. ቅ/ሲኖዶሱ የአስታራቂ ኮሚቴውን ሪፖርት አዳምጧል::
. ሦስት የአስታራቂ ኮሚቴው አባላት አዲስ አበባ ናቸው::
. ቅ/ሲኖዶሱ አካሄዱን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ቡድኖችን እንደማይታገሥ አስታውቋል::
. ከፓትርያርክ ምርጫ ይልቅ በመሠረታዊ መዋቅራዊ ችግሮቻችን ላይ መግባባት ለሚፈጥሩና ለተግባራዊ ለውጥ ለሚያነሣሱ ሚዲያዊ ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል::
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 29/2004 ዓ.ም፤ September 4/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ቅዱስ ሲኖዶስ መጪው ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ሰላሟንና አንድነቷን የምታረጋግጥበት፣ ዐበይት ተቋማዊ ችግሮቿን በመፍታት ለአገራችንና ለመላው ዓለም ሐዋርያዊ አገልግሎቷን የምታጠናክርበት ይኾን ዘንድ ካህናትና ምእመናን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር የሚያመለክቱበትና ከመስከረም 1-12/2005 ዓ.ምየሚቆይ የሱባኤ ጊዜ ማወጁ ታወቀ፡፡ የሱባኤ ጊዜ እንዲታወጅ የተወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ ትናንት፣ ነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ሲሆን ዛሬ ማክሰኞ ባደረገው ስብሰባም ቀናቱን ይፋ አድርጓል። (ዝርዝሩን እንደደረሰልን ለማቅረብ እንሞክራለን።) ሱባኤውን የተመለከተ መግለጫ በተከታዮቹ ቀናት በቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊው በኩል እንደሚሰጥም ተመልክቶ ነበር፡፡ በመንፈሳዊው ትውፊታችን እንደቆየን ወደ አዲሱ ዘመን የምንሸጋገርባትና እንደ 13ኛ ወር የምትቆጠረው ጳጉሜን በበርካታ ክርስቲያኖች ዘንድ የፈቃድ ጾም የሚያዝባት ወቅት እንደኾነች ይታወቃል፡፡