Wednesday, 30 October 2013

የሌለውን ፍለጋ -ክፍል አንድ

በዳንኤል ክብረት


አቡነ ተክለ ሃይማኖትና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ( ጎርጎራ፣ ደብረ ሲና ማርያም)

ተስፋየ ገብረ አብ ‹የስደተኛው ማስተዋሻ› የተሰኘ መጽሐፍ ማውጣቱንና ባነበው መልካም እንደሆነ ገልጦ አንድ ወዳጄ ‹ስስ ቅጅውን› ከሀገረ አሜሪካ ላከልኝ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች መጻሕፍቱን አንብቤያቸዋለሁ፤ በአጻጻፍ ችሎታው የምደሰተውን ያህል እንደ አበሻ መድኃኒት ነገሩን ሁሉ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ምስጢር ስለሚያደርገው፤ በአንዳንድ ጉዳዮችም ሆን ብሎም ሊያናጋቸው የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ያሉ ስለሚመስለኝ፤ ተስፋዬ ለምን እንደዚህ ይጽፋል? እያልኩ የምጠይቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡

በዚህ መጽሐፉ ውስጥም ያንን ጥርጣሬየን አጉልቶ ሥጋ ነሥቶ እንዳየው የሚያደርገኝ ነገር ገጠመኝ፡፡ ተስፋየ በገጽ 306 ላይ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ› በሚል ርእስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የማያውቀውን ነገር ጽፏል፡፡ ስለማያውቀው ነገር የጻፈው ባለማወቁ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አንድም ለማወቅ ባለመፈለጉ፣ አለያም ሆን ብሎ የማፍረስ ዓላማ ይዞ ይመስለኛል፡፡
ይህን የምለው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለመጻፍ ሲፈልግ ሊያነባቸው የሚችላቸው መጻሕፍት በምድረ አውሮፓ እንደ ማክዶናልድ በዝተው ሞልተው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ኤንሪኮ ቼሩሊ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔቶች ታሪክ(Gli Abbati di Dabra Libanos, 1945)፣ ኮንቲ ሮሲኒ ከሐተታ ጋር ያሳተመውን ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣በዋልድባ ቅጅ (Il Gadla Takla Haimanot secondo la redazione Waldebbana, 1896)፣ የዊልያም በጅን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወትና ተአምር (The Life and Miracles of Takla Haymanot, 1906)፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጸሐፍትም ውስጥ የታደሰ ታምራትንChurch and State in Ethiopia, ማንበብ በተገባው ነበር፡፡