December 11, 2013
፩. የቤተ ክርስቲያን ምንነት፣ ዓላማና ተልእኮዎች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው በአጭር ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ አካል ስትሆን፣ አማንያን ደግሞ የተለያዩ የአካል ክፍሎቿ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለቤቷና መሥራቿ እግዚአብሔር ሲሆን ከእግዚአብሔር ጋር መንፈሳዊ ኅብረትና ግንኙነት ያላቸው መንፈሳውያን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ አንድ ሰው በሃይማኖትና በምሥጢራት አማካይነት ወደዚህች ጉባኤ ሲገባ የዚህ ጉባኤ (ኅብረት) አካል ሆኖ ይሠራል፡፡ ሐዋርያው “ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው” በማለት ያስረዳው ይህን ነው፡፡ 1 ቆሮ. 1፡9 እንዲሁም “ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም” የሚለው ቃል ይህን የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እሳቤ ያሳያል። ኤፌ. 2፡19-22 ይህች እግዚአብሔር የመሠረታት ጉባኤ (ማኅበር) ቀዳማዊት ናት፤ “ተዘከር ማኅበረከ ዘአቅደምከ ፈጢረ - አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን አስብ” ያለው ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 73፡2
የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መሠረት ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ ሃይማኖት ደግሞ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አንድና ብቸኛ እውነት ነው፡፡ ሐዋርያው “ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት እንዴት መኖር እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው” ያለው ለዚህ ነው፡፡ 1 ጢሞ. 3፡15 ይህ የቤተ ክርስቲያን አምዷ (ምሰሶዋ) የሆነው እውነትና ሃይማኖት ካልተጠበቀ ወይም ችላ ከተባለና እግዚአብሔር ከገለጠው እውነት ጋር እንሸቃቅጠው ከተባለ ቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋ ስለማይፈቅድላት እንዲህ ያለ ነገር መቀበል አትችልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረቷ እና ዓምዷእውነት ነውና፡፡