(ምንጭ፡አዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ ቅጽ 7፣ ቁጥር 153፣ የካቲት 2005)
በአሁኑ ጊዜ ‹‹ፍቅር››ን የማይጠራው አለ ለማለት አይቻልም፡፡ አፍቃሪ -ተፈቃሪው፣ አጣይ-አፋቃሪው ፣ ሸምጋይ አስታራቂው፣ የሥነ ልቡና ባለሙያው፣ ጸሐፊ ደራሲው፣ አንባቢ ተርጓሚው፣ ሃይማኖት ሰባኪው፣ ልጅ አዋቂው፣ ከተሜ ገጠሬው ፣...ሁሉም ፍቅር ፍቅር ይላል፡፡ የሁሉም ፍቅር ግን አንድ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ‹‹ አምላክ›› የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ሁሉ ‹‹ አምላክ›› በምንለው አካል እንደምንለያየው ማለት ነው፡፡ ለምን ቀናሽ? ለምን ገደልህ? ለምን ከሳህ?ለምን ታመምሽ? ለምን ተጣላህ?... ለሚሉት ድኅረ ፈተና ወመከራ ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ መልሳቸው ‹‹ ስለ ምወደው! ስለምወዳት!›› የሚለውነው፡፡ ይኸ የገረማቸውም እረ ለመሆኑ ‹‹ፍቅር›› ራሱ ምንድን ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በርግጥም ፍቅር ራሱ ምንድን ነው?