የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣይ ዘመናት የሚመራውን አባት የመምረጡ ታላቅ ሥራ ቅዱስ ሲኖዶሱን ከገጠሙት የዘመናችን ተግዳሮቶች ዋናው ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮ ከተግዳሮቶቹ ሁሉ ዋናው የሚያደርጉት አራት ምክንያቶች ናቸው፡፡
የመጀመርያው በአራተኛውና በአምስተኛው ፓትርያርኮች መካከል በተደረገው ሽግግር በተፈጠሩ ወቅታዊና ቀኖናዊ ጉዳዮች ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ‹ሲኖዶሶችን› ያስተናገደችበት ዘመን ላይ የሚደረግ ምርጫ መሆኑ ነው፡፡ በሀገር ቤትና በውጭ ባሉት አባቶች መካከል እየተከናወነ ባለው የዕርቀ ሰላም ሂደት ውስጥ ዛሬም በሕይወት ያሉት የአራተኛው ፓትርያርክ ዕጣ ፈንታ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላማዊና መንፈሳዊ ብሎም ቀኖናዊ ጉዞ የሚወስነው ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድም አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበር ትመልሳለች፣ ያለበለዚያም አራተኛውን በጸሎት ወስና በእንደራሴ ትቀጥላለች፣ ያለበለዚያም ስድስተኛውን ትመርጣለች፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኅብረተሰቡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በንቃትና በቅርበት በሚከታተልበት ጊዜ የሚከናወን ሂደት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉት የፓትርያርክ ምርጫዎች የሕዝብን በቂ ክትትል ለማግኘት ዕድል አልነበራቸውም፡፡ በአንድ በኩል የመገናኛ አውታሮች እንደልባቸው ያለመሆን፣ በሌላም በኩል ሕዝባችን አስቀድሶ ከመሄድ ባለፈ የቤተ ክህነቱን ጉዳይ ለቤተ ክህነት ሰዎች ብቻ የተወበት ዘመን ስለነበር ምርጫዎቹ የሕዝብን በቂ ትኩረት አላገኙም ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የስብከተ ወንጌል መስፋፋቱና የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚዘግቡ ሚዲያዎች መብዛት የፓትርያርክ ምርጫው ጉዳይ ትኩረት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ በመረጃ መረብ እንኳን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚዘግቡ 26 ብሎጎችና ከስድስት በላይ ድረ ገጾች አሉ፡፡