- አቶ መለስ ዜናዊና አቦይ ጸሀዬ ከደርግ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ገዳማውያን አባቶች የመነኮሳትን ልብስ በማልበስ ከሞት አድነዋቸዋል፡፡(ደርሶ ጡት ነካሽ ቢሆኑም)
- ‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ ዶ/ር አረጋዊ
- ‹‹መንግሥት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር››አቡነ ማትያስ
- ፓትርያርኩ የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ ዕንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ሥራቸውንእያስተጓጎሉባቸው እንደኾነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለኹ፤ ስተኛ ደግሞ እረሳዋለሁ››በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል፡፡
- ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ይመለከታል›› በሚል ርእስ ለደኅንነቱ ዋና መሥ/ቤት የተላከ ደብዳቤ…(ያንቡት)
- ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን ‹እናንተ የጸጥታ ስጋት አለ› ብላችሁ በደብዳቤ ሓላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛምለካህናቱ ለምእመናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልጻለን›› አቡነ እስጢፋኖስ መዋቅራዊ ጥናቱ ይቁም በማለት ለመጣ የመንግሥት ካድሬ ሰጡት መልስ…
(አንድ አድርገን መጋቢት 21 ዓ.ም 2006 ዓ.ም)፡-ይህ ጽሑፍ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት›› በሚል የቀረበ ሲሆን ‹አንድ አድርገን› የተሰጠው አርዕሱን ብቻ በመቀየር የጸሐፊውን ሙሉ ጽሑፉን እንደወረደ ለአንባቢያን አንዲህ አቅርበዋለች፡፡ ጽሑፉ እንዲህ ቀርቧል ፤ ሌላውን ነገር ለአንባቢ ትተናል…
‹‹ማኅበረ ወያኔ››
በኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራው መንግሥት ከናቅፋእስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አውሮፕላን፣ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥቢደበድብም በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውንእያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምራት ኾነውበታል፡፡የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጭ›› ቤዝ-ዓምባው በተወሰነ መልኩም ቢኾን ለጥቃት የመጋለጥ ዕድሉ አናሳ በኾነውየሳህል በርሓ በመኾኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያ አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፣በርካታ ክፉ ቀናትን ካሳለፉባቸው ቦታዎች መካከል በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትናእምነት ገዳማት ውስጥ መደበቅ እንደሆነና በየስፍራው መዘዋወር ሲፈልጉም ራሳቸውን ከሚሰውሩባቸውዘዴዎች ውስጥ በቀሳውስቱና መነኰሳቱ አልባሳት መጠቀም አንዱ እንደነበር በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናትያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ ፤ ኣባይ ፀሃዬ ፤ ግደይ ዘርአጽዮን ስዩም መስፍን ፤ ስብሀት ነጋንየመሳሰሉ የአመራር አባላቱ የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ከዚሁ ጋር ተየይዞ የሚነገር ታሪክ አለ ፤ የመንግሥት ጸጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›. መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ከመነኮሳት ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸውን መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡ ይህን መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረዥሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባባው በማሸሽ ይታደጓቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊና አቦይ ጸሀዬ ነበሩ፡፡ በእርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ ዕድል ህይወታቸውን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱ በጓሮ በር ወደ ዙንባብዌ ሸኝተን በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጦ ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል ፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡
‹‹ማኅበረ ቅዱሳን››
መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችንሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግሥጋሴ ሲያፋጥኑ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢነት፣ በደኅንነት ሠራተኞችና በኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነትትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴ የጦር ማሠልጠኛከተቱ፤ ዩኒቨርስቲውም ተዘጋ፡፡
…………ከመላው ዘማቾች አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰብስበው ሲያበቁ በየቀኑ በካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኝው ሚካኤል ቤተክርስቲያን በመሄድ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በጸሎት መማጸን የህይወታቸው አካል አደረጉት ፡፡ ከቀናት በኋላ በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትምስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል እሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው የሰየሙትን የጽዋ ማኅበርመሠረቱ፡፡…ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም. በ‹ፓዌ መተከል› ዞን የተደረገውንየ‹መልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ቅዱሳን ከሚዘከሩባቸውሌሎች የጽዋ ማኅበራት ጋር በመዋሐድ የዛሬውን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበትየነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡
ሃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይኾን ለሥልጣን እርካብመወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ“The Origin of TPLF” በሚል ርእስ ሠርቶት ኋላ ወደ መጽሐፍ በቀየረው የጥናት ጽሑፉ ላይ ‹‹የቤተክርስቲያኗ ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሃት ነጋ የሚመራ የስለያ ቡድን ተቋቋመ፡፡ይህ ቡድንም ደብረ ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኰሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱንእንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ሥር የማስገዛት ሥራ ሠርቷል›› ሲል በገጽ 317 ላይ ገልጧል፡፡ ድርጅቱ ሙሉበሙሉ ሃይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሣበትን ገፊ ምክንያትም እንዲህ በማለት አብራርቷል፡-
‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊንቃት(ማንነት) ማስተማርያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ ዕንቅፋት እንደነበረች ግልጽ ነው፡፡ስለዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ሥር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሣም የእርስዋንተጽዕኖ ለማግለል ጥልቅ ርምጃ ወስደዋል፡፡›› (ገጽ 315 – 316)
ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ ርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፈረንስበማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያን ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይብሔርተኝነት ስር ማካተት›› እንደነበረ በዚሁ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያህል የምንደነግጠው፣ ዶክተሩ ከዚሁ ጋራ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሣሣውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ተጽዕኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊመረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢሆን ሐሳብ የተቃኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱን በመሪነትና ሐሳብ በማዋጣትከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖሊቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡
የሆነው ሆኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም. ድረስ ባሠለጠናቸው ካድሬ ‹‹ካህናት›› አማካይነት ‹‹ነጻ በወጡ››መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ ክህነት አስተዳደር (ኖዶስ የተገነጠለ) መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱለእኒዚህ ቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ ዓሥርቱ ትእዛዛት በፍጹምልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡ እንዲህዓይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምና ላይም መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙባቸውአካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የሆኑ ታጋዮችን እየመረጠና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንምሐሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደሆነ በመግለጽ የፕሮፓጋንዳ ሥራይሠራ ነበር፡፡ በዚህ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዳንድ ዓረብ አገራትን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህደግሞ ከዓረቦቹ በገፍ ርዳታ ያጎረፈለት ሲኾን ወደ መሃል አገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡
ከመንግሥት ለውጥ በኋላም ሁለቱንም እምነቶች የተቆጣጠረው በታጋይና ምልምል ‹ካህናት› እና ‹ሼኾች›ለመኾኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ የሆነው ጠቅላይ ቤተ ክህነትውስጥ ከሚገኙ አሥራ ስምንት መምሪያዎች ውስጥ አሥራ ስድስት በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱበተሳካ ኹኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡ በተለይ ዋነኛው ሰው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሲኖዶሱን ብቻበሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉበተደጋጋሚ መደመጣቸው እና አንዳንድ ጳጳሳት ተቃውሞ በሰነዘሩባቸው ቁጥር ‹‹መንግሥት ያግዘኛል ብዬነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭሲመልሱ መስተዋላቸው ለሥርዓቱ ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ሦስትወር የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው የሠሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ሁልጊዜ ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብእርሳቸው(ፓትርያርኩ) ‹መንግሥት እንዲህ አለ›፤ ‹መንግሥት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ››በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል(በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ ዕንቅልፍየማብዛትና መሰል ችግሮች ሥራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደኾነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝእተኛለኹ፤ ስተኛ ደግሞ እረሳዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል፡፡)
በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቀድሞው መጅሊስ የባሰ እንደሆነ በርካታ ሙስሊምምዕመናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዝዳንቶችሲሆን፣ ይህች ዓይነቱ ጫዎታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመኾኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱሼኽ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ ምእመናኑን ቀጥቅጠውሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር እንደሚደፍሩ የቅርብ ሰዎቻቸውይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታጋይ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሼኽ ኪያር መሐመድከእኚኹ ታጋይ ምክትላቸው ጋራ በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸውና ‹‹መንግሥት የሚያዘውንሁሉ ለመሥራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከ ማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡከሓላፊነታቸው ሊነሡ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡
ኢሕአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ ገበያው››
ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎየመንቀሳቀሱ መግፍኤ ከሦስት ጉዳዮች አንጻር በአዲስ መሥመር ለመተንተን እሞክራለሁ፡-
የመጀመሪያው÷ ቤተ ክህነት በነገሥታቱ ዘመን የነበራትን ፖሊቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳ ራሱኢሕአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ሆነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠርቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማኅበራዊ ተቀባይነት ባላቸው ሼኾች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ሲቀሰቅስበተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናን ይኹንየደርጉን ሁሉንም ሃይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራርአባል የነበሩት አቶ ገብሩ ኣስራት እንደ ሼኾች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱንብዙኃኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚኽ ዘመንም በአብያተ እምነቶች ካድሬ ጳጳሳትንና ካድሬ ሼኾችንአሰርጎ የማስገባቱ ምሥጢር ይኸው ነው፡፡
እንደ ኹለተኛ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው÷ የታገለለትን ዘውግ ተኰር ፖሊቲካ ያለአንዳችተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሃይማኖቶች ‹‹የሰው ልጆችበሙሉ የአንድ አምላ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመኾናቸው አኳያ፣ ማንነታቸውንበዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚኽም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ‹መንፈሳውያን› በየእምነቱ ተቋማቱ እንዲፈለፈሉና ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን መቆጣጠር እንዲችሉበማብቃት ላይ የተመሠረተ ብቻ መኾኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡ይህ ‹ዕውቀታቸው›ምይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስና በሥነ ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፣ እንዲሁምበእምነት አቋማቸው በተከታዮች ዘንድ ተኣማኒና ቅቡል ያልኾኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከ ማድረግያደረሳቸው፡፡ የራሳቸው የስለላ መዋቅርም ጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም. ‹‹ለዋናው መሥሪያ ቤት፣ አዲስአበባ፤ ከ-ል.ዮ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስንይመለከታል›› በሚል ርእስ ለደኅንነቱ ዋና መሥ/ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲኽ ሲል ገልጾታል፡-
‹‹ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመሆናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠለጠለ ኾኗል፡፡›› ከዚህ ሪፖርት በኋላም እንኳ በቀጣዩ ሢመት ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገደድናል፡፡
3 . ገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሦስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለውምክንያት፣ ምንም እንኳ ተሳክቷል ሊባል ባይቻልም፣ በሥነ ምግባር መታነፅ፣ በአገር አንድነት ማመን፣ለሕዝብ ጥቅም መቆም፣ የትኛውንም ሕገ ወጥነት ለምን ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችንመርሑ አድርጎ የሚነሣ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ አድርጎ እየሠራ ያለውን ሤራ ነው ብዬአስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የሥርዓቱ ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት የጭቆና ቀንበርለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደኾነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡ከዚሁ ጋራ አንሥተን ማለፍያለብን ጭብጥ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵዊ ብሔርተኝነት ጋራ የሚያያዝ ነው ፤ የሃይማኖቱናየማእከላዊ መንግሥቱ የቅድመ – አብዮቱ ጋብቻ (በምንም ዓይነት መከራከርያ ልንሟገትለት ባንችልም)ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም‹የሃይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ሆኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ሃይማኖቱ ተቋማዊ ነጻነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ኹሉ ሲያደርግ፣ ሃይማኖቱን በማዳከምየብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡
ገደል አፋፍ የቆመው ማኅበረ ቅዱሳን…
ሥርዓቱ የሃይማኖት ተቋማቱንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ ምክንያቶች ኾነውታል ብዬ ከላይለማብራራት የሞከርኋቸውን ሦስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረጉበት፣ በቀጥታበምእመናኑ የተመሠረቱ ማኅበራት መኾናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያኽል ከኦርቶዶክስ ክርስትና –ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከእስልምና ያለፉትን ኹለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ኾኖ የተመረጠው ኮሚቴአባላት መንግሥትንም ኾነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ይሁንና የሙስሊሙንተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ኾነ መሰል ማኅበራት ጠንካራ እንደኾነየሚነገርለትን ማኅበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ዒላማ አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማኅበሩ አባላትበዓለማዊ/ዘመናዊ ዕውቀት የተራቀቁ፣ በሀገራዊ አንድነት ፈጽሞ የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ…የመኾናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬአስባለኹ፡፡
በርግጥ በአቶ መለስ ይዘጋጅ እንደነበር ከኅልፈቱ በኋላ በይፋ በተነገረለት የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት– አዲስ ራዕይ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖሊቲከኞች፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴትናት፤ አንድ ሃይማኖት አንድ ሀገር እና ሙስሊም ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደልበማራገብና በመቀስቀስ፣ ከዚኽም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎች በማቅረብ ለማነሣሣትናለማተረማመስ ሲሠሩ ማየት የተለመደ ሆኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ በድፍን ፍረጃ ዘልሎ መንፈሳውንማኅበራትን በስም ጠቅሶ ያወገዘባቸው አጋጣሚዎች ብዙም አልነበሩም፡፡ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሃይማኖታዊየመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይኹን ማኅበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ኾኗል፡፡ ከውግዘትምተሻግሮ ጥያቄዎቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያናሥቅየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈጸም ጉዳዩን በጠመንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡
‹‹ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?›› በሚል ከስድስት ወራት በፊት በዚኹ መጽሔት ላይለማተት እንደሞከርኁት ኹሉ፣ ከላይ በተዘረዘሩ የፖሊቲካ አጀንዳዎችና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደውንሀገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ዓለማዊይኹን መንፈሳዊ ነጻ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ያለው የእነ ኣባይ –በረከት መንግሥት፣ በአኹኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ይህን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍጹም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱበርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያኽል አንዱን በአዲስ መሥመር ላቅርብ፡-
ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎእንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ አገልጋዩና ምእመኑ እንዲወያይበት ሲኖዶሱ በሰጠውአቅጣጫ መሠረት ከኹሉም አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ 2700 ሰዎች የተሳተፉበትና በድምሩ አስራ አራትቀናት የፈጀ ውይይት ይጠራል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ አማካይነትበተመራውና ጥናቱን በሠራው የባለሞያ ቡድን ፈጻሚነት የተከናወነው ውይይት ሲካሔድ በነበረባቸውበመጨረሻዎቹ ሳምንታት በአንዱ ቀን ‹ከአንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ አጋጥሟል›መባሉን ተከትሎ በሊቀ ጳጳሱና በፓትርያርኩ መካከል የሚከተለው ውዝግብ መካሔዱን ሰምቻለኹ፡-
ፓትርያርኩ፡- ‹‹ጥናቱን የሚሠሩት ባለሞያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
አቡነ እስጢፋኖስ ፡- ‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሞያዎች ናቸው የሠሩት››
‹‹አይደለም! የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተውየመጡ ሞያቸውን ዓሥራት ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍጹም ጥናቱ የማኅበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢኾንስ፣ ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግሥት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሣሉና የጸጥታ ስጋት አለ››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሡት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለምእንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሐሳቡን ይግለጽ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሔ ይኾናል? ደግሞስሲኖዶሱ አይደለም ሰነዱ ወደ ታች ወርዶ ይተችበት ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››
….. የስልክ ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን ቢሮ ድረስ መጥቶ፣ ትእዛዙንያስተላለፈውን አካል ገልጾ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን ‹እናንተየጸጥታ ስጋት አለ› ብላችሁ በደብዳቤ ሓላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱ ለምእመናኑ ሁኔታውንዘርዝረን እንገልጻለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ ውይይቱ ይቋረጥ እንግዲህ ለጊዜው ግልጽ ባልሆነ አንድ ምክንያት መንግስት ‹‹ይቋረጥ›› የሚለውን ማስፈራሪያ ማንሳት ያቻለው፡፡ ኩነቱግን ፓትርያርኩ ማኅበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና በአገዛዙ ለሚወሰድበት ማንኛውም ርምጃ ተባባሪመኾናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ሌላው መንግሥትና ፓትርያርኩ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሠሩ መኾናቸውንየሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና ያወጡትንየአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በተመለከተ ያወጡት የአቋም መግለጫ ፤ የዋንኛ የመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር ፤ የማኅበሩ ሒሳብ መንግሥት በሚመድበው የውጭ ኦዲተር ይመርመር ፤ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን( ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተክህነቱ ይዘዋወሩ፡፡ የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት ፤ ሬስቶራንቶቹ ፤ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻ እና ማከፋፈያውን) ያስረክብ ፤ ከምዕመናን በቀጥጣም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል ፤ የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርጸው ትምህርት እንዳይወስዱ መስራት ፤ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅ ተነስቶ ፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን… ›› የሚሉ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ከዚህ ሤራ ጀርባ በተቀረፀው ድምፅ ላይ ፓትርያርኩና መንግሥት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው ፣ የተቃዋሚዎቹ አስተባባሪ መሰብሰቢያ አዳራሹን ለመጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፈቃድ እንደኾነ ከመግለጽ በዘለለ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ ተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም ፤ አይዟችኹ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም እንጂ ካስወጡን መንግሥታችን ቸር ስለኾነ ከእርሱ ቦታ ተቀብለን የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች ማኅበር እንመሠርታለን›› እስከ ማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋራ ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ ተመስገን ቀጥሎም በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተቀሰቀሱት 169 አድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሰራተኞች ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አዝማችነትበማኅበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በጥናት ስም በተከታታይ የሚወጡና በየመድረኩ የሚቀርቡወረቀቶች ማኅበሩን የኦርቶዶክስ አክራሪ ከማለት አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ›› ሲሉይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእኒህ ‹ጥናት› ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማኅበሩ የትምክህተኞች ምሽግ ነው፤ አክራሪነት አለበት ፤ አመራሩና ሕትመት ውጤቶቹ የፖለቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል ፤ በቤተ ክርስቲያንአስተዳደር ጣልቃ ይገባል፤ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሠራል፤ በውጭ ጽንፈኛ የፖሊቲካኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡የማኅበሩ አመራሮች እንዲህ ዓይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜከአቶ በረከት ስምዖን እስከ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፣ ከአዲስ አበባ የጸጥታ ሓላፊዎች እስከ ጠቅላይሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ ፀጋይ በርሄ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላውተቀባይነት ያለው ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት እንደኾነ ቢያስረዱም መፍትሔ እንዳላገኙ ምንጮችተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግሥት ተቋማት ያሉ የፋክት መጽሔት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወርከሚካሔደው የሲኖዶሱ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በፊት፣ ከኻያ የሚበልጡ የማኅበሩ አመራሮችን ከሽብርተኝነትጋራ በማያያዝ ለመክሰስና ማኅበሩንም እንደተለመደው በዶኩመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ከሶስት ሳምንት በፊት በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ዶ/ር ሽፈራው አቡኑን ቃል በቃል እንደነገራቸው የተሰማው ነገር ይህን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-
‹‹በማኅበረ ቅዱሳን አመራር ውስጥ ከሃያ በላይ የተቋዋሚ አባላት አሉ››
‹‹ለዚህ ምንድነው ነው ማስረጃህ? አቅርበው እስኪ እንየው?››
በሀገር ውስጥ ካሉ ጽንፈኛ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአመራርነት አሉበት (የሁለቱን ሰዎችን ስም ጠቅሷል)
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማኅበሩ በእንዲህ አይነት ተግባር ራቀ ነው ፤ እናንተ ማስረጃ አለን ካላችሁ አቅርቡና እንየው ፤ ከዚህ ውጪ ይህን አይነት ክስ አንቀበልም..››
በአናቱም የግንባሩ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት የማኅበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትንና ለምን? ብለውየሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለጽ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማኅበሩ ዕጣ ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናትላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡-
‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጠብጥ ለመፍጠር፣ በኦርቶዶክሶችና ሌሎችሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህት ኃይሎችቅሪቶች ናቸው፡፡ እኒኽ የትምክኽት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሃይማኖትንበፖሊቲካ ዓላማ ዙሪያ ብቻ መጠቀሚያ አድርገው እየሠሩ ለመኾናቸው ከ97 ምርጫ በኋላአንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባትነት ካባቸውንእንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ኹነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› (አዲስራዕይ፤ ሐምሌ – ነሐሴ 2005 ዓ.ም.)
የኾነው ኾኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማኅበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት ዕቅዶች ማኅበሩ መሠረቱን ከጣለበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ከመከልከልና አባላት ከማለያየት፣ ንብረቶቹን ከመውረስ ጋራ የሚያያዙ ናቸው፡፡ (ከላይ የተመለከተው የተቃዋሚዎች የአቋም መግለጫም ለማኅበሩ የደም ሥር ለኾኑት እኒኽ ኹለት ጉዳዮች ትኩረት የሰጠ መኾኑን ልብ ይሏል)
ስቅለትን ለተቃውሞ
ኢሕአዴግ ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን በመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይርምጃዎች›› በሚል ርእስ ለካድሬዎች በበተነው ድርሳን (በአቶ መለስ እንደተዘጋጀ ይገመታል)፣ ይህን አሁንየተነጋገርንበትን ሃይማኖታዊ ተቋማትን ለሚያቅዳቸው ሥልጣንን የማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳበኋላ ተቋማቱን ለሥርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደኾነ ያሠምርበታል፡፡ ይህ የማይቻልከኾነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳውያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሃይማኖቶቹን መምራትየአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መኾን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልጽ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ከመጅሊሱ እስከማኅበረ ቅዱሳን ያየነው መንግሥታዊ አፈና የዚህን ሃያ ዓመት የሞላው የተጻፈ ሐሳብ መተግበርን ነው፡፡
ግና፤ ከዚኽ ቀደም በተጻፈ ነውረኛ ሐሳብ ትግበራ ፊት ከኹለት ዐሥርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋውማኅበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኋቸው አሳማኝ መረጃዎችና ተጨባጭ ኹነቶች በተከታታይ መከሠትመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ መነሣት የሚኖርበትአስቸጋሪ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማኅበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲኾን ምላሾቹም ሁለትናቸው፡፡ የመጀመሪያው የማህበሩ አመራሮችና አባላት እስከዚች ቀን እያደረጉ ያለው የውስጥ ለውስጥ የእርምት እንቅስቃሴ ይመለከታል፡፡ በሃይማኖቱ ተቋማት በኩል ለዓመታት ሲሞከር የቆየው ይህው አማራጭ እንደ አስተዋልነው ማኅበሩን ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ስለዚህም ወደ ሁለተኛውና ዋንኛ መፍትሄሔ አማራጭ መሻገር ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ስጽፍ ለማስረዳት እንደሞከርኩት የማኅበሩ አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ማኅበራቸውን ብቻ ሳይሆን ሕልውናቸውንና ህያውነታቸውን የመሰረቱበትን ሐይማኖት ለማውደም የሚተጋውን ስርዓት በሰላማዊ አመጽ መናድ ብቸኛው የዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መሸጋገሪያ መንገድ ነው፡፡ በዋናነት የተማሩ ከተሜ ወጣቶችን በአለማዊ ሆነ በትምህርተ ሃይማኖቱ የማይታሙ ዜጎችን የያዘው ይህ ማኅበር ፊቱ በተገተረው ኢህአዴግ ላይ በሕጋዊ እና ሰላማዊ እምቢተኝነት ከማመጽ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖረው የሚረዳ ይመስለኛል፡፡
‹‹ችግሮች ሁሉ የየራሳቸው በጎ ገጾች አሏቸው›› እንዲሉ፣ ማኅበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚታሰበው የስቅለት ቀን ነው፡፡የሃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተክርስቲያኒ የሚውሉበት ይህ በዓል ፤ አገዛዙ እጁን ከማኅበሩ ላይ እንዲያነሳ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን መሆኑን ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኹለተኛና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩን የ2007 ዓ.ም. ምርጫን ነው፡፡ ለየትኞቹ የሕገ መንግስት ሃሳቦች አልያም የሞራል እሴቶች የማይገዛው ኢህአዴግ ፤ በሃይማኖቱ ላይም ሆነ በማኅበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሕዝባዊ አመጽ መሆኑን እስከመተማመን ድረስ ፤ ከዓመታዊ የንግስ በዓላት ጀምሮ ያሉ መድረኮችን በእቅድ ለመጠቀም የዝግጅቱ ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፤ ካነሳው ርዕሰ ጉዳይ አኳያ የማኅበሩን መኖር የሚሹ ሁሉ ቀጣዩን የምርጫ ወቅት ለማስገደጃነት የመጠቀም ተመክሮዎቻቸውን ተፈላጊው ብቃት ላይ እንደሚያደርሰው አምናለሁ፡፡ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ አባላቱ የምርጫውን ተጨማጭ እድል መንግሥታዊ ተቋማት በማሽመድመድ ጭምር እንዴት ስርዓቱን ወደ መቃብሩ ማሻገር እንደሚያውቁ ስንገነዘብ ፤ ቀሪው ጉዳይ ‹‹ሃይማኖታችሁን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳን መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግሥት የመታመን ብቻ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ይህ ጽሁፍ ያለ ምንም ማስተካከያ ቀርቧል
No comments:
Post a Comment