Thursday, 16 May 2013

የኤማሁስ መንገደኞች...ሉቃስ 24


በእታ ሰይፈ

ጸጥ ባለው አሸዋማ በረሃ ረጅሙን መንገድ ተያይዘውታል። ከመነሻቸው ጀምሮ እስከአሁን የመጡበትን ርቀት ባለማስተዋል
የልባቸውን ጭንቀት ያወጋሉ። ሰሞኑን በምድረ ኢየሩሳሌም ተደርጎ የማያውቅ ወደ ፊትም የማይደረግ ግፍ ተፈጽሟል፣ ፍርድ ተስተጓጉሏል። 

ሰዎቹ የጸሃዩን ግለት፣ የመንገዱን ርቀት፣ ረሃብና ድካሙን ረስተው ስለዚያ በግፍ ስለተገደለው ደግ ሰው ያወራሉ። አብሯቸው በቆየባቸው 3 አመታት ውስጥ ያዩትን የተለየ ፍቅር፣ ቸርነት፣ ትህትና፣ ደግነት፣ ተዓምራት እያሰቡ፡ ከአንደበቱ እንደ ማር እያዘነበ ያስተማራቸውን የጣፈጠ ቃል እያውጠነጠኑ ይነጋገራሉ። ፍቅሩ እንደ ልክፍት ተጠናውቷቸው ስለ እርሱ ከማሰ...ብ አልቦዘኑም። ስድሳውን ምዕራፍ እንደተጓዙ ያላስተዋሉት 3ኛ ሰው ተቀላቀላቸው። 

ድንገትም፦ 
"እንዲህ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ እርስ በርስ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው?"ሲል ጠየቃቸው። 
በንግግሩ እጅጉን ተገርመው ከሁለቱ አንዱ ቀለዮጳ ፈጠን በማለት፦ 
"አንተ ደግሞ በኢየሩሳሌም ስትኖር በእነዚህ ቀናት የሆነውን አታውቅምን?" አለው። ሰውየውም ምንም እንዳልሰማ በመሆን፦ 
"ይህ ነገር ምንድር ነው?" አላቸው። 
"ከወዴት ሀገር የመጣ እንግዳ ይሆን?" ሲሉ አሰቡና በእግዚአብሔርና በህዝቡ ፊት በቃልና በስራ ብርቱ ስለነበረው በግፍ ስለተሰቀለው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ አንድ በአንድ አወሩለት። 

አስቀድሞ እንደሚነሳ ቢነግራቸውም አሁን ግን ሞቶ ከተቀበረ 3 ቀን ሆነው። በእስራኤል ሁሉ የሞቱ ወሬ ተናፍሶ እነርሱም ተስፋ ቆርጠው ወደ መንደራቸው ኤማሁስ እየተጓዙ ነው። ግን ደግሞ የዛሬው የሴቶቹ ወሬ አጠራጥሯቸዋል። ቀጠል አድርገውም አሁን ደግሞ ያስገረመን አሉ፦ 
"ከእኛ መካከል ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የሄዱ ሴቶች ስጋውን ባጡት ጊዜ ተነስቷል በዚያ የለም አሉን" 
አሉ ግራ በተጋባ በሰከነ ድምጽ። የልባቸውን መዛል የተመለከው በጸጥታ ታሪኩን ያዳምጥ የነበረው ሰው፦ 
" እናንተ የማታስተውሉ፥ነብያትም የተናገሩትንም ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፡ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?"አላቸው። 
 ከሙሴና ከነብያት ጀምሮ ስለ እርሱ በመጽሃፍ የተነገረውን እየተረጎመላቸው ሳያስቡት ከመንደራቸው ደረሱ። ማንነቱን ያልተረዱት በቃሉ ብርታት የተማረኩት የሩቅ ተጓዥአብሯቸው ያድር ዘንድ ግድ አሉት። 
"ማታ ቀርቧልና፡ ቀኑም ሊመሽ ጀምሯልና እባክህ ከእና ጋር እደር?" አሉት በሚማጽን ንግግር።
 ሰውየው ቃላቸውን ተቀብሎ ከቤታቸው ገባና አብሯቸው በማዕድ ተቀመጠ። እንጀራንም በርኮ ሰጣቸው። ተከፍተው የማያዩ አይኖቻቸው ተከፈቱ፤ ሰውየውን አዩት፡ ያውቁታል። ረጅሙን መንገድ አብሯቸው የተጓዘው፣ንግግሩ ልባቸውን ያቀልጠው የነበረው፣ ከሞት የተነሳው እርሱ ኢየሱስ ነው። ሉቃስና ቀለዮጳ በደስታ ሰከሩ። ጊዜ ሳያባክኑ በፍጥነት ወደ ኢየሩሳሌም ሮጡ፤ ሁሉን በአንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው አገኛቸው።
"ተነስቷል! ተነስቷል! ጌታ በእውነት ተነስቷል" በደስታ ሲቃ ምስራቹን አበሰሯቸው።
 በመንገድ የተናገራቸውን፣ እንጀራም ሲሰጣቸው የሆነውን እየነገሯቸው ሳለ በብርሃን ጸዳል የተሞላ ድምጹ የሚያሳርፍ ሰው በመሃከላቸው ቆሞ 
"ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው፡፡ 
 በእርግጥ ኢየሱስ ነው። ምትሃት ያዩ መስሏቸው ፈሩ ደነገጡም፤ እርሱ ግን 
"እኔ ነኝ አትፍሩ አትደንግጡም፤ መንፈስ ስጋና ደም የለውም፡ እኔ እንደሆንኩ ታምኑ ዘንድ እጆቼንና እግሮቼን እዩ ዳስሱም" በማለት አረጋጋቸው።
 ኢየሱስን አዩት፥ ተነስቷል! ደስታቸው እጥፍ ሆኖ አይናቸውን ማመን ቸገራቸው። ልባቸውን ያወቀው አምላክ፡ እምነታቸው ሙሉ እንዳልሆነ ተመልክቶ 
"በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?" አላቸው።
 የተጠበሰ ዓሣ ቁራጭና የማር ወለላ አቀረቡለት፤ እምነታቸው ይሞላ ዘንድ ዛሬም እንደቀድሞው በመሃከላቸው ተመገበ። አብሯቸው ሳለ በሙሴ ህግና በመዝሙራት መጻህፍት መከራን እንዲቀበልና እንዲነሳ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ እንደሚገባው ያስተማራቸውን ያስታውሳቸው ጀመር... 

"ሰላም ለእናንተ ይሁን" ሉቃ 24:36...  
 እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤ በሰላም 

አደረሳችሁ!!!..