በዓለ መከር(በዓለ ሠዊት)-በዓለ ኀምሳ
የክርስቲያኖች በዓለ ኀምሳም አከባበር በዚሁ ቢቀጥልም እኛ ዘንድ ግን በዚሁ መንፈስ ተጠብቆ አልደረሰም፡፡ ደርሶንማ ቢሆን ኖሮ በዓለ ኀምሳችን እንደዚያ ዘመን ሰዎች ፈቃደ ሥጋችንን ገድለን የመንፈስ ፍሬ አፍርተን ለእግዚአብሔር ቁርባን የሚሆነዉን ቀዳምያት የምናቀርብበት በዓል ሊሆን ይገባዉ ነበር፡፡ ነገር ግን የዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበዉ እንደ ሐዋርያት ያመኑ ምእመናን ነዉ ወይስ ሌላ ብለን ስንጠይቅ ኅሊናችን የሚነግረንን መልስ እናዉቀዋለን፡፡ የሐዋርያት ታዛዦችና በሥራ የሚላላኳቸዉ በጸጋ የከበሩ ሀብተ ፈዉስና ተአምራት የተሰጣቸዉ አርድእትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በእኛ ዘመን ባለችዉ በእኛ ቤተ ክርስቲያንስ? እነዚያ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይማከሩ ነበረ የእኛስ ዘመን መሪዎች ከየትኛዉ መንፈስ ይማከራሉ? የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች በርግጥም እንደ ጥንቱ ሰዉን ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሚያበቁ አባቶችና መምህራን ናቸዉ ወይስ ለገንዘብ፣ ለክብርና ለዝና እንዲሁም ለሌሎች ጥቅሞች የሚራኮቱ ስግብግቦች? በልሳኖች እስኪናገሩ ድረስ በጸጋ የከበሩ አገልጋዮች ወይስ ሁሉንም ነገር ለገነዘብ ማግኛ ሊያዉሉት የሚሯሯጡ ሲሞኖች? በርገጥ አሁን ለክርስቶስ እያቀረብነዉ ያለዉ ምንድን ነዉ? የመንፈስ ፍሬዎችን ወይስ የሥጋ ፍሬዎችን? ሺዎችን አንድ እናደርጋለን ወይስ ጥቂቶቹንም እንከፋፍላለን? ሌሎች የዘሩትን በእነርሱ ተገብተን እንደ ሐዋርያት እናጭዳለን ወይስ የሰበሰቡትንም እንበትናለን? የሚያቀርቡትና የሚያማክሩትስ እነማንን ነዉ? እንደ ጳዉሎስ ሲላስን ወይስ እንደ ባላቅ በለዓምን? እንደ ሐዋርያት እመቤታችንን ወይስ እንደ አክዓብ ኤልዛቤልን?ፈርዖን በዮሴፍ ናቡከደነጾርም በዳንኤል ሲጠቀሙ እነ ሳዖል ወደ ምዋርተኛዋ ሴት መሔዳቸዉ ለምን ይሆን? ወይ ተገላቢጦሽ!!!በርግጥም ያሳስባል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ባወቀ ከኤልያስ እንኳ የተሰወሩ ቅዱሳን እንደነበሩ ሁሉ አሁንም በየ አጥቢያዉ እንደ አልባሌ የሚቆጠሩ እንደ ደንቆሮም የሚታዩ ንጹሐን አገልጋዮች በየገዳሙና በየመናብርቱም አባቶች አይጠፉም፡፡
አብዛኛዉን ስናየዉ ግን በርግጥም ቤተ ክርስቲያን በዓለ ኀምሳን እያከበረች ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡ በዓለ ኀምሳ የፍሬ በዓል እንጂ የገለባ በዓል አይደለም፡፡ የአንድነት እንጂ የመለያየት በዓል አይደለም፡፡ የትሕትናና የጸጋ በዓል እንጂ የዐመጻና የኃጢኣት በዓል አይደለም፡፡ ወንጌልና የምሥራች የሚታወጂበት እነጂ ደባና ተንኮል እንደ ዘሃ የሚዘጉበት በዓል አይደለም፡፡ የቅንነትና የጽድቅ በዓል እንጂ የመሠርይነትና የወንጀል በዓል አይደለም፡፡ እዉነቱን እዉነት ሐሰቱን ሐሰት በሉ ተብለናልና እስኪ በእዉነትና በቅንነት ቤታችንን እንመርምረዉ፡፡በከበረዉ መንፈሳዊ ሀብታችን ማኅሌቱ ቢቆምም ኪዳኑ ተደርሶ ቅደሴዉ ተቀድሶ ብንመለስም የጸጋ ፍንጣሪ ቀርቶ የእርቅ ወሬ አይሰማም፡፡ ከቶ ለምን ይሆን ይህ ሁሉ የሐስትና የአስመሳይነት ሕይዎት እንዲህ የነገሰዉ?
ታዲያ እኛ ያቀረብንለት እሸት የምንድን ነዉ? ‹‹የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ›› /ዘጸ 34፣ 22 / ተብሎ እንደ ተጻፈዉ ስንዴ ነዉ ወይስ ኩርንችት? እኛ እጂ ላይ የሚታየዉ ፍሬ የወይኑ ዘለላ፣ ወይም የገብስ ዛላ ወይም የባቄላ ነዶ ወይስ እሾህና አለብላቢት? ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰዉ የሚዘራዉን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል›› /ገላ 6፣7/ ይላል፡፡ ስለዚህ እኛም ሁላችን የምናጭደዉ የዘራነዉን ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በእዉነት እንዴት ይህን ሁሉ ዐመጻና ጥፋት እናጭዳለን? ይህ የአሁኑ ሌብነትና ዝርፊያ ማንአለብኝነትና ሥርዓት አልበኝነትስ ደግሞ ምን ያፈራልን ይሆን? ለቤተ ክርስቲያን ተቆረቆርን የምንለዉስ ከእዉነት ይሆን ወይስ በሥጋ ገበያ ስለተበለጥን? መጽሐፍ ‹‹ ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ›› /ኤር 4፣ 4/ በማለት ቅናታችን ሥጋዊ ሀሳባችንም ምድራዊ እንዳይሆን፤ ይልቁንም በብልጣብልጥነትና በተጥባበ ነገር ፣ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳሉ በምንላቸዉም መጥፎ ነገር እንኳ ሳንመኝ እንድነፈጽመዉ ያዝዘናል፡፡ ክፉ በምንላቸዉ ሁሉ ላይ ክፉ የምንመኝ አንዳች መጥፎ ነገር በመፈጸም መልካም የሚመጣ የሚመስለን እንዳንኖርም ያሰጋል፡፡ ሐዋርያዉ ‹‹ በገዛ ሥጋዉ የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳል›› /ገላ 6፣8/ እንዳለ መዓቱን እየጨመርን የመከራችንን ዘመን እናረዝመዉ እንደሆን እነጂ ዕርቅና ሰላምን፣ በረከትና ጸጋን ልናገኝ አንችልም፡፡ በተቀመጥንበት ቦታና በሚመስለን ነገር ልናጠቃዉም በምንፈልገዉ ሰዉ ተለያየን እንጂ በክፉ ሀሳብ አልተበላለጥንምም ማለት ነዉ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ለሰዉ ፊት አያዳላምና መቅሰፍቱን በጋራ ያካፍለናል፡፡
እኛ ምእመናኑም ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እነዚያ የጥንቶቹ አማኞች ቀዳምያታቸዉ ምን ነበር? መጽሐፍ ስለ እነርሱ ‹‹ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸዉ›› /ሐዋ 4፣33/ ይላል፤ እኛስ? ፍሬያችንስ ከመንፈስ ነዉ ወይስ ከሥጋ? እስኪ ራሳችንን እንመርምረዉ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነዉ የምንቀርበዉ ምንድን ነዉ? ጥል፣ ክርክር፣ ቁጣ፣ አድመኛነት ወይስ በጎነት፣ የዉሃት ፣ ራስን መግዛት? ወሬና ሐሜት ወይስ ፍቅርና መተሳሰብ? ….. ከቶ ምንድን ነዉ? የመንፍስን ፍሬዎች ወይስ የሥጋን ፍሬዎች? የቤተ ክርስቲያንን ሥራ በእልህና በዐመጻ እሠራለሁ ብሎ መነሣት ለኣማኝ በእሳት እንደ መጫዎት ያለ ነዉ፡፡ በተሳሳተ መንገድና በሥጋዊ ሃሳብ አሸናፊ በመሆን እግዚአብሔርን ለማገልገል መነሣትም አንተ ያሳየኸን መንገድ የተሳሳተ ነዉ ብሎ ጌታን እንደመዉቀስ ያለ ነዉ፡፡ መንፈሳዊ ነገርን በሥጋዊና ግልፍተኛ በሆነ ስሜት ለመሥራት እንደመነሣት ያለም ጎጂ ነገር የለም፡፡ ይህማ ቢቻል ኖሮ ቅዱስ ጴጥሮስ የ ማልኮስን ጆሮ በመቁረጡ አይወቀስም ነበር፡፡ እግዚአብሔርን በጉልበት እናግዝህ ማለት ነዉና እጂግ ጸያፍ ነዉ፡፡ይህን ለሚያደርጉ ‹‹ኃይል የእግዚአብሔር ነዉ እያሉ›› መዘመርም አይቻልም፡፡ ለእኛ ከሚያስፈልገዉ ዉጭ የኃይል እርምጃ የሚያስፈልጋቸዉ ካሉም እግዚአብሔር መንገድ አለዉ፡፡ ሐዋርያዉ ስለ ባለ ሥልጣን ሲጽፍ ‹‹በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቁጣዉን ለማሳየት ክፉ አድራጊዉን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነዉና›› /ሮሜ 7፣4/ ያለዉ ይህንኑ ያመለክታል፡፡
እንግዲህስ እግዚአብሔር ይቀበልልን ዘንድ ሰዉነታችን የተቀደሰ አድርገን እናቅርብ፡፡ በእዉነት ሁላችንም ተመሳሳይ ባንሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ነገር ሊፈጸም አይችልም ነበር፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በዐመፃ ተካከልን፤ በበደልም ተመሳሰልን፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር የሚያስፈርድ ሊገኝ አልቻለምና በሥጋ የዘራነዉን በሥጋ ለማጨድ ተገደድን፡፡ ስለዚህ ፈጥነን እንመለስ፡፡ ልቡናችንን አለስልሰን ፣ ንጹሑን ዘር ቃለ እግዚአብሔርን አብቅለን ለፍሬ እናብቃዉ፡፡ ያን ጊዜ እኛም በዘመነ ሐዋርያት እንደነበሩት ሰዎች ለመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የምንቀርብ ቀዳምያት ለሰማዕትነትም የምንመረጥ ባለመቶዎች ለመሆን እንበቃለን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡