ከአዲስ ጉዳይ መጽሄትቅጽ 6 ቁጥር 136 ጥቅምት 2005 ዓ.ም
- “እኔ ችግር ያለብኝ ‹እናቴ አልዳነችም› ማለታቸው ላይ ነው ፤ እንደዚህ ማለታቸው ሌሎቹም ሁሉ እንዳልዳኑና እሳቸው ብቻ እንደዳኑ የሚያረጋግጥ ሃሳብ ነው፡፡” ፕሮፌሰር መስፍን
- አቶ ኃ/ማርያም ለቀድሞ ጠ/ሚኒስትር “ዘላለማዊ ክብር እመኛለሁ” ማለታቸውን እንደተጸጸቱበት ተናግረዋል፡፡
- “እናቴ አልዳነችም” ብለው መናገራቸው ራሱ በጣም የሚያሳዝንና ሞኝነት ጭምር ነው፡፡ ይህ እኮ ሁላችንም ማለትም ኦርቶዶክስም ፤ ሙስሊሙና ካቶሊኩ በሙሉ አለመዳናችንን የገለጹበት ቀላል አሽሙር ይመስለኛል” ዶ/ር ያእቆብ
- “አቶ ኃይለማርያም የአቶ መለስን ራዕይ ለማስጠበቅና በሃይማኖተኛነት መካከል እየዋለሉ የሀገሪቱን ሕገ መንግስት ሊጥሱ ይችላሉ” ዶ/ር ያእቆብ
- ዛሬ ስለ ሃይማኖት መጠቃቀስ የጀመሩት የአገር መሪ ነገ ደግሞ ስልጣናቸውን ተጠቅመው እግዚአብሔርን ማገልገል በሚል ሰበብ ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት ምን ያዳግታቸዋል?
(አንድ አድርገን ጥቅምት 27 2005 ዓ.ም)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ከተረከቡ ወዲህ ህዝብ ስለ እኚህ አዲሱ መሪ ስብዕና የተለያዩ አስተያየቶችንና ቅድመ ግምቶችን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል ፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ በተለይም የህትመት ሚዲያው እንዲሁም ድህረ ገጹ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የፖለቲካ ብቃትና የፊት ለፊት ተግዳሮቶች ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት በመረጃና ትንተና ላይ ተመርኩዘው ለንባብ አብቅተዋል ፡፡ ሰውየው ወደ ስልጣን ከወጡ ብዙም ጊዜ አላለፈምና አሁንም አዲስ ተብለው ቢጠሩ አይገርምም ፤ አዲስ ነገር ደግሞ ሁሌም በውስጡ የሚነገር ወሬ አያጣውም ፡፡ አዲስ ጉዳይ እስከ አሁን ስለ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለንባብ ካበቃቻቸው ጉዳዮች ውስጥ የዛሬውን ርዕሰ ጉዳይ ለዳሰሳ መርጦት አያውቅም፡፡ ይህም የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከተሉት ሃይማኖት የግል በመሆኑና ይህም እምነታቸው በፖለቲካ ህይወታቸው ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ለንግግር የሚያበቃ ጉዳይ እስካልፈጠረ ድረስ ነገሩ እንደ አንድ ጉዳይ አንስቶ ማራገብ ፋይዳ የለውም ተገቢም አይደለም በሚል እምነት ነው፡፡