Friday, 6 July 2012

ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ.ም  እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ::
በዘሚካኤል አራንሺ


በዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ዘመን የነበረው ፈርኦንና የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ለዘፋኝ ወሮታ የሰጠው ሄሮድስ የሚያመሳስላቸው አንድ 
ዓይነት ተግባር ፈጽመዋል:: ይኽውም ሁለቱም ልደታቸውን ያከብሩ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱ ነው:: /ዘፍ.40፥20 ፤ 
ማቴ.14፥6/:: ታሪካቸውን ስናጠና ደግሞ በርካታ መመሳሰል እንደነበራቸው እንገነዘባለን:: ሁለቱም ነገሥታት ናቸው:: ሁለቱም 
ንጹሐንን አስረዋል:: ሁለቱም ደም አፍሳሾች ነበሩ:: በልደት በዓላቸውም ነፍስ አጥፍተዋል:: በልደት በዓላቸው ነፍስ ያጠፉ 
ሰዎች ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ መጻፉ የልደት በዓል ማክበርን ስህተት አያደርገውም:: በጌታችን ልደት መቶ አርባ አራት ሺህ 
ሕጻናት በሄሮድስ ትእዛዝ ተገድለዋል:: የጌታችንን ልደት ግን እናከብራለን:: መግደል ኃጢአት መሆኑን እንመሰክርበት ካልሆነ በቀር 
ነፍስ በማጥፋት የሚከበር በዓል የለንም:: የፋሲካን በዓል በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለማክበር እንገደዳለን እንጂ ዘፋኞች ድግስ 
ስለሚያዘጋጁበት ማክበሩ ቢቀር ቢባል ሞኝነት ነው:: ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳንን ልደት በዓል ስታከብር የራሷ 
ሥርዓትና ባሕል የበዓላት መቁጠሪያ /ሊተርጂካል ካላንደር/ አላት:: የቱ መቼ መከበር እንዳለበትም ምክንያታዊ በሆነ መንገድ 
ታስረዳለች:: ጥንታዊት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆንዋም በርግጥኝነት ዕለታቱን ቆጥራ ትናገራለች:: በነቢይ የአዋጅ ነጋሪ 
ቃል ተብሎ የተነገረለት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን የልደት በዓል የምታከብረው በሰኔ ሠላሳ ቀን ነው::

የጻድቃን ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ እንደሆነ፤ ቅዱሳኑን ያገኘንባት ልደታቸውም የከበረች ናት:: /መዝ.116፥15/:: 
የመጥምቁ ዮሐንስን ልደት ያበሰረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል::” እንዳለ በልደተ ቅዱሳን ደስ 
እንሰኛለን:: /ሉቃ.1፥14/:: በዓለ ቅዱሳን የደስታ በዓላት ናቸውና:: የተወለዱበት ፥ ልዩ ልዩ ገቢረ ተዓምራት ወመንክራት 
የፈጸሙባቸው፥ ሰማእተ ኢየሱስ ሆነው መከራ የተቀበሉባቸው፥ያረፉበትና የተሰወሩበት፥ ቃል ኪዳን የተቀበሉባቸውን ዕለታት 
የምናከብረው በደስታ ነው:: ቅዱስ ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና በዓል የሚያደርጉ ሰዎች 
የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ።” እንዲል:: /መዝ.42፥4/:: ዕለታቱ በደንጊያ ተወግረው፥ በመጋዝ ተተርትረው ፥ ወደ እሳት 
ተጥለው፥ ለአናብስት ተሰጥተው፥ በሰማእትነት ያረፉባቸው እንኳ ቢሆኑ የደስታ በዓላት ናቸው:: የምስክርነታቸውን እውነትነት፥ 
የእምነታቸውን ጽናት፥ ታዛዥነታቸውንና ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር በመግለጣቸው፤ የሚያገኙትን ክብር፥ የሚወርሱትን 
መንግስት እናስባለንና:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን የከበረች የእረፍቱን ቀን በማኅሌት ከበሮ መትተን፥ጸናጽል ጸንጽለን፥ ወረብ 
ወርበን፥ ቅዳሴ ቀድሰን፥ መዝሙር ዘምረን፥ መልክ ደግመን፥ ገድል አንብበን፥ ተዓምሩን ተናግረን፥ ቅድስናውን መስክረን 
እንደምናከብረው በዓለ ልደቱንም እንዲሁ እናከብራለን:: ጠቢቡ “ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል...” ብሏልና:: 


በመወለዳቸው ደስ ተሰኝተን በዓል እናደርጋለን:: /ምሳ.29፥2/::ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ የብዙዎችን ደስታ ወልደዋል:: 
ጌታችን በወንጌል “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ . . . ” /ማቴ.7፥17-19/:: በማለት እንዳስተማረን የመጥምቁ 
ወላጆች “በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ” ተብሎየተመሰከረላቸው መልካም ዛፎች ነበሩና:: መልካም ፍሬ ቅዱስ ዮሐንስን 
አስገኙልን:: /ሉቃ.1፥6/:: ቅድስናቸው ከፍሬያቸው ከዮሐንስ የተነሳ ገኖ ዛሬም ድረስ ይታያል:: ለብዙዎች የሚሆን ደስታን 
ወልደዋልና ስሙን ዮሐንስ አሉት ትርጓሜው ደስታ ማለት ነው:: የክርስቲያናዊ ጋብቻ ዓላማ ምእመናንን መልካም ዛፍ አድርጎ 
መትከል ነው:: ሲንከባከቡትም እንደ ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ደስታው ከቤተ ዘመድ ያለፈ መልካም ፍሬ ያፈራል:: 
በመጥምቁ ዮሐንስ ልደት “እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል . . . ” በማለት ነቢያተ እግዚአብሔር 
የተናገሩትን የትንቢት ቃል ለሚጠባበቁ ሁሉ ደስታ ነበረ:: /ሚል.3፥1 ፤ኢሳ.40፥3 ፤ማር.1፥1-5/:: የዮሐንስ መምጣት 
ለጌታችን መምጣት የምሥራች ነውና:: “ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።” የሚለው ስብከቱም የሚያስታውሰን ይህንኑ ነው:: /
ማር.1፥7/:: በዮሐንስ መጥምቅ ልደት ደስ የሚሰኘው ያለፈውም የሚመጣውም ትውልድ ነው::

በዘመኑ የነበሩትን በትምህርቱ ደስ አስኝቷቸዋል:: ትምህርቱና ተግሣጹን የሰሙትን ከስህተት መልሷቸዋልና ደስ ተሰኝተውበታል:: 
በኃጢአት ያደፈ ስውነታቸውን በንስሀ ጥምቀት አዘጋጅቷልና ደስ ተሰኝተውበታል:: አገልግሎቱን በሚገባ የተረዳ መናኒ ነበርና 
ሕይወቱ ደስ የሚያሰኝ ነበረ:: አገልግሎቱን የምታውቅ፥ ክብሩን የምትመሰክር፥ በቃል ኪዳኑ የምትታመን ቤተ ክርስቲያንም ደስ 
ትስኝበታለች:: ስለዚህም በልደቱም በእረፍቱም ቀን የደስታ በዓል ታደርጋለች:: ምእመናንም በቃል ኪዳኑ በመታመን የምናደርገው 
የመታሰቢያ በዓሉ ደስታን የሚሰጥ ነው:: በመወለዱ ያገኘናቸውን የመጥምቁን በረከቶች እያሰብን አምላኩን እናመሰግናለን:: ልደተ 
ቅዱሳንን የማዘከር ዓላማው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አስቦ ለማመስገን ነው:: ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት ስንናገር ወላጆቹንና 
ጽድቃቸውን የአባቱን የክህነት አገልግሎት፥ የመልአኩን ተራዳኢነት፥ የእናቱን በመንፈስ ቅዱስ መቃኘት፥ የእርሱን በማኅጸን 
መዝለል፥ የአባቱን አንደበት መክፈቱን፥ ስለ አደገበት የናዝራውያን ሥርዓት፥ ስለ አሳደገችው የበረሀ ፍየል /ቶራ/፥ ይመገበው 
ስለነበረው አንበጣና የበረሀ ማር፥ ዞሮ ያስተማራቸው ትምህርቶች፥ ስለ ፈጸማቸው የጽድቅ ሥራዎች፥ ጌታችንን ስለ ማጥመቁ፥ ስለ 
ተግሣጹና በሰማእትነት ስለ ማረፉ፥ ስለ ተዓምራቱ ከዚያም በኋላ በጸሎቱና በአማላጅነቱ ለሰው ልጆች ስለ ረዳው ርዳታ . . . 
በደስታ በማውሳት ነው:: የሌሎችም ቅዱሳንን በዓል የምናከብረው በዚህ መንገድ ነው::

እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው:: ቅድስት ኤልሳቤጥን የጎበኛት ድንቅ ነው፤ የአገልጋዩን ድካም ያልዘነጋ ድንቅ ነው፤ ዘመን 
ካለፋቸው በኋላ በእርግና ዘመናቸው ዘር የሰጠ ድንቅ ነው እያልን ደስ ተሰኝተን የምናመሰግነው በቅዱሳኑ ላይ ድንቅን ያደረገውን 
እግዚአብሔርን ነው::/መዝ.68፥35/ “ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር 
እርሱ ይዘምር።” ተብሏልና:: /ያዕ.5፥13/:: ልደተ ቅዱሳን የደስታ የዝማሬ በዓላት ናቸው:: የእግዚአብሔር ወዳጆች ቅዱሳን 
ጽናታቸው ይደነቅበታል፥ አምላካቸው ይመሰገንበታል፥ ትምህርታቸው ይነገርበታል:: ስለ ቅዱሳን በመናገር የሚጠፋ ጊዜ የለም ፤ 
ስለ ቅዱሳን መመስከርን አብነት የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስን ነው:: መጽሐፍ ቅዱስን እናውቃለን ለሚሉን በውስጡ የበርካታ 
ቅዱሳንን ልደት፥ እድገት፥ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ክብርና ጸጋ የሚመሰክር መጽሐፍ መሆኑን እንመሰክርላቸዋለን::

የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት በዜማ በግጥም በንባብም ቢሆን የምናወሳው መጽሐፍ የመሰከረለትን እውነት ነው:: መጥምቁ ዮሐንስ 
በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት በትንቢት ቃል “የአዋጅ ነጋሪው ቃል” ፤“የቃል ኪዳን መልእክተኛ”፤ “መንገድ ጠራጊ”፤ “በበረሃ የሚጮኽ 
ሰው ድምጽ” ወዘተ እያሉ አመስግነውታል:: መልአከ እግዚአብሔር ቅድስናውንና ክብሩን ሲናገር “ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ 
ቅዱስ ይሞላበታል፤” ፥“ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ብሎለታል ፤ ካህኑ ዘካርያስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ “አንተ 
ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤” እያለ አገልግሎቱን ገልጧል ፤ ጌታችንም “እርሱ 
የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥” ፤ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ 
አልተነሣም፤” ብሎ ሰማያዊ ክብሩን ገልጾለታል:: /ማቴ.11:11፤ ዮሐ.5፥35/:: ይገስጸው የነበረው ሄሮድስ እንኳን ሳይቀር 
“ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤” ተብሎ 
ተጽፏል:: /ማር.6፥20/:: የቅዱሳንን ሕይወት ማውሳት መጽሐፋዊ ነው፤ የምንለው በዚህ መንገድ ክብራቸውን፥ 
አገልግሎታቸውን፥ ቅድስናቸውን የምንመሰክር በመሆኑ ነው::

ቅዱስ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስል የነበረ ነቢይ ነው:: ዮሐንስ መጥምቅና ነቢዩ ኤልያስ አኗኗራቸው ለመናንያን አርአያ ምሳሌ የሚሆን 
ነበር:: ኤልያስ በበረሀ ኖሯል፥ ዮሐንስም እንደዚያው:: መምህራን ሲጠሯቸው መምህር ወመገስጽ ይሏቸዋል ኤልያስ አክአብን 
ኤልዛቤልን ገስጿል፥ ዮሐንስም ሄሮድስን ገስጿል:: የጽድቅ ምስክሮች ነበሩ ኤልያስ ስለ ናቡቴ፥ ዮሐንስ ስለ ሕገ እግዚአብሔር 
ተሟግተዋል:: ሌሎችም በርካታ ተመሳስሎ አላቸው፡፡ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን የልደቱን ዜና የተናገረው መልአክ 
“በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” በማለት መሰከረለት:: /ሉቃ.1፥17/:: በነቢዩ ኤልያስ በቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ሂደው 
ያገለገሉ መናንያንን ሰማእታትን ስውራንን ቅዱሳንን ሁሉ እነርሱን እንዳከበርን እናከብራቸዋለን:: ገድላቸውን ጽፈን ተዓምራቸውን 
ተናግረን ምስክርነታቸውን አጽንተን እንይዛለን:: የሕይወታቸውን የቃላቸውን የጽሑፋቸውን ትምህርት እንመሰክራለን:: ሕዝብ 
ደስ እንዲለው:: ለሕገ እግዚአብሔር የሚቀኑ ስለ ደሀ መበደል ስለ ፍርድ መጓደል የሚታገሉ ጻድቃን ይበዙ ዘንድ በኤልያስ መንፈስ 
በዮሐንስም መንገድ የሚመጡ ጻድቃን ለማፍራት ይረዳልና::/ምሳ.29፥2/::

የቅዱሳንን በዓል ማክበር የሚጠቅመው በረከታቸውን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የቅዱሳኑን ትምህርት ለመያዝም ነው:: በዓለ ቅዱሳን 
ሲከበር ትምህርታቸውም ይዘከራል:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትምህርቶች በአራቱም ወንጌላውያን ተዳሰዋል:: የመጥምቁ ታላላቅ 
ትምህርቶች በሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ:: የመጀመሪያ ትምህርቱ የንስሐ ጥሪ ነው:: ሕዝቡ እንዲመለሱ ይሰብካል ፥ 
ደንዳና ልብ የነበራቸውን እንደ ሄሮድስና የአይሁድ መምህራን ያሉትን ይገስጻል:: ይህ ትምህርቱ ዘመኑን እየዋጀ በየዘመናቱ የሚነሱ 
ምእመናንን ሕይወት ለማነጽ ይጠቅማል:: ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ለመጡ ለሕዝቡ ቸርነትን ስለ ማድረግ፥ ለቀራጮች ስለ እውነት 
ሚዛን፥ ለጭፍሮች ስለ ፍትሕ፥ . . . ያስተማራቸው ትምህርቶች ዘመናትን እየተሻገሩ የሚመክሩ ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ ናቸው::/
ሉቃ.3፥11-14/:: የንስሐ ትምህርት ተግሣጽና ምክር ይሰጣል:: ከመጥምቀ መለኮት ከቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት የተወሰደ ነው:: 
በዚህምክንያት ነው በዓለ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናባቸው፥ የሚነገርባቸው፥ የሚተረጎምባቸው 
ናቸው የምንለው::


ሁለተኛ ነገረ ሥጋዌ ላይ ያተኮረው ትምህርቱ ነው:: መጥምቁ ዮሐንስ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን ሲያስረዳ መሲህ ይመጣል 
ተብሎ በነቢያት የተነገረው በጌታችን መፈጸሙን አስረግጦ የተናገረ መምህር ነው::/ዮሐ.1፥29-36/:: የዓለም መድኃኒት መሆኑንም 
ከመልአኩ ቀጥሎ የመሰከረ ነቢይ ነው:: “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” ብሎታልና:: በሥጋ ልደት 
ቢቀድመውም ለመለኮት ዘመን አይቆጠርለትምና ቅድመ ዓለም የነበረ ሕልውናውን “ከእኔም በፊት ነበር” ሲልም መስክሯል:: 
የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን ምስክርነት ልዩ የሚያደርገው ነገርም አለ:: ምስክርነቱ የእውቀት ብቻ አይደለም:: በዮርዳኖስ ባሕር ቆሞ 
ጌታውን ሲያጠምቅ ሰማይ ተከፍቶ ያየ የእግዚአብሔር አብን ምስክርነት የሰማ የምስጢር ሰው ነው:: አይሁድን ያሳፈረበት ትልቁ 
ምስክርነቱም “እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” የሚለው ነው:: የነገረ ሥጋዌ ትምህርቱን 
ሲደመድም “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ 
ሕይወትን አያይም።” ሲል የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን በሚገባ አስረድቷል:: /ዮሐ.3፥25-36/:: ጌታችንም የምስክርነቱን 
እውነትነት “እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል።” በማለት ገልጿል:: /ዮሐ.5፥33/:: በዓለ ቅዱሳን 
በጠቅላላ ነገረ እግዚአብሔር የሚነገርባቸው፥ ትምህርተ ሃይማኖት የምናጠናባቸው፥ ታሪከ ቤተ ክርስቲያን የሚዘከርባቸው በዓላት 
ናቸው::

በአጠቃላይ በዓለ ቅዱሳንን አታክብሩ ማለትን የሚያህል የወንጌል እንቅፋትነት የለም:: ጌታችን ባለሽቱዋ ማርያም በንስሐ እንባ 
አጥባ ሽቱ ቀብታ መልካም አድርጋለችና ለውለታዋ መታሰቢያ ሲያቆም “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ 
በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።” ካለ:: /ማቴ.26፥13/:: ስለ 
ስሙ እስከ ሞት ድረስ ለተደበደቡ፥መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ፥ በእስራትና በወኅኒ ለተፈትኑ፥ በደንጊያ ተወግረው ለሞቱ፥ በመጋዝ 
ለተሰነጠቁ፥ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ለተቅበዘበዙ . . . ወዳጆቹማ እንዴት ያለ 
መታሰቢያን ይሰጣቸው? የወንጌል ትምህርት ለሚተረጎምባቸው አብነቶችማ እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ቅዱሳን ሥርዓታዊና ትውፊታዊ በሆኑ መንገዶችም ይዘከራሉ:: ሥርዓታዊው መንገድ ገድልና 
ተዓምር መጻፍ፥ ድርሳንና መልክ መድረስ፥ በስማቸው መቅደስ መሰየም፥ . . . ናቸው:: ትውፊታዊውም “ማንም ከእነዚህ 
ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” ከሚለው 
አማናዊ ቃል ኪዳን ለመሳተፍ በቅዱሳኑ ስም ጸበል ጸዲቅ ማድረግን የመሰሉ ናቸው:: በመጥምቁ ዮሐንስ ስም የሚሰበሰቡ 
ወዳጆቹም ገድሉን አንብበው፥ ተዓምሩን ተናግረው፥ ለነዳያን መጽውተው፥ ሰማእቱን ያዘክራሉ:: በልደቱ የወላጆቹን ሐዘን ያራቀ 
በምልጃው ለሚተማመኑ መታሰቢያውን ለሚያደርጉ ወዳጆቹም ደዌያቸውን እያራቀ መንፈሳዊ ደስታን ያለብሳቸዋል::

የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የልደቱ ረድኤትና በረከት አይለየን: