- ባለፉት 20 ዓመታት በወር በአማካይ 28 ቤተክርስትያኖችን አቡነ ጳውሎስ እንዳሰሩ ይገልጻል (በ20 ዓመት 6800 ቤተክርስትያናት ተስርተዋል ይለናል)
(አንድ አድርገን ሐምሌ ሚካኤል ፤ 2004 ዓ.ም)፡- አንጸባራቂዎቹ 20 ዓመታትን በማስመልከት በጠቅላይ ቤተክህት አንድ መጽሀፍ ተዘጋጅቶ ነበር ፤ ይህን የአቡነ ጳውሎስን ገድል የሚተርክ መጽሀፍ ለማሳተም በርካታ ሺህ ብሮች እንደወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ፤ የመጽሀፉ አዘጋጆች ምዕመኑ በብር ግዛ ቢባል እንደማይገዛ በማወቃቸው በሺህ የሚቆጠሩ መጻህፍትን በነጻ ሲያድሉ ተመልክተናል ፤ ሐምሌ 5/2004 ዓ.ም አራት ኪሎ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ከመንግስት የተጋበዙ ባለስልጣኖች ፤ የውጭ ጥቂት ዲፕሎማቶች ፤ ፈቅደው ሳይሆን ከየደብሩ የመጡ ካህናትና መዘምራን ፤ ብዛት ያላቸው ጳጳሳት የተገኙበት ስርዓት ነበር፡፡ ምዕመኑ ከ150 የማይበልጥ ሲሆን አብዛኛው ቦታውን የያዙት ተጋባዥ እንግዶች ነበሩ ፤ መሀል ላይ ያለው 10 ሜትር የሚያህል ቦታ ዳር ዳር የቆሙት ምዕመናን ለመታዘብ እንጂ በዓለ ሲመታቸውን ለማክበር የመጡ አይመስሉም ፤ የቅድስት ስላሴ የፊት ለፊቱ ደረጃ በቅጡ በምዕመኑ መሙላት አቅቶት አስተውለናል ፤ አቡነ ጳውሎስ በስተቀኝ እነ ተስፋዬ ውብሸትን ከበስተኋላ ዲፕሎማቶችን ፤ ከበስተቀኝ ደግሞ ሊቃነ ጳጳሳትን አስቀምጠው መሀል ቁጭ ብለዋል፤ በነጻ የሚታደለውን መጽሀፍ በግራ እና በቀኝ የሚያድሉ ሰዎች ተሰማርተው ሰው እጅ ላይ የማድረስ ስራቸውን ተያይዘውታል ፤ ፕሮግራም መሪው የአቡነ ጳውሎስን ፤ የተጋባዥ የመንግስት ባለስልጣናትን ፤ አምባሳደሮችን ስም ሲጠራ ለሰማ ምንድነው ይህ ሁሉ የመዓረግ ጋጋታ ማለቱ አይቀርም ፤የነሱ ስምና መዓረጋቸው ብቻ ከአንድ ገጽ ቢበልጥ እንጂ አያንስም ፤ የሚነበበውን ነገር ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጥ ሰው ማግኝት መታደል ይመስላል ፤ ማን እንደሚያነብ ስለምን እንደሚነበብ ፤ የጽሁፉ መልዕክትና ይዘት የነበረው እንግዳ ቢጠይቁ ከመቶ አምስቱ አይመልስሎትም ፤ በጣም አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ሰው እስከ 5 ገጽ ያነበበበትም ጊዜ ነበር ፤ አቡነ ጳውሎስ አስከ አሁን የሰሩት ወይም ወደፊት የሚሰሩት ስራ አሳስቧቸው ነው መሰል እርሳቸውም ንግግሩን በአጽንዎ እየተከታተሉ አይደሉም ፤ ታዲያ ይህ በዓለ ሲመት ለማነው የተዘጋጀው? የሚያስብል ሁኔታን ይመለከታሉ ፤ እኛ እንኳን የመጣነው 4 ኪሎ ስላሴ ቤተክርስትያን ግቢ ውስጥ እንደ ቦሌው ሌላ ሃውልት ካቆሙ ሃውልቱን ለማፍረስ እንጂ መርሀ ግብሩን ለመሳተፍ አልነበረም ፤ ማን ያውቃል ሀውልቱን እንደማይደግሙት ?