ከታምራት ፍሰሃ
በአገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ት/ት ተቋም ተማሪወችን አሰባስቦ ስላስተማረ ፡ ብዛት ያላቸውን በግእዝ የተፃፉ መፃህፍትን ተርጉሞ ፡ ለወጣቱ የሚጠቅሙና የሚያንፁ መፃህፍትን አሳትሞ ስላቀረበ ፡ እጅግ የበዙ ገዳማትን አድባራትን ስለረዳ ፡ የአብነት ተማሪወችና አስተማሪወች ራሳቸውን እንዲችሉ እጅግ ብዙ ፕሮጄክቶችን ቀርፆ በተግባር ስላዋለ ፡ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትን ስላሳነፀ ፡ ብዙ ሺህ ኢአማንያንን በፈቃዳቸው አስተምሮ እንዲጠመቁ ስላስተባበረ ፡ የካህናት ማሰልጠኛወች በየቦታው እንዲቋቋሙ ስላስተባበረ ፡ አፅራረ ቤተክርስቲያንን ነቅቶ ስለጠበቀ ፡ የመናፍቃንን ክፉ አላማ ለሁሉ ዘወትር ግልፅ ስላደረገ ፡ ቤተክርስቲያንን ከተሃድሶወች ስለተከላከለ ፡ የክርስቶስን ወንጌል በየገጠሪቷ ክፍል እየዞረ ስላስተላለፈ ፡ ወጣቶች በነፃ ያለምንም ክፍያ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ አርአያ ስለሆነና ስላስቻለ ፡ በጣም ርቀው የነበሩ ክርስቲያኖችን አቅርቦ ለቤተክርስቲያን በሙያቸው እንዲያገለግሉ ስላስተባበረ ፦አክራሪ ከተባለ እንግዲህ እኔም አክራሪ ልባል እወዳለሁ!!!
ከሙስና መራቅ ፡ ሃገርን መውደድ ፡ ቤተክርስቲያንን ማወቅ ፡ ክርስቶስን ማምለክ አክራሪ ካስባለ እኔም አክራሪ ተብየ እንድከሰስ እወዳለሁ!!!
ቦንብ ሳልወረውር ቦንብ የሚወረዉሩትን አስቀድሜ አይቼ ወገኖቼን እንዳያጠፉ ማሳሰቢያ መስጠቴ አክራሪ ካስባለኝ ፡ እንዲህ ያለ አክራሪነቴን እወደዋለሁ!!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ትክክል ናት ፡ ክርስቶስም መሰረቷ ነው ፡ ድንግል ማርያምም ክብሯ ናት ማለት አክራሪ ካስባለ ፡ አክራሪ ተብሎ መሞት ክብር ነው!!!
ክርስቶስን በካደ ትውልድ መካከል ፡ በዲያቢሎስ በምትደምቅ አለም ለመዋብ በሚቋምጥ ሰው መካከል እውነት እውሽት መስላ መወቀሷ ፡ ውሽትና ክፋትም ከሚሰሯት ጋር መከበሯ የሚጠበቅ ነው፡፡
ዲያቢሎስ የተጣባት ክርስቶስ የራቃት ህሊና ፦ የገደላትን እየሾመች የሞተላትን መጥላቷ የሚጠበቅ ነው፡፡
ነገር ግን ፦ እኛ ከዚህ ህብረት አለመሆናችን ይታወቅ ዘንድ : አንድም እውነት ስለሆነው ስለጌታችን ስለክርስቶስ ምስክርነት ከእውነት ጎን እንቆማለን፡፡
ማቴ 5፡11 “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።”