Wednesday, 26 March 2014

የ‹‹አክራሪነትና የጽንፈኝነት›› ታፔላ ለጠፋ ከምን ተነሳ ? አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?

(አንድ አድርገን መጋቢት 17 2006 ዓ.ም)፡- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት ከማለፋቸው በፊት በመጨረሻ የፓርላማ ቆይታቸው ላይ ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ የተናገሩት ነገር ነበር ፤ ነበሩ ሳይባሉ በፊት የመንግሥታቸውን አቋም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህዝቡ አስተላልፈዋል ፤ ይህን ንግግር ከተናገሩ በኋላ ግን ዳግም ለ20 ዓመት በተቀመጡበት የፓርላማ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ሳናያቸው ወደ ማይቀረው መንገድ ተጉዘዋል ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እሳቸው ከመናገራቸውም በፊትም ሆነ በኋላ መንግሥት ስለ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ጉዳይ በ”አዲስ ራዕይ” መጽሔት ፤ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በብቸኛው የመንግሥት እስትንፋስ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብዙ ነገሮችን ብሏል ፤ ዘጋቢ ፊልምም እስከ መሥራት ደርሷል፡፡ ያለፈውን አንድ ዓመት የመንግሥትን ዝምታ መሰረት አድርገው መንግሥት ይህን አቋም የቀየረ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ሳይታሰብ የተከሰተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላ የሀዘን ጊዜው በመርዘሙ የተነሳ ቀድሞ አቋም የተያዘባቸው አጀንዳዎች ሳይራገቡ ተከድነው መቆየታቸው እንጂ በመንግሥት በኩል አቋሙን የለወጠበት ነገር አልተመለከትንም፡፡ ገዥው ፓርቲ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ያንጸባርቁትን አቋም ሳይቀንስ ሳይጨምር ለማስቀጠል እየሰራ ይገኛል ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በተሰየሙበት እለት “እናስቀጥላለን” ብለው ነበር የተናገሩት፡፡ እስኪ ይህ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ታፔላ ለጠፋ ጉዳይ የመንግሥት አቋም ከምን ነጥብ እንደተነሳ ፤ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንቃኝ…