በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
አንድ ገዳም ዉስጥ የሚኖሩ አንድ አባት አዉቃለሁ፡፡ እኝህ አባት ሁል ጊዜ የሚናገሩት በምሳሌና በተዘዋዋሪ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለእርሳቸዉ እንግዳ የሆነ ሰዉ ነገራቸዉን ቶሎ ላይረዳዉ ይችላል፡፡ በአንድ ወቅት ከጓደኛየ ጋር ሆነን ስለ ምጽዋት ስናነጋግራቸዉ በአሁኑ ጊዜ ከጠቃሚነቱ ይልቅ ጎጂነቱ ያመዝናል የሚለዉ ሰዉ እንደሚበዛና በርግጥም ይህን ሊያስብሉ የሚችሉ ብዙ አጭበርባሪዎች መኖራቸዉን ነገርናቸዉ፡፡ እርሳቸዉም ዝም ብለዉ ካደመጡን በኋላ የሚከተለዉን ታሪክ ነገሩን፡፡ በንጉሡ ጊዜ ፈረንጆች መጥተዉ አንድ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጥያቄዉም ጥቁር ነገር ለዓለማችን ጠቃሚ ስላልሆነ ከምድር ልናጠፋዉ እንፈልጋለን፤ የእርሰዎ ሃሳብ ምንድን ነዉ? የሚል ነበር፡፡ እርሳቸዉም ጎጂማ ከሆነ መጥፋት ይኖርበታል፤ ግን ጎጂነቱን አረጋግጣችኋል? ደግሞስ ምንም ሳታስቀሩ ሁሉንም ልታስወግዱ ቆርጣችሁ ተነስታችኋል ? ሲሉ ጠየቛቸዉ፡፡ እነርሱም አዎን ፤ ጥቁር ነገር ለሥልጣኔና ለመልካም ነገር እንደማይስማማ ደርሰንበታል፤ ካጠፋንማ የምናጠፋዉ ሁሉንም ጥቁር ነገር ነዉ አሏቸዉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡም፡- ጥሩ የምትጀምሩትስ ከየት ነዉ፤ ከነጮች አገር ነዉ ወይስ ከጥቁሮች? ይላሉ፡፡ ፈረንጆቹም ሃሳባችንን እየተቀበሉት ነዉ ብለዉ እየተደሰቱ ፤ የምንጀምረዉማ በእኛ ሀገር ካለዉ ጥቁር ነገር ነዉ ሲሉ መለሱላቸዉ፡፡ እንደዚህ ከሆነና ምንም ምን የጥቁርን ትንሿንም ሳትንቁ በሀገራችሁ ካለዉ ማጥፋት የምትጀምሩ ከሆነ እስማማለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ዐይናችሁ ዉስጥ ያለችዉንም ጥቁር ነገር ንቃችሁ መተዉ የለባችሁም፡፡ እንዲያዉም ዋናዉ የሰዉነታችሁ ክፍል ላይ በመሆኗ ከእርሷ መጀመር አለባችሁ አሏቸዉ፡፡ የሚያነጋግሯቸዉ ፈረንጆችም በዚህ ጊዜ ደንገጥ ብለዉ ለካ ጥቁር አስፈላጊ ነገር ነዉ አሉ፡፡ ይህን ከነገሩን በኋላ አባ እንደ ልማዳቸዉ ያለምንም ተጨማሪ ማብራሪያ ዝም አሉ፡፡