Tuesday, 4 September 2012


ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጀው የሁለት ሱባኤ የምሕላ ጸሎት


  • ለአገራችን መልካም መሪ ለቤተ ክርስቲያናችንም ደገኛ አባት እንዲሰጥ ጸሎት ይደረጋል::
  • የተቀጸል ጽጌና መስቀል ደመራ በዓላት አከባበር ዝግጅት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል::
  • የአገር ሽማግሌዎች ቡድን በዕርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከቅ/ሲኖዶስ ጋራ ይወያያል::
  • ነገ ከሚጀመረው የማኅበረ ቅዱሳን ዐሥረኛ ጠቅላላ ጉባኤስ ምን እንጠብቅ?
 (ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 29/2004 ዓ.ም፤ September 4/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኅልፈተ ሕይወት ታውጆ የሰነበተውና ሀገሪቱን ማቅ ያለበሳት ብሔራዊ የሐዘን ቀን ካበቃና ሐዘኑን በተለያየ መንገድና በተለያየ መንገድ ሲገልጽ ለቆየው የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል  ወደ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴው እንዲመለስ ከተጠየቀ፣ ዝቅ ብሎ ሲውለበለብ የቆየው ሰንደቅ ዓላማ ወደ መደበኛ ከፍታው ከተመለሰ በኋላ ለሁለት ሱባኤ ያህል (ዐሥራ ሦስት ቀናት) የቆየው ብሔራዊ ሐዘን ማብቃቱ ከወደ ቤተ መንግሥት በተገለጸበት ዕለት የሁለት ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ ደግሞ ከቤተ ክህነት በኩል ታውጇል፡፡ ለሁለት ሱባኤ ማለትም ለዐሥራ አራት ቀናት የሚዘልቀው የጸሎተ ምሕላ ሱባኤ ጳጉሜን 1 ቀን 2004 ዓ.ም በዘመነ ዮሐንስ ተጀምሮ መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም በዘመነ ማቴዎስ የሚፈጸም ነው፡፡ የጸሎተ ምሕላው ሱባኤ የታወጀው በትናትናው ዕለት ተጀምሮ ዛሬም ቀጥሎ በዋለው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ነው፡፡


በዚህ የጸሎተ ምሕላ ሱባኤ ልዑል እግዚአብሔር ለአገራችን ኢትዮጵያ የሚበጃትን ርእሰ መንግሥትእንዲሰጣት፣ ለቤተ ክርስቲያናችንም አንድነቷን እንዲመልስና ለመንጋው የሚራራ ደገኛ ርእሰ አበውእንዲሰጣት ጸሎት ይደረጋል፡፡ በሊቁ አለቃ አያሌው አገላለጽ “ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የማትለይ÷ መቃድ ያልነካት፣ ስፌት ያልዞረባት የክርስቶስ ሥረ ወጥ ልብሱና መቅደሱ” ናትና ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በያሉበት በዚህ የሁለት ሳምንት የጸሎተ ምሕላ ሱባኤ  ስለውዲቱ አገራቸውና ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው መንፈሳቸውን ያስተባብራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዛሬው ዕለት የጸሎተ ምሕላው ሱባኤውን የተመለከተ ዝርዝር መግለጫ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንደሚሰጥ ተጠብቆ የነበረ ቢኾንም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው በገጠማቸው እክል ሳቢያ ለነገ መተላለፉ ተመልክቷል፡፡ ይኹንና በዛሬው ዕለት ረፋድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ለተሰበሰቡት መላው የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እንደተገለጸው ለሁለት ሳምንት በሚዘልቀው ሱባኤ በሁሉም ገዳማትና አድባራት በየዕለቱ በነግህ፣ በሠርክ ጸሎተ ምሕላ ይደረሳል፡፡ ዝርዝር መግለጫው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በኩል እንደወጣ የምናቀርብ ይሆናል፡፡

በዚሁ ስብሰባ ላይ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ - ሰላሌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚከበረው የተቀጸል ጽጌ በዓልና መስከረም 16 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ በመስቀል አደባባይ ለሚከበረው የመስቀል - ደመራ በዓል የሚደረገው ዝግጅት እንዲጠናከር አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል በዓመት አራት ጊዜ ታከብራለች፡፡ የመጀመሪያው ተቀጸል ጽጌ የሚባለውና በኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የጌታ ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ የገባበት በዓል የሚከበርበት ሲኾን በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን በብሔራዊ ደረጃ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚከበር ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና÷ በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሐቅ የሚመራው የአገር ሽማግሌዎች ቡድን (ጉባኤ) በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ ስለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋራ ሊመክር መኾኑ ተሰምቷል፡፡ ውይይቱ ሌሎች ተጨማሪ ልሂቃንን ሳያካትት እንደማይቀር የተነገረ ሲኾን በነገው ዕለት እንደሚካሄድም ተገምቷል፡፡ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ከጉዳዩ ጋራ አግባብነት ያላቸው ልሂቃን ከቀድሞም ጀምሮ እንደታየው ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት የበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ መዘጋጀታቸው በአሁኑ ወቅት ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት መጠበቅ ከዚህ የበለጠና የተለየ አጀንዳ እንደማይኖር ያመላከተ መኾኑ እየተነገረ ነው፡፡ “የዕርቀ ሰላሙ ውጤት አንድም ብዙም ሊኾን ይችላል፤ የፈለገው ቢሆን ዕርቀ ሰላም ሳይፈጸም የፓትርያርክ ሹመት ብሎ ነገር የለም፤ ወቅቱ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወርቃማ አጋጣሚ ሲኾን እኛም ወይ በሰላም አባትነት ወይ በዐመፀኝነት የምንፈረጅበት ይኾናል፤ ዕርቀ ሰላሙ ሳይፈጸም፣ ተቋማዊ ኹኔታችን ሳይሻሻልና ሳይለወጥ በአንዳንድ ወገኖች የሚደረገው ውትወታ ግላዊ ፍላጎትን ከማስፈጸም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፤” ይላሉ ለዜናው ምንጮች አስተያየታቸውን የሰጡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዐሥረኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነገ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ይከፈታል፡፡ እስከ ሰኞ ጠዋት እንደሚዘልቅ የሚጠበቀው ይኸው ጠቅላላ ጉባኤ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የተወከሉ የማኅበሩ አባላት የሚገኘበት ሲኾን በዋናነት በማኅበሩ የተልእኮ መፈጸሚያ ጠገግ ለአራተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ በመምከር እንደሚያጸድቀው ተሰምቷል፡፡ ሌሎችም የማኅበሩን አገልግሎት የሚገመግሙና የወቅቱን ጉዳዮች የሚመለከቱ ጥናቶች ለውይይት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡ እንዲህስ ከሆነ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ለቤተ ክህነቱ የሚያስፈልገውን ተቋማዊ ሽግግር በተመለከተ ማኅበሩ አስተዋጽዖውንና ሞያዊ ትሩፋቱን ትርጉም ባለው መልኩ ለማበርከት የሚያስችለውን ውሳኔ ያሳልፋል ብለን እናምናለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

ከጳጉሜን መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም አንድ ድረስ ሕዝቡ የወንዝ ውኃ ወዳለበት በሌሊት እየሄደ፣ ጠበል ነው እያለ የመጠመቅ የቆየ ባህል እንዳለው ይህም የአምልኮ ባዕድ መርዝ እስካልተቀላቀለበት ድረስ ነውር እንደሌለው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ጳጉሜን ጥቂት በማይባሉ ምእመናን ዘንድ ለአዲሱ ዓመት ቅድመ ዝግጅት የሚደረግባት የፈቃድ ጾም (በአንዳንዶች ዘንድ የወታደር ጾም ትባላለች) እንደሚጾምባት ይታወቃል፡፡
ጳጉሜን የተመለከተው ተከታዩ ጽሑፍ ሁለገቡና አንደበተ ርቱዕ ሊቅ አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ በሬዲዮ ያስተማሩትና በእጃቸው የጻፏቸው ትምህርቶች በልጃቸው ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ በተሰበሰቡበትና ለኅትመት በበቁበት “ለኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ” ከተሰኘው መጽሐፍ የተገኘ ነው፡፡ ለምንይዘው የጸሎተ ምሕላው ሱባኤ አጠቃላይ ግንዛቤ እንደሚሰጠን በማመን ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡
ጳጉሜን
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከነሐሴ በኋላ ጳጉሜን የምትባል አምስት ቀን አለች፡፡ ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፡፡ ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ኾናለች፡፡ ጳጉሜን የሚለው ስያሜዋ ግን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ መኾኑ በአበው ቃል ተነግሯል፡፡
“ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው ተብሎአል፡፡ በግእዝ ቋንቋችን ተውሳክ ማለት ነው፡፡ ተውሳክ ማለት ተጨማሪ ማለት ነው፡፡ “ወሰከ - ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ኤውሮፓዎች ጳጉሜን የወር ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጠር ሠላሳ ስናደርግ እነርሱ ሠላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከነሱ ብለው ደምረውታል፡፡
ሊቃውንቱ እንደ ሱባኤ ቀን ቀኖና እንዲፈጽምባት ለብቻ ለይተው አኑረውታል፡፡ “ይህ ዓለም ኑሮ፣ ኑሮ በመጨረሻ ያልፋል፡፡ ጌታ ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል” ሲሉ የገታ የመምጣቱ ነገር እንዲነገርባት፣ መሥዋዕት እንዲሠዋባት፣ ጾም እንዲያዝባት፣ ምጽዋት እንዲመጸወትባት ለይተው መድበዋታል፡፡
ሕዝቡ ሳይቀር “ጳጉሜን ዕድሜ ትሰጠናለች፤ በኋላም ታድነናለች” ብለው ጾም ይጾሙባታል፡፡ የዚሁም ማስረጃ በቅዱስ መልከ ጸዴቅ ድርሳን ይገኛል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ የጾም ሥርዐት ይፈጽሙባት ነበር፡፡ ሌሎችም ሽማግሌዎችና ባልቴቶች አክብረው ይጾሙባታል፡፡ ኾኖም የጳጉሜን አቆጣጠር አንዱ ከወር ጋራ፣ ሌላውም ከዓመት ጋራ ቢያደርገውም በሀሉም አቆጣጠር ውስጥ ሕያዊት ኾና መገኘቷ የታወቀ ነው፡፡
የነቢዩ ኄኖክ መጽሐፍም የዓመቱን አቆጣጠር ሦስት መቶ ስድሳ አራት አድርጎ ገልጦታል እንጂ ጳጉሜን ጨርሶ አልዘነጋትም፡፡
ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment