሽ
ስለፈሰሰው ደምሽ
……..ነፍሴን አደራ ጥቁረቷን ያጥፋልኝ
የጠራሁት ስምሽ የሰማሁት ገድልሽ
………………………ዋስ ጠበቃ ይሁነኝ
……………………………ከእሳቱ ያድነኝ!
……………………….. ያድነን አደራ!!! ..................
…………………..…………...=//=…….……………………
በልዑል ገ/እግዚአብሄር
በልዑል ገ/እግዚአብሄር
(መስከረም29/2005ዓ.ም.)
* * * በእንተ ማርያም * * *
የምርቃት ካባ ፣ በስውር ደርቤ፣
የጀግና ቀበቶ ፣ በቀጭን ወገቤ ፣
አረንቋ የበዛበት ፣የተራራው ግርጌ ፣
እሾኅ ሲጎትተኝ ፣ ልቀርብሽ ፈልጌ፣
የተኩላ ጩኸቱ ፣ ያንበሳው መንጋጋ፣
......................... 'ዳልቀርብ አንቺ ጋ፤
የጅቦቹ መንጋ ፣ .... መንገድ የዘመቱ፣
የሰው ሥጋ በልተው ፣ጥጋብ ያመረቱ ፤
ተራራው ሥር ወድቀው፤
በሆድ ቁንጣን አልቀው፤
የተራራው አናት ፣ልምላሜ ውበቱ፣
የሰማይ ዝማሬ ፣....... መና ማኅሌቱ፣
የቁልቁሊት ሳየው...
ያ ረዥም እሾኁ ፣ .... ተዳፋት ዳገቱ፣
በርምጃ የቀለለኝ ፣ኃይልና ጉልበቱ፣
የተራራው አናት፣............. ምስጢር ስጦታዬ፣
መንገዴን ስጀምር፣ "በእንተ ማርያም" ብዬ፤
.......................... ቀለለኝ! ..........................
* * * * * * * * =//= * * * * * * * *
good
ReplyDelete