Tuesday, 19 February 2013

የአቶ መለስ ዜናዊ ሃውልት ሲመረቅ አቡነ ጳውሎስ ያረፉበት ቦታ እንደታጠረ ነው




(አንድ አድርገን የካቲት 12 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር የአቶ መለስ ዜና ሀውልት ትላንትና የካቲት 11 2005 ዓ.ም ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ ፤ ቤተሰቦቻቸው እና ጥቂት ባለስልጣኖች በተገኙበት ተመረቀ ፡፡ በምርቃቱ ጊዜ አንድም የሚዲያ ተቋም በቦታው አልተገኝም ፤ የዲዛይንና የኤሌክትሪካል ስራውን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ስራው የመከላከያና ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ድርጅት አማካኝነት የተሰራ ሲሆን ስራውን  ለማጠናቀቅ ከስድስት ወር በላይ መፍጀቱ ታውቋል፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን ያረፈበት ቦታ በመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ ውስጥ በስተግራ በኩል  በግምት ከ260 እስከ 300 ካሬ ቦታ የፈጀ ሲሆን አስከሬኑ ያረፈበት ቦታ ከ40 ካሬ እንደማይበልጥ በቦታው ተገኝተን ለማወቅ ችለናል፡፡ ይህ ሃውልት ሙሉ በሙሉ በጥቁር እምነበረድ የተሰራ ሲሆን በምሽት የተለየ ውበት የሚሰጡት በርካታ መብራቶች ተገጥመውለታል ፡፡  ሃውልቱ ላይ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ከ1947-2004 ዓ.ም”የሚል ጽሁፍ ብቻ በአማርኛ እና በእግሊዝኛ ተጽፎበታል፡፡ ሃውልቱ ላይ ፎቶም ሆነ ሌላ ጽሁፍ አይታይበትም፡፡ ቦታው ተገኝተን እንደጎበኝነው ሃውልቱ ለህዝብ እይታ ክፍት የሆነ ሲሆን ቦታው ላይ ባሉት በአራት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ በግቢ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሃውልቶች ፊታቸው ወደ ቤተክርስቲያኑ ያዙሩ ሲሆን የአቶ መለስ ሃውልቱ ግን  ፊቱን ወደ ውጭ በር አድርገው ሰርተውታል፡፡

ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዝግ ስብሰባ  “መለስ ፋውንዴሽን” የሚል ተቋም መንግሥት ያቋቋመ ሲሆን ፤ ፋውንዴሽኑ ስራውን ሲጀምር አስከሬኑን ከቅድስት ሥላሴ በማንሳት አስገነባዋለሁ ወደሚለው ህንጻ እንደሚያዛውር ለማወቅ ተችሏል፡፡  “መለስ ፋውንዴሽን”ን ስራ ለማስጀመር 12 አባላት ያሉት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ቤተሰቦቻቸው የቦርድ አባል የሆኑበት ኮሜቴ መቋቋሙን ለማወቅ ተችሏል ፤ የተቋቋመው ኮሚቴ የመጀመሪያ ስራው አቶ መለስ ዜናዊን የሚዘክር ፊልም መስራት ሲሆን ፤ በኮሚቴውም የሚሰራውን የፊልሙን ይዘት ፤ የሚሰራበት የቋንቋ ብዛት ፤ የፊልሙ ርዝመትና ፤ በማን መሰራት እንዳለበት እና መሰል ጉዳዮች እያየ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን ፋውዴሽን ገቢ ለማሰባሰብ በማሰብ ከወራት በፊት እሳቸው ሲጽፏት  የነበረችው “አዲስ ራዕይ” መጽሄት በነፍስ ወከፍ በ100 ብር ሂሳብ ለአባሎቻቸው ሲሸጥ እንደነበር የምናስታውሰው ነው ፡፡ የመጽሀፉን ዋጋ (100 ብር) በአንድ ጊዜ መክፈል ያልቻሉትን የድርጅት አባሎቻቸውን በአራት ጊዜ ክፍያ ተከፍሎ የሚያልቅ እዳ እየተመዘገቡ ሲወስዱ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሃውልት እስከ አሁን ድረስ መስራት እንዳልተጀመረ እና ከ30 ካሬ የመይበልጥ ቦታ በቆርቆሮ ብቻ ታጥሮ የተቀመጠ መሆኑንም ለመመልከት ችለናል፡፡ 


ቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስትያን ሲገቡ በስተቀኝ በኩል በ1967 ዓ.ም በደርግ በግፍ የተገደሉትን ሰዎችን ሃውልት በሶስት የማያንሱ   የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ሲመለከቱ በስተቀኝ በቁል ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊን ሃውልትን ለመጠበቅ አራት የሰራዊቱ አባላትን ይመለከታሉ፡፡ 


ለሁሉም ነፍስ ይማር

No comments:

Post a Comment