በታደሰ ወርቁ ከፌስ ቡክ ገጹ ላይ የተወሰደ
ቋማዊ ለውጥ (Institutional Reform) የተቋማዊ ቀውስ መድኀን የመሆኑን ያህል ፤ውጤታማ ያለመሆኑም ተግብሮት የተቋማዊ ውድቀት አመክንዮም ነው፡፡የተቋማዊ ውድቀቱ አመክንዮም ተቋሙ ከቆመለት መሠረታዊ ግብ-ዓላማ-ተልእኮ ጋራ ሰለሚቆራኝ ክትያው ተቋማዊ ቁመናን አሳጥቶ የታሪክ ሽታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ እንይኖረው ያደርጋል ፡፡ ከአምስተኛው ፓትርያርክ ሞት በኃላ በተቋማዊ ለውጥ ጅምሮች ላይ ተስፋ ያደርግነው በአንድ ጀንበር የቤ ተክህነቱ ተቋማዊ የሞራል ዝቅጠት ፈውስ ያገኛል በሚል ሳይሆን የተቋማዊ ውድቀትን አመክንዮ ተግብሮት ቀድሞ ከመረዳት ነው፡፡ከዚህ አኳያ በቤተ ክህነቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር መምጣት ያለበት ተቋማዊ ለውጥ በሁለት ዳርቻዎች ሊጠቃለል ይችላል፡፡በመጠን ለውጥ (Quantitative Change)እና በዐይነት ለውጥ (Qualitative Change)፡፡
ባለፈው ዕትም በዚሁ ርዕስ ከአምስተኛው ፓትርያርከ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎሰ ሞት በኃላ ተስፋ ያደርግነው በድዩስጶራነት በሚኖሩ አባቶች እና በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል ሲደረግ የነበረው የእርቀ ሰላም ድርድር እንዴት እና በምን መልክ እንደመከነ በዝርዝር ተመልክተናል፡፡በዚህ ዕትም የምንመለከታቸው ሁለት የመከኑ ተስፋዎችና ተግብሮታዊ ክትያዎቻቸውን እነሆ፡፡የተቋማዊ ለውጥ ጅምሮች!
የትኛውም ለውጥ በመጠን ለውጥ ላይ የተመሠረተ ወይም ከሱ እንደሚመነጭ የለውጥ ኀልዩት ያስረዳል፡፡ከቤተ ክህነቱ አኳያ የመጠን ለውጥ መምጣት አለበት ሲባል ቤተ ክርሰቲያኒቱ የመሠረተ እምነት ፣የሥርዐት አምልኮና ትውፊት ለውጥ ሳታደርግ ፤እነዚህኑ ተቋማዊ ዓምዶቿን ከኢትዮጵያውያን መጠነ ክበብ ወደ ቀረውም ዓለም ማስፋትየሚያስችሏትን ፖሊስዎች፣ስትራቴጂዎችና መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን መፍጠር አለበት ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረትነት በመሠረተ እምነቷ፣በሥርዐተ አምልኮዋና በትውፊቷ ላይ ቅሰጣ የሚፈጽሙትን ቡድኖችና ግለሰቦች አውግዞ መለየት የሚያስችል ብቁና ፈጣን ድርጅታዊ ድርጁነት መፍጠር መቻልም የመጠን ለውጥ አንዱ ዘርፍ ነው፡፡