(አንድ አድርገን ህዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም)፡- “ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፤ ክብር ፤ ባህል ፤ እምነት ፤ሥርዓት ፤ መንግሥትና ቋንቋ ያቋቋመች ፤ የማትናወጥ ከመሆኗ ጋር ፤ ከሔኖክ ፤ ከመልከ ጼዲቅ ፤ ከነቢያትና ከሐዋርያት የተላለፈውን ትምህርት ፤ ሥርዓት ፤ እምነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ የኖረች ፤ በማስተላለፍ ላይ ያለች ፍኖተ ሕይወት ናት፡፡ ቅዱሳን አበውን ፤ ኃያላን ነገሥታትን ፤ ልዑላን መሳፍንትን ፤ ክቡራን መኳንንትን ፤ ዐይናሞች ሊቃውንትን በሥጋ ፤ በነፍስ ወልዳ ያሳደገች የሌላ የማትፈልግ ፤ የራሷንም የማትለቅ ዕጥፍ እናት ፤ ስንዱ እመቤት ናት፡፡” በማለት ስለ ቤተክርስቲያን የተናገሩት ታላቁ ሊቅ የቀለም ቀንድ አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩ ፡፡ እንዲህ የተባለላት ቤተክርስቲያን ዛሬ ከእርቀ ሰላም የተከደነ አጀንዳ በኋላ ስድስተኛ ብላ ፓትርያርክ ለመሾም ወሳኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡
Tuesday, 19 February 2013
የአቶ መለስ ዜናዊ ሃውልት ሲመረቅ አቡነ ጳውሎስ ያረፉበት ቦታ እንደታጠረ ነው
(አንድ አድርገን የካቲት 12 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር የአቶ መለስ ዜና ሀውልት ትላንትና የካቲት 11 2005 ዓ.ም ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ ፤ ቤተሰቦቻቸው እና ጥቂት ባለስልጣኖች በተገኙበት ተመረቀ ፡፡ በምርቃቱ ጊዜ አንድም የሚዲያ ተቋም በቦታው አልተገኝም ፤ የዲዛይንና የኤሌክትሪካል ስራውን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ስራው የመከላከያና ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ድርጅት አማካኝነት የተሰራ ሲሆን ስራውን ለማጠናቀቅ ከስድስት ወር በላይ መፍጀቱ ታውቋል፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን ያረፈበት ቦታ በመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ ውስጥ በስተግራ በኩል በግምት ከ260 እስከ 300 ካሬ ቦታ የፈጀ ሲሆን አስከሬኑ ያረፈበት ቦታ ከ40 ካሬ እንደማይበልጥ በቦታው ተገኝተን ለማወቅ ችለናል፡፡ ይህ ሃውልት ሙሉ በሙሉ በጥቁር እምነበረድ የተሰራ ሲሆን በምሽት የተለየ ውበት የሚሰጡት በርካታ መብራቶች ተገጥመውለታል ፡፡ ሃውልቱ ላይ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ከ1947-2004 ዓ.ም”የሚል ጽሁፍ ብቻ በአማርኛ እና በእግሊዝኛ ተጽፎበታል፡፡ ሃውልቱ ላይ ፎቶም ሆነ ሌላ ጽሁፍ አይታይበትም፡፡ ቦታው ተገኝተን እንደጎበኝነው ሃውልቱ ለህዝብ እይታ ክፍት የሆነ ሲሆን ቦታው ላይ ባሉት በአራት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ በግቢ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሃውልቶች ፊታቸው ወደ ቤተክርስቲያኑ ያዙሩ ሲሆን የአቶ መለስ ሃውልቱ ግን ፊቱን ወደ ውጭ በር አድርገው ሰርተውታል፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)