ጠቅ/ቤተ ክህነት “ጉባኤ አርድእት” ነን ባዮች በመንበረ ፓትርያርኩ እንዳይሰበሰቡ አገደ
· እገዳው የተላለፈው መንግሥት ለአባ ጳውሎስ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ነው ተብሏል።
· በአባ ጳውሎስ ቀጥተኛ ይኹንታ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ለቀናት በኅቡእ ሲሰበሰብ የቆየው ቡድኑ÷ ከፊል መሥራች አባላቱ ከሸሹትና የስብሰባ እገዳ ከተጣለበት በኋላ÷ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት የ‹ዕወቀኝ› ጥያቄ ማቅረቡ ተነግሯል።
· የቅ/ሲኖዶስ እና የጠቅ/ቤ/ክህነት ጽ/ቤቶች÷ ቤተ ክርስቲያን “ጉባኤ አርድእት” የተሰኘውን ኅቡእ ቡድን እንደማታውቀው ገልጸዋል።
· የኅቡእ ቡድኑ አስተባባሪ ፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ የያዘውን የጠ/ቤ/ክህነቱን መኪና እንዲያስረክብ ተደርጓል።
· አባ ጳውሎስ የእምነት ንጽሕናቸውን በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ያላረጋገጡትንና ከቡድኑ ቀንደኛ አስተባባሪዎች አንዱ የኾኑትን አባ ሰረቀን በመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥ/አስኪያጅነት ለመሾም ማሰባቸው ተሰምቷል።
· “ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ሲባል የቡድኑን ኅቡእ እንቅስቃሴ በጥብቅ እየተከታተልነው ነው” /የጠ/ቤ/ክ መመሪያ ሓላፊዎች/።
· “ከጉባኤው አስተባባሪዎች አብዛኞቹ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ተቀባይነት ያጡ ግለሰቦች ናቸው” /የቋሚ ሲኖዶስ ምንጮች/።
ባለፈው ሳምንት፣ ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ተፈርሞ በአድራሻ ለጥበቃ አገልግሎት ክፍል የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው÷ ራሱን “ጉባኤ አርድእት” በሚል የሚጠራው ቡድን ከቅዱስ ሲኖዶስ ይኹን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተሰጠው አንዳችም ዕውቅና የለውም፤ የጉባኤው አስተባባሪዎች በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ በውል ተለይቶ ላልታወቀና ላልተፈቀደ ዓላማ በኅቡእ መሰብሰባቸው ሕገ ወጥነት በመኾኑ የትኛውንም አዳራሽ ይኹን ቢሮ ለስብሰባ መጠቀም አይችሉም፤ የጥበቃ አገልግሎት ክፍሉም ይህንኑ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ደብዳቤ ባሻገር “ጉባኤ አርድእት”ን የሚመለከተው የስብሰባ እገዳ በማሳሰቢያ መልክ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቅጽር በይፋ እንዲለጠፍ መደረጉ ተገልጧል፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደገለጹት “ጉባኤ አርድእት” ነን ባይ አስተባባሪዎች በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ እንዳይሰበሰቡ የሚያግዳቸው ውሳኔ የተላለፈው÷ ቡድኑ ዕውቅና ባልተሰጠው ማንነቱና በሌለው ሥልጣን ፓትርያርኩ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊ ባልኾነ መንገድ ለመለወጥ በተለያየ መንገድ የሚያደርጉትን ሙከራ በማገዝ፡- የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን እንዳሻቸው ለመሾምና ለመሻር፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው እንዳሻቸው ለማንከራተት፣ ኤጲስ ቆጶሳትን እንዳሻቸው ለመሾም. . . ወዘተ በማስቻል ዐምባገነናዊ አስተዳደራቸውን ለማጠናከር፤ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበርና ሌሎችም በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስፋፋትና መጎልበት ዙሪያ የሚሠሩ ማኅበራትን በ”ባዕድ አደረጃጀትና ተቀጽላ” እንዲቆጠሩ በማድረግ ለማፈራረስ፤ ከዚህ ጋራ ተያይዞና ይህን ተከትሎ በሚፈጠረው ክፍተትም “ጥናትና ምርምር አደርጋለኹ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩንና ቅዱስ ሲኖዶስን አማክራለኹ” በሚል ስም የግልና የቡድን ጥቅሙን ብሎም የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ሤራ ለማሳካት የወጠነው ዕቅድ በብዙኀን መገናኛ መጋለጡን ተከትሎ መንግሥት ለአባ ጳውሎስ በሰጠው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መኾኑ ተገልጧል፡፡
ለ”ጉባኤ አርድእት” ነን ባይ ግለሰቦች በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሳይቀር የመሰብሰብ ፈቃድና ሌሎችንም ድጋፎች በመስጠት የሕገ ወጥ ዓላማቸው ተባባሪ በመኾናቸው ክፉኛ የተወቀሱት አባ ጳውሎስ÷ በቡድኑ ነውጠኛ እንቅስቃሴ ሳቢያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚፈጠር ማንኛውም ሁከት ብቸኛ ተጠያቂው እርሳቸውና እርሳቸው ብቻ እንደሚኾኑ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ አባ ጳውሎስ ቡድኑ በኅቡእ ሲያካሂድ የቆየውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ መደገፋቸውን ለማበል ሞክረው እንደነበር ምንጮቹ የጠቆሙ ሲኾን÷ ከመንግሥት በተሰጣቸው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እና “በዚህ የተነሣ በዓሌን (ነገ የሚከበረውን 20ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን) አላበላሽም” በሚል ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት በሰጡት መምሪያ የስብሰባ እገዳው ደብዳቤ እንደተጻፈ ነው የተመለከተው፡፡
አባ ጳውሎስ 12 ንኡሳን ኮሚቴዎች ያቋቋሙለትንና ቀደም ሲል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መመደቡ የተነገረውንግማሽ ሚሊዮን ብር ሳይጨምር÷ የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በሀ/ስብከቱ ጠንካራ አድባራትና ገዳማት ላይ በሚፈጥሩት አስገዳጅነትና ልዩ ልዩ ማግባቢያ እየተሰበሰበ የሚገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ የሚደረግበትን የኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን “በሰላም ለማክበር” በሚል የ”ጉባኤ አርድእት” አስተባባሪዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዳይሰበሰቡ መከልከላቸው ስልታዊ እንጂ ልባዊአለመኾኑን ነው ምንጮቹ የሚናገሩት፡፡
ለዚህም የቡድኑ ዋነኛ አስተባባሪዎች (አባ ሰረቀን ጨምሮ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ አእመረ አሸብር፣ ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን) በተለይም የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ በኾኑት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ቢሮ መሰብሰብ መቀጠላቸውን እንደ አስረጅ ይጠቅሳሉ፡፡ አባ ጳውሎስ የቡድኑ ሤራ በብዙኀን መገናኛ በመጋለጡ ዋነኛ አስተባባሪዎቹን ‹በማኅበረ ቅዱሳን ተበልጣችኋል›በሚል ዘልፈውና አብጠልጥለው ሲያበቁ÷ አልፈርምም በሚል አሻፈረኝ ያሉበትን የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ያስተላለፈውን ቃለ ጉባኤ ዘግይተው መፈረማቸው ሌላው የተቃውሞ ማብረጃ፣ የማዘናጊያና በዓለ ሢመትን ለማድመቅ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ድጋፍ የማሰባሰብ ስልት ኾኖ ተወስዷል፡፡
ሌላው የአባ ጳውሎስን ውሳኔ ስልታዊ ነው ያሰኘው አስረጅ በበዓለ ሢመታቸው ማግስት ለአባ ሰረቀ ሕገ ወጥ ሹመት በመስጠት የተናጋውን የኀይል ማእከላቸውን ለማጠናከር ያሰቡት ዕቅድ ነው፡፡ ይኸውም የግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ጥንተ አብሶን በተመለከተ÷ በእመቤታችን ክብርና ቅድስና ላይ ያላቸውን የእምነት አቋም ጉዳዩን እንዲያጣራ ለተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጉባኤ ጥምር ኮሚቴ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ የተላለፈውን ውሳኔ በአግባቡ መፈጸማቸው በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ሳይረጋገጥ ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ለማድረግ አስተላልፈውት የነበረውን ሕገ ወጥ ትእዛዝ ለመተግበር መወሰናቸው ነው፡፡
“በንጹሕ እምነቴ ላይ ከደረሰብኝ ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል ነጻ መኾኔን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ይዣለኹ”በሚል በራሳቸው ጊዜ ‹ነጻነታቸውን› እያወጁ የሚገኙት አባ ሰረቀም÷ በእነ ኀይለ ጊዮርጊስ (ክልፍልፊት)ና እጅጋየሁ በየነ (ኤልዛቤል) አጋፋሪነት የቋመጡለትን የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ሹመት ለማግኘት እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ነውር ጌጣቸው፣ ሕገ ወጥነት ልማዳቸው ለኾኑት እኒህ ሁለት ግለሰቦች የሚያስጨንቃቸው÷ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የምክትል ሥራ አስኪያጅ ሹመትን በተመለከተ በአንቀጽ 30 ንኡስ አንቀጽ 9 መሠረት÷ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሥልጣነ ክህነት፣ በቂ የትምህርት ደረጃና ችሎታ ያላቸውን ሦስት ሰዎች በዕጩነት ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርቦ በማስመረጥ ቋሚው ቅ/ሲኖዶስ ሲስማማበት ብፁዕነታቸው በሚጽፉት ደብዳቤ በፓትርያርኩ እንደሚሾም የተቀመጠው ድንጋጌ መጣስ አይደለም፡፡ አባ ጳውሎስንና ነውረኞቹን እነኀይለ ጊዮርጊስን የሚያስጨንቃቸው አባ ሰረቀ÷ ለዚያውም በመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት÷ የሚሾሙት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የእምነት ንጽሕናቸው በሚመለከተው አካል ፊት አለመረጋገጡ አይደለም፡፡ የእነርሱ ስጋት ሹመቱን በቀዳሚነት በሚቃወሙት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስና የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ሳቢያ የበዓለ ሢመቱ አከባበር ጥላ እንዳያጠላበት ነው፡፡ ስለዚህም አባ ሰረቀን በም/ሥ/አስኪያጅነት ለማስቀመጥ የተያዘው ዕቅድ ከበዓለ ሢመቱ በኋላ እንዲኾን መታሰቡ እየተነገረ ነው፡፡
ምናልባትም በበዓለ ሢመቱ ሳቢያ በመዲናዪይቱ አዲስ አበባ የሚሰበሰቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ይኸው የአባ ሰረቀ ሹመት በአጀንዳ የሚቀርብላቸው ከኾነ የግንቦቱን ውሳኔ አፈጻጸም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ በዚህም አጋጣሚ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል÷ አባ ሰረቀ ስለእምነት ሕጸጽ የቀረበባቸውን ጥያቄ አስመልክቶ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ኮሚቴ የሰጡትን ምላሽ በተቀመጠው ውሳኔ አግባብ በጽሑፍ ሳያረጋግጡ “ነጻነቴን አውጆልኛል” ያሉትን ደብዳቤ ወጪ ስላደረጉበትና ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጠንካራ ወቀሳ ስላስከተለባቸው የጫና አሠራር ማብራሪያና ይቅርታ እንደሚጠይቁ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል የ”ጉባኤ አርድእት” ነን ባይ አስተባባሪዎች በመንበረ ፓትርያርኩ አዳራሾችና ቢሮዎች እንዳይሰበሰቡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መታገዳቸውን ተከትሎ የቡድኑ ቀንደኛ አስተባባሪ የኾነው ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ከአሜሪካ ከመጣ ጀምሮ በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ የሚያሽከረክረውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መኪና በምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ትእዛዝ እንዲያስረክብ መደረጉ ታውቋል፡፡ ፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ በሰሜን አሜሪካ “የአህጉረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ” እና የሕገ ወጡ “የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሙሉ ሥልጣን” ኾኖ በአባ ጳውሎስ እብሪት ለተሾመበት ሥልጣን ያስፈልገኛል ያለው በጀት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ ተግዳሮት የገጠመው መኾኑም ተሰምቷል፡፡
“የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር” (Ethiopia Assemblies of God) በሌላ ሰበካ ስያሜው “ቤዛ ቸርች” የተሰኙትን የፕሮቴስታንት አብያተ እምነት እንደሚከታተል የተጋለጠው ፕሮቴስታንታዊ ኀይለ ጊዮርጊስ÷ መረጃው በደጀ ሰላም ይፋ ከተደረገ በኋላ ሞራላዊ ይዞታው በከፍተኛ ደረጃ ተንኮታኩቶ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ ግለሰቡ የለየለት ፕሮቴስታንት መኾኑን የገለጸው የዜና ጥቆማ በጡመራ መድረካችን ከወጣ በኋላ የኀይለ ጊዮርጊስን ግላዊ ሕይወት ጨምሮ በሥራ አጋጣሚ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች በቅርበት የሚያውቁትደጀ ሰላማውያን በርካታ ማስረጃዎችን ለጡመራ መድረካችን ማድረሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከእኒህም መካከል ከሰሜን ወሎ - ወልዲያ፣ ከደቡብ ጎንደር - ደብረ ታቦር፣ ከምዕራብ ጎጃም - አጉንታ ማርያምና ባሕር ዳር እንዲሁም ከመዲናዪቱ አዲስ አበባ ያገኘናቸው ይጠቀሳሉ፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን የሚመለከቱ ግላዊ ማስረጃዎችን እናቆያቸውና ፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮጀክት አስተባባሪ ኾኖ ወልዲያ ከተማን ማእከል አድርጎ ይሠራ በነበረበት ወቅት ወጣቶችን በቤቱ ሰብስቦ እጆቹን በፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ ጭኖ ይጸልይ፣ ይሰብክና ይዘምር እንደነበር የሚያሳየው ማስረጃ አስደናቂ ኾኖ አግኝተነዋል፡፡ በወቅቱም ፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ በማኅበረ ቅዱሳን የወልዲያ ንኡስ ማእከልና በሰንበት ት/ቤቶች አባላት የተባበረ ጥረት ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መታገዱን አረጋግጠናል፡፡
ከአዲስ አበባ የመንበረ ፓትርያርክ ምንጮቻችን ያገኘው ማስረጃ ደግሞ ፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ በሙስኛ ተግባራቸው ከላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ተነሥተው ለአባ ጳውሎስ በሰጡት መተያያ (ከፍተኛ የዝውውር ክፍያ እንበለው?) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ም/ሥራ አስኪያጅ በኾኑት አባ አእምሮ ሥላሴ ታከለ ሹመት ጀርባ ከባለሟላ እጅጋየሁ በየነ ጋራ ስሙ እየተነሣ መኾኑን ይጠቁማል፡፡ አባ አእምሮ ሥላሴ በ”ጉባኤ አርድእት” አባልነት በፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ እና በሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ አማካይነት አስወዳጅም አስገዳጅም በኾነ መንገድ እየተመለመሉ ከሚገኙት የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ካህናት ተባባሪ አባላት መካከል አንዱ መኾናቸው የማስረጃውን እውነታ አጉልቶታል፡፡
ሞራላዊ ይዞታው ከተንኮታኮተ በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን እንደ እኵያ/ጓደኛ በመቁጠር በጽሑፍ ለመግለጽ በሚያሳፍርና ለጡመራ መድረኩ በማይመጥን አኳኋን በፍጹም ንቀትና ዘለፋ የሚናገርበት የድምፅ ማስረጃም ሌላው ጥቆማ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ጋጠ ወጥነቱ የብዙዎችን ቁጣ እያነሣሣ የሚገኘው ፕሮቴስታንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ “ከመቸው ጊዜው ደርሶ በሄደልን?” በማለት አምርረው የሚናገሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኞች ፍጹም ጥላቻ ማትረፉን ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡ ከብዙኀኑ ፍጹም ጥላቻ የቀሩለት ባልንጀሮቹም በሰሞኑ የኮሌጅ ምረቃቸው ዕለት ከእጅጋየሁ በየነ ጋራ በፕሮቴስታንታዊ ዳንኪራ ያስረገጡት መናፍቁ አሰግድ ሣህሉና አእመረ አሸብር (ከ”ጉባኤ አርድእት” ሌሎች አመራሮች ጋራ) መኾናቸው ተገልጧል፡፡
ከአባ ጳውሎስ ባገኘው ይኹንታ “ጉባኤ አርድእት” በሚል ራሱን ሠይሞ፣ አደራጅቶና ተልእኮ ሰጥቶ በኅቡእ ሲንቀሳቀስ የቆየው ቡድን ፀረ - ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ፀረ - ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ፀረ - መንፈሳውያን ማኅበራት በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከር ይልቅ ለአባ ጳውሎስ ዐምባገነናዊ ሥልጣን መጠናከር፣ የቡድኑ አባላት በቤተ ክህነቱ በያዙት ሓላፊነት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚያሳድዱትን የግልና የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የያዘው ዓላማ ከተጋለጠ በኋላ መሥራች አባሎቼ ናቸው ያላቸው ግለሰቦች ራሳቸውን ማሸሻቸው እየተገለጸ ነው፡፡ ከእኒህም የሚበዙት ፕሮቴስንታዊው ኀይለ ጊዮርጊስ፣ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ላይ የሚሠራው ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ቡድኑ በኅቡእ የሚያካሂዳቸውን ስብሰባዎች በማስተባበር የሚታወቀው ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን (በመቐለ ስሙ ብርሃነ ውሪጥ) በፓትርያርኩ ስም እያስፈራሩ ያሰባሰቧቸው የመምሪያ ሓላፊዎች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ይህም ኹኔታ ቡድኑ ራሱን በይፋ ገልጦ ማንነቱን የሚያስረዳ ነው የተባለ ሰነድ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በመላክ የ‹ዕወቀኝ› ዐይነት ትእዛዝ አይሉት ጥያቄ ለማቅረብ እንዳስገደደው ነው የተነገረው፡፡ ውሎ አድሮ በይፋ መውጣቱ ግድ ቢኾንም ለፀሐይ ብርሃን መጋለጡ ያጠወለገው ወይ ያጸድቀው ይኾን የሚለውን ወደፊት አብረን እናየዋለን፡፡
በተያያዘ ዜና ራሱን “ጉባኤ አርድእት” በሚል የሚጠራው ቡድን በምን ምክንያት እንደተቋቋመና ለምንስ በኅቡእ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ጥያቄ ያጫረባቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሐላፊዎች ለቤተ ክርስቲያኗ ደኅንነት ሲባል እንቅስቃሴውን በትኩረት እየተከታተሉ መኾናቸውን ትላንት ለኅትመት የዋለው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ጋዜጣው በ19ኛ ዓመት ቁጥር 20 እትሙ ያነጋገራቸው የመምሪያ ሓላፊዎች÷ “ጉባኤ አርድእት” በሚል ራሱን የሚጠራው ቡድን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ ሊሠራ ከኾነ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ማግኘት ይገባዋል፤ ነገር ግን ይህን በመተላለፍ ለተለየ ዓላማ መሰባሰቡ አደጋ ስለሚኖረው እንቅስቃሴውን በጥብቅ እየተከታተሉት መኾናቸውን ሓላፊዎቹ መግለጻቸውን አስረድቷል፡፡
“ጉባኤ አርድእት” የተሰኘውን ቡድን ቤተ ክርስቲያን እንደማታውቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊንና የጠቅላይ ቤተ ከህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጠቅሶ የዘገበው ጋዜጣው÷ አብዛኞቹ የቡድኑ አስተባባሪዎች በሚሠሩባቸው ቦታዎች ተቀባይነት እያጡ የመጡ ግለሰቦች በመኾናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ እኒህ ግለሰቦች ለመፍጠር ካሰቡት አደጋ ቤተ ክርስቲያንን እንዲታደግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን አስታውቋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን።
1 comment: