Wednesday, 26 March 2014

የ‹‹አክራሪነትና የጽንፈኝነት›› ታፔላ ለጠፋ ከምን ተነሳ ? አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?

(አንድ አድርገን መጋቢት 17 2006 ዓ.ም)፡- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት ከማለፋቸው በፊት በመጨረሻ የፓርላማ ቆይታቸው ላይ ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ የተናገሩት ነገር ነበር ፤ ነበሩ ሳይባሉ በፊት የመንግሥታቸውን አቋም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህዝቡ አስተላልፈዋል ፤ ይህን ንግግር ከተናገሩ በኋላ ግን ዳግም ለ20 ዓመት በተቀመጡበት የፓርላማ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ሳናያቸው ወደ ማይቀረው መንገድ ተጉዘዋል ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እሳቸው ከመናገራቸውም በፊትም ሆነ በኋላ መንግሥት ስለ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ጉዳይ በ”አዲስ ራዕይ” መጽሔት ፤ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በብቸኛው የመንግሥት እስትንፋስ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብዙ ነገሮችን ብሏል ፤ ዘጋቢ ፊልምም እስከ መሥራት ደርሷል፡፡ ያለፈውን አንድ ዓመት የመንግሥትን ዝምታ መሰረት አድርገው መንግሥት ይህን አቋም የቀየረ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ሳይታሰብ የተከሰተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላ የሀዘን ጊዜው በመርዘሙ የተነሳ ቀድሞ አቋም የተያዘባቸው አጀንዳዎች ሳይራገቡ ተከድነው መቆየታቸው እንጂ በመንግሥት በኩል አቋሙን የለወጠበት ነገር አልተመለከትንም፡፡ ገዥው ፓርቲ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ያንጸባርቁትን አቋም ሳይቀንስ ሳይጨምር ለማስቀጠል እየሰራ ይገኛል ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በተሰየሙበት እለት “እናስቀጥላለን” ብለው ነበር የተናገሩት፡፡ እስኪ ይህ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ታፔላ ለጠፋ ጉዳይ የመንግሥት አቋም ከምን ነጥብ እንደተነሳ ፤ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንቃኝ…
ግንቦት 2004 ዓ.ም ‹‹አዲስ ራዕይ›› መጽሔት ልዩ ዕትም እንደመነሻ

አዲስ ራዕይ በየሁለት ወሩ በአማርኛ ቋንቋ እየተዘጋጀች በኢኮኖሚያዊ ፤ ፖለቲካዊ ፤ ማህበራዊ ፤ ዓለም ዓለማቀፋዊና ፤ ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራያና ትንታኔ ይዛ የምትቀርብ የኢህአዴግ የትንታኔ መጽሄት ነች፡፡ የዚች መጽሄት አዘጋጅ “የኢህአዴግ ህዝብ ግንኙነት ክፍል” ሲሆን መጽሔቷ ድርጅታዊ እና መንግሥታዊ አቋም የምታንጸባርቅ ነች ፤ በርካታ የክስ ዶክመንተሪ በኢቲቪ እና በኢህአዴግ ሕዝብ ግንኙነት ሰዎች ሲሰራ በርካታ ግብዓቶችን መስመር በመስመር ጋዜጠኞቹ እንዲያነቡ የሚገደዱት ከአዲስ ራዕ መጽሔት ነው፡፡ ይች መጽሐሔት ግንቦት 2004 ዓ.ም ይዛ የወጣችው ጽሑፍ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ላይ የመንግሥትን አቋም በግልጽ አስቀምጣለች፡፡ በመጽሔቷ በጊዜው የሰፈረው ይህን ይመስል ነበር፡-
በተመሳሳይ አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሌላው ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸው ክርስቲያኖችንም ቢሆን የሚከተሉትን እምነት ክርስትና ትክክል አይደለም ብለው ከማመን አልፈው ፤ እነዚህ ተለየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች እምነታቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ በተለያየ ሽፋን ማፈን ይከጅላቸዋል፡፡
“በክርስትና ውስጥም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በተለይ ከማኅበረ ቅዱሳንም የተወሰኑ ከመሰረታዊ የእምነቱ አስተምህሮ ፈንጠር ያሉ እና በመሰረቱ ጸረ-ሕገመንግሥት መገለጫ ያላቸው አቋሞች የተላበሱበትና አንዳንድ የእኛ አባላትና አመራሮችም ኢህአዴግነትንም ጸረ ኢህአዴጋዊ አቋሞችን የያዙ ይዘቶችንም የሚያንቀሳቅሱበት ሁኔታ በገሀድ የሚታይ ነው፡፡ አባላችን ወደ ሃይማኖት ሲሄድ ኢህአዴግነቱን ትቶ ፤ ወደ ኢህአዴግ ሲመጣ ደግሞ ሃይማኖቱን ትቶ ሊሆን አይችልም ፡፡ ጠንካራ አማኝም ጠንካራ ኢህአዴግም በመሆን መካከል ግጭት የለም ፡፡ ግጭት የሚፈጠረው ድንበሮችን ስናደበላልቅ ነው፡፡ ስለዚህም በዚሁ አግባብ ግልጽነት ተፈጥሮ አባላችንን አመራራችን ሰልፉን ያስተካክል ፤ ለማስተካከል የሚቸገር ደግሞ በሰበባ ሰበብ ሳይሸፋፈን ከድርጅቱ መጽዳት አለበት”
“የዲሞክራሲ ስርአታችን መንግሥትንና ሃይማኖት መለያየት እንዳለባቸውና አንዱ በሌላው ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይገባው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ዲሞክራሲ ብሎ ነገር በፍጹም የማይታሰብ ነገር መሆኑን ያረጋግጣል ፡፡ የሃይማኖት አክራሪነት የምንለው ይህንኑ መሰረታዊ የዲሞክራሲ መርህ በሃይማኖት ሽፋን መናድ ነው ፤ ይህው አመለካከት በተለያየ መልኮች ሊገለጽ ይችላል፡፡ ሰፊ ቁጥር ባይኖራቸውም ጥቂት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እንደ ድሮ ሁሉ ኦርቶዶክስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን ፤ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት ከሚል ቅዥት ባለፈ “አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት” የሚል መፈክር ደረታቸው ላይ ለጥፈው ለመሄድ እንኳን ሀፍረት የማይሰማቸው ሆነው በአደባባይ ይታያሉ፡፡ ከሌሎች የተለየ መብትና ጥቅም እንዲኖረው ይመኛሉ፡፡ ይህ አመለካከት ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የከሰመ ቢሆንም አክራሪነት የሚገለጽበት አንዱ ገጽታ መሆኑ አልቀረም ፡፡
አዲስ ራዕይ ላይ አክራሪዎችና ጽንፈኞችን በአንድ አንቀጽ አንዲህ ብሎ ይገልጻቸዋል “ሁል ጊዜም ጽንፈኞች ማንኛውም ሰው በሚከተለው እምነት የግል መብት የለውም ብለው ያምናሉ ፡፡ ውይይትና መግባባት ፤ ሰላማዊ ውይይትን በማውገዝ በአመጽ ተደግፈው የራሳቸውን አተያይ ይጭናሉ ፡፡ ከፍቅር ጥላቻን ፤ ከርህራሄ ጭካኔን ፤ ከመቻቻል መናቆርን ፤ ከእውቀት ድንቁርናን ፤ ከውይይት ጉልበትን ይመርጣሉ ፤ ያበረታታሉ ፡፡ ጽንፈኞች የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን አይቀበሉም ፤ ይልቅ እነሱ እምነት የተለየ የበላይነት እንዲኖረውና መንግሥታዊ ድጋፍ ጡንቻ እንዲኖረው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ አመለካከት በተለያዩ የእስልምና እና ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ በመሸጉ የተወሰኑ ቡድኖች የሚስተዋልና በተለያየ መልክና ደረጃ የሚንጸባረቅ ነው፡፡”
እኝህን የመሰሉ በርካታ አክራነትንና ጽንፈኝነትን መሰረት አድርገው የተቀመጡ ሃሳቦች ተስተናግደውባታል ፤ ይህ ማለት ከሁለት ዓመት በፊት የነበረ የመንግሥት አቋም ነው፡፡ ይህን አቋም የሚያስለውጥ አንዳች ነገር በመሃል ሲደረግ አልተመለከትንም ፤ ከዚች መጽሄት ህትመት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስሩ በፓርላማ ተገኝተው መንግሥታቸው በዚህ ዙሪያ ላይ ምን አቋም እንዳለው እና ምን አይነት አመለካከትን እንደሚከተል ለእርሳቸውና ለፓርላማው የመጨረሻ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል ፡፡

የአቶ መለስ የመጨረሻ የፓርላማ ንግግር

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አሁን ላለንበት ሁኔታ መነሻ ባይሆንም ነገሩን ወደ ሌላ ምዕራፍ ያሸጋገረ ንግግር እንዳደረጉ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ከዚያን በፊት የግንቦት ወር አዲስ ራዕይ መጽሄት እና ከዚያን በፊት የነበሩ እትሞች ለጉዳዩ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድገዋል ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሉት ላይ ሳይጨመር ቃል በቃል ይህን ይመስል ነበር ፡፡

“መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ፤ መንግስሥት በሃይማት ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገባም ፤ ሃይማኖት በመንግሥት ሥራ ላይ ጣልቃ አይገባም ፤ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት ማራመድ ይችላል ፤ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህ ግልጽ ነው ፤ ማንኛውም ዜጋ ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት ፤ በዚህ መሰረት ነው ሁኔታዎችን የምናየው ፤ በዚህ አኳያ ስናየው በተለያዩ ሃይማኖቶች የተለያዩ የጽንፈኝነት አካሄድ እናያለን ፤ ከክርስትና አኳኋን የጀመርን እንደሆነ ምናልባት የምክር ቤት አባላት ልብ አላላችሁ ይሆናል ፤ ጥምቀት ላይ አዲስ አበባ ከነበሩት መፈክሮች አንዱ ጸረ ህገ መንግሥት ነው ፤ ከነበሩት መፈክሮች አንዱ “አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት” የሚል ነው ፤ ይህን መፈክር የያዙ ጥቂቶች ናቸው ፤ አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት የሚል ሕገ-መንግሥት የለንም ፤ ሕገ መንግሥቱ የሚለው አንድ ሀገር የፈለገው አይነት ቁጥር ያለው ሃይማኖት ነው ፤ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ የክርስቲያን መንግሥት እንዲኖር እና ሕገ መንግሥቱን ከዚህ አኳያ ለመሸርሸር የሚፈልጉ በጣም ጥቂቶችም ቢሆኑ እንዳሉ ያሳየናል ፤ እነዚህ በአብዛኛው የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰዎች ናቸው ፤ እና በማስተማር ሊመለሱ የሚችሉ ናቸው ፤ ስለ ሕገ-መንግሥቱ ትምህርት በመስጠት የሚመለሱ ናቸው ፤ እድሉ ሲገኝ ሕገ-መንግሥቱን በማስረዳት በማሳመን ሊመለሱ የሚችሉ ናቸው ፤ የሃይማት መሪዎቹ ራሳቸው ሲያስተምሯው ይመለሳሉ ብለን እናስባለን ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በእስልምና እምነት ዙሪያ በሀገራችን ለረዥም ጊዜ የቆየ ነባር የእስልምና እምነት አለ ፤ በሀገራችን የሚገኝው ነባር የሆነው የእስልምና እምነት “ሱፊ” የሚባለው ነው ፤ በሁሉም በሃገራችን ክልሎች መቶ በመቶ የነበረው አማኝ ሱፊ ነበረ ፤ ሺያ የሚባል የለም ቀድሞ ነበር ፤ ሰለፊ የሚባለውም ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የመጣ ነው ፤ እነዚህ ሱፊ የሀገራችን እምነት ተከታዮች ከክርስትና ጋር ለብዙ ሺህ አመታት አብረው ኖረዋል ፤ ስርዓቶቹ የነበራቸው የአድልዎ ፖሊሲ እንደተጠበቀ ሆኖ በእስላሙ እና በክርስትያ መካከል በየትኛውም ዓለም እና ከየትኛውም ሀገር በተሻለ ሁኔታ የመቻቻል እና አብሮ መኖር የታየበት አካባቢ ነው ፤

የሰለፊ እምነት ተከታዮች ነን የሚሉ ሁሉም ባይሆኑ አንዳንዶቹ ከዚህ የተለየ አቋምና አመለካከት አላቸው ፤ እንደሚታወቀው ብዙዎቹ የአልቃይዳ አሸባሪዎች ከእምነት አኳያ የሱፊ እምነት ተከታዮች ናቸው ፤ ሰለፊዎች በሙሉ አልቃይዳ ናቸው አይባል ወንጀል ነው ፤ ነገር ግን አልቃይዳዎች ሁሉ ሰለፊዎች ናቸው ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአልቃይዳ ህዋስ ተገኝቷል ፤ አብዛኛው ባሌና አርሲ ፤ የዚህ ህዋስ አባላት የሆኑት በሙሉ ሰለፊዎች ናቸው ፤ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሰለፊዎች የአልቃይዳ አባል ናቸው ማለት አይደለም ፤ በጣም የሚበዙት አይደሉም ፤ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ የሰለፊ እምነት ተከታዮች አንዳንዶች ወሀቢ ይሏችዋል ፤ ወሀቢ የሚለው ቃል ትክክለኛ አገላለጽ ላይሆን ይችላል ፤ እነዚህ ሰለፊዎቹ በተለያየ መንገድ አንዳንድ ማኅበረ ቅዱሳን የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ታይቷል ፤ በነዚህ አክራሪዎች አማካኝነት “ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ህዝብ ሙስሊም ነው ፤ ስታስቲክስ ያቀረበው መረጃ ውሸት ነው ፤ “አብዛኛው ህዝብ ሙስሊም ስለሆነ የእስላም መንግሥት ነው መቋቋም ያለበት” የሚል ቅስቀሳ በሰፊው ነው የሚካሄደው ፤ በሙስሊሙ እና በክርስቲያኑ መካከል የቆየው መቻቻል ማውገዝና ማጥፋት ነው ስራቸው ፤ አንዳንዶቹ ሰለፊዎች እንጂ ሁሉም አይደሉም ፤ እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚያደርጉ ከሰለፊዎች ውስጥ ጫፍ የረገጡ በሀገራችን ውስጥ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ምልክቱ እየታየ ነው ፤ ከሰለፊ ውስጥ መቻቻል እንዳለ የሚገነዘብ ሃይል እንዳለ ብንገነዘብም ፤ ከነዚህ ውስጥ ግን ጥቂቶቹ ልክ ከኦርቶዶክሱም ጥቂቶቹ “አንድ ሃይማኖት አንዲት ሀገር” ብለው መፈክር እንዳራገቡ ሁሉ ፤ ልክ እንደዛው ከሰለፊዎቹም ጥቂቶቹ ይልቁንም “አንድ ሃገር አንድ ሃይማኖት” ብለው መፈክር ካሰሙት በቁጥር የሚበልጡ ሰዎች ስራ እየሰሩ መሆኑን እናውቃለን ፤ ስለዚህ ይህ ነገር በእንጭጩ መቀጨት አለበት ፤ በእንጭጩ ካልተቀጨ ግን ውጤቱን ለማወቅ ነገ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልገን ፤ በተለይም በወጣቱ አካባቢ የሕገ መንግሥቱ አስተሳሰብ ፤ አብዛኛው አለማወቅ ነው ፤ ስለዚህ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨት ስለሌለበት ሕጉን ማክበር ስላለበት ፤ ሃይማኖትና መንግሥት መለያየት እንዳለበት ፤ የሙስሊሙም ሆነ የክርስቲያኑም ሆነ የዋቄፈታም ሆነ የሌላ እምነት መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ እንደማይኖር ይህን በደንብ እንዲጨብጥ እንደ መንግሥት ስራ እየተሰራ ነው፡፡

እንደ መንግሥት ሕገ መንግሥት የማስተማር መብት አለን ፤ ስለ እስልምናም ሆነ ስለ ክርስትና ለማስተማር ግን ችሎታም መብቱም የለንም ፤ ችሎታውም መብቱም ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች ናቸው ፤ ስለዚህ እስከ አሁን ድረስ እንደ መንግሥት ምንድነው ያደረግነው ቢባል ፤ ሕግ ማስከበርና ሕገ-መንግሥት ማስተማር ነው ፤ …” በማለት ነበር የተናገሩት
ይህ ንግግር በፓርላማ ከተሰማ በኋላ ብዙዎች በአንዲቷ አገላለጽ ያልተስማሙ ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸው ነበር ፤

ከጠቅላይ ሚኒስሩ ንግግር በኋላ የተደረገ ስብሰባ

“….አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት….” በማለት በውሃቢያን እና ከሱፊዎች ጋር በመደመር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በመናገራቸው ነገሩን ለማጥራት የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮች እና መንግሥትን የሚወክሉ ኃፊዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በጊዜው የመንግሥት እና የማኅበረ ቅዱሳን ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት ውይይት ጥሩ የሚባል እና ረዥም ሰዓታትን የወሰደ ቢሆንም የስብሰባውን ውጤት ግን ከስብሰባው በኋላ ባለፉት ወራቶች በሂደት መመልከት አልቻልንም ፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ላይ በተናገሩት ነገር ላይ እና መሰል ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከ6 ሰዓት ያላነሰ ቆይታ ያለው ስብሰባ አድርገዋል ፡፡ በስብሰባው ውጤት መንግሥትን “አድሮ ቃሪያ” ከመሆን መለስ ሲል አልተመለከትንም ፡፡

በጊዜው ‹‹ደጀ ሰላም›› ስለተደረገው ስብሰባ እና ስላለው ነገር እዲህ በማለት አስፍራለች ፡-
“የማኅበሩ አመራሮች ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ባደረጉት ውይይት መንግሥት አክራሪነትንና ሌሎች የጸጥታ ስጋቶችን በተመለከተ በማኅበሩ ላይ የሚወስዳቸው አቋሞች በትክክለኛ የመረጃ ምንጭና በተገቢ የመረጃ ትንታኔ የተመሠረቱ እንዳልነበሩ ማብራራታቸውን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ÷ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ብሎጎች ላይ የሚነዙ አሉባልታዎችን መነሻ በማድረግና የመንግሥትን የደኅንነት ስጋት በመጠቀም ለድብቅ ዓላማቸው መሳካት ማኅበሩን ማጥቃት የሚሹ በየደረጃው የሚገኙ ባለሥልጣናት ስለመኖራቸው በውይይቱ ወቅት የተሰጠውን ገለጻ እንደሚያጠናክር አስረድተዋል፡፡ ይህ ዐይነቱ ውንጀላ ከውይይቱም በኋላ አንዳችም እርማት ሳይደረግበት ሰሞኑን የሃይማኖት አክራሪነትን በተመለከተ ለክልሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሠራተኞች በተጀመረውና ከመስከረም 23 2005 ዓ.ም ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባና በአዳማ በሚቀጥለው ውይይት እየተንጸባረቀ እንደኾነ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የአክራሪነትን አስተሳሰብና ተግባር በመኰነን ማኅበሩ የሃይማኖት አጥባቂነት እንጂ የአክራሪነት ትእምርት እንዳልኾነ የሚገልጹ ጽሑፎችን በማውጣት ላይ እንደኾነ ተገልጧል፡፡” በማለት አስነብባናለች

ማኅበሩም እንዲህ ብሏል
“ትናንትም ሆነ ዛሬ ምልክቱ ሰላም እንጂ “አክራሪነት” ያልሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ሀገራዊ ድርሻውን በሦስት መልኩ ተወጥቷል፡፡ የመጀመሪያው ከመጀመሪያው ጀምሮ ምእመናን አክራሪውን፣ ነባሩንና ሰላማዊውን እስልምና ነጥለው እንዲመለከቱ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ሁለተኛ አክራሪዎቹ ለሚያነሷቸው ታሪካዊና ዶግማዊ ጥያቄዎች በተጻፉት ጽሑፎች መጠንና ቁጥር ጋር ሊነጻጸር ቀርቶ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም መጠነኛ ምላሾችን ሰጥቷል፡፡ ሦስተኛ ተቻችሎና ተከባብሮ ስለመኖር ከየትኛውም አካል በፊትና በከፍተኛ ሽፋን ሠርቷል፡፡ ስለ አክራሪ እስልምናና ስለትንኮሳው እጅግ አነስተኛና ክስተት ተኮር የሆኑ መረጃዎችን በመስጠት ችግሩ ሲያጋጥም ለመንግሥት ማመልከት እንደሚገባ አቅጣጫ ለማሳየት ሞክሯል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ውላ አድራ ፍሬ እያፈራች መሆኗን የምናያቸው ነገሮች ያመላክቱናል ፡፡ አቶ መለስ የመንግሥትን አቋም የሚያንጸባረቅ ንግግር በወቅቱ አድርገዋል እርሳቸው ቢያልፉም በጊዜው ያንጸባቁት አቋም አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ኢህአዴግ በየ 15 ቀን ልዩነት ውስጥ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ምን አይነት ዘገባ እንዳወጡ ፤ በተለያዩ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ምን አይነት ዜናዎች እንደተላለፉ ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚደግፉ እና የሚቃወሙ ተቋማት በድረ ገጾቻቸው ምን አይነት ጽሁፎች እንደለጠፉ ፤ የተጻፉትን ዋና ዋና ሃሳቦችን በመልቀም ለከፍተኛው የአመራር አካል እንደሚያቀርብ እና የተነሱትን ጉዳዮችን በሚመለከት መንግሥት በየጊዜው የራሱን አቋም እንደሚይዝ ይናገራሉ ፡፡ ስለዚህ ይህ የአክራሪነት ጉዳይ አቋም የተወሰደበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በፊት ነው ፤ በተጨማሪ መንግሥት የያዘውን አቋም በ”አዲስ ራዕይ” የግንቦት እትም መጽሔት ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡

በዚያን ጊዜ የነበረውን የአክራሪነት ንፋስን መሰረት በማድረግ ኢህአዴግ በየሁለት ወሩ የሚያሳትማት “አዲስ ራዕይ”ን በተቻለን አቅም በወቅቱ ለአንባቢያ በማቅረብ ሁኔታው ለማስዳሰስ መሞከራችን የሚዘነጋ አይደለም ፡፡ 2004 ዓ.ም ክረምት ላይ በጦላይ ጦር አካዳሚ ከቀበሌ ፤ ከወረዳ እና ከክልል የተወጣጡ በሺህ የሚቆጠሩ በየደረጃው የሚገኙ ለመንግሥት ኃላፊዎችና ባለስልጣናት ምን ዓይነት ስልጠና እንደተሰጣቸው በጊዜው ገልጸናል፡፡ መንግሥት በነገሮች አቋም ሳይዝ በሺህ ለሚቆጠሩት ካድሬዎቹ ስልጠና እንደማያዘጋጅ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ከላይ ባለው አካል አማካኝነት አቋም የተወሰደበት ጉዳይ በመሆኑ እንጂ በሌላ በምንም አይደለም ፡፡ ድርጅቱ ውስጥ በየጊዜው ሀገሪቱ ላይ ስለተፈጠሩት አንኳር ጉዳዮች በማንሳት መወያየት እና አቋም የመውሰድ አካሄድ እንዳለ እጅግ የቀረቡ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ የአክራሪነትና የጽንፈኝነትን ታፔላ መለጠፍ ብሎም የመፈረጅ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ በሌላ ስብሰባ ከፍተኛ የፓርቲው አባላት ተነጋግረው ካልቀየሩት በቀር መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት ዝም ስላለ ብቻ የአቋም ለውጥ አድርጓል ማለት አንድም የዋህነት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የውስጥ አሰራራቸውን አለማወቅ መስሎ ይሰማናል፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት የያዘውን አቋም መቀየር ወይም ማለዘብ አለመቻሉን እየተመለከትን ነው፡፡ ዓመት አልፎም የሞኝ ዘፈን ይመስል በአቶ ሽፈራው የሚመራው የፌደራል ጉዳዮች መ/ቤት ከወር በፊት ሃዋሳ ላይ በተደረገው ስብሰባ ላይ ጉዳዩን ተዳፍኖ ካለበት ከሚመስለው እሳት ውስጥ የዝምታውን አመድ ፈንቅ እንዲወጣ ሲቆሰቁሱት አስተውለናል፡፡ ባለስልጣኖቻችን እየተሳሳቱ እና የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ታፔላ እየለጠፉ የሚገኙትና ትክክለኛ ያልሆነ አቋም ሲያንጸባርቁ የሚስተዋለው ከቤተክህነቱ ውስጥ ተሰግስገው አይናቸውን ሆዳቸው በሸፈኑባቸው የውስጥ ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡

የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ታፔላ ለጠፋ በአንድ ቀን ተጠንስሶ ዛሬ ላይ የደረሰ ጉዳይ አይደለም ፤ ሥረ መሰረቱ ህወሀት ጫካ በነበረበት ጊዜ ከነበረው ርዕዮተ ዓለመ ይመዘዛል፡፡ በመልክ እና በስም ተመሳሳይነት ባይኖረውም መጨረሻ ግቡ ግን ይችን ለምዕተ ዓመታት ታሪኳን ጠብቃ የኖረችን ቤተክርስቲያንን መሰረቷን መናድ ብቻ ነው፡፡ ከዓመት በፊት መንግሥት እስከ ቀበሌ በመውረድ ስለ አክራሪነትና ጽፈኝነት በየቦታው የሚገኙ ኃላፊዎች አማካኝነት ስልጠና እንደሚሰጠም ይታወቃል ፡፡ የዛሬ ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሆቴሎች ለተለያዩ ተቋማት ለ10 ቀን የተሰጠው ስልጠና እንደሚያመለክተው‹‹ኒዮ ሊበራል እና የእምነት ነጻነት ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ላይ ያለው የእምነት አመለካከት ፤ ከሕገ-መንግስቱ ጋር ያላቸው የአመለካከት ግጭት ፤ በጅማ አካባቢ የደረሰውን አክራሪነት ለምን መንግሥት እርምጃ እንዳልወሰደ ….›› እና በርካታ ነገሮችን አንስተው ተወያይተው እንደነበረ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ይህ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ታፔላ ለጠፋ ከመሬት የተነሳ እና እዚህ ደረጃ የደረሰ አለመሆኑን ያሳለፍናቸው መንገዶች ያመላክቱናል፡፡

መጥፎ ልማድ
የዛሬ ዓመት ግድም ቅዱስ ሲኖዶስ መርጦ ያስቀመጣቸውን ብጹአን አባቶቻችንን አንድ ባለስልጣን ተነስቶ የስድብ ውርድብኝ ሲያወርድባቸው ቤተክርስትያኒቱንም ሆነ አባቶችን ወክሎ መናገር የደፈሩ አባቶችን አልተመለከትንም ፤ “ቤተክርስትያኒቱ በጳጳሳቱ አማካኝነት ገደል አፋፍ ላይ ናት” ፤ ጳጳሳት እንዲህ ናቸው…” በማለት ሰውየው ሲናገር መልስ የሰጠ አካል አልነበረም ፤ ይህ የመሰለው ያለአግባብ ዘለፋ በምዕመኑ ዘንድ የሚያሳድረውን የውስጥ መሰበር ማንም አልተመለከተውም ፤ አፉን ለከፈተ ሁሉ መልስ ይሰጥ እያልን ሳይሆን ከአንድ ትልቅ የሚባልና የመንግሥትን ቁልፍ ቦታ የያዘ ሰው ያለ አግባብ ንግግር በቤተክርስቲያን እና በአባቶች ላይ ሲናገር ግን ዝም ተብሎ መመልከት ያለብን አይመስለንም ፡፡ የተሰደቡት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ጭምር መሆናቸው መዘንጋት የለበትም ፤ ዝምታችንን ጥቅሙንና ጉዳቱን በአግባቡ ያወቅነው አይመስለንም ፤ “ዝም አይነቅዝ” የሚለው የሀገራችን ብሂል የሚባልበት ቦታ እንዳለ ሁላ ዝምታም የሚነቅዝበት ውሎ አድሮም ችግር የሚያመጣበት ሁኔታም እንዳለ መዘንጋት መቻል የለብንም፡፡

ይህን ሁሉ ያነሳነው ያለ አግባብ አይደለም ፤ያለመናገራችን ምን ያህል እየጎዳ መሆኑን ለማሳየት ነው ፤ በየጊዜው ከመንግሥትም ይሁን ከተለያዩ አካላት የሚነሱትን ዘለፋዎች እና ስም ማጥፋቶች በጊዜው መልስ መስጠት ካልቻልን ውሎ አድሮ የምንሰጠው ምላሽ ውሃ ያዘለ ላይሆን ይችላል የሚል እምነትም ስላለን ጭምር ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ቤተክርስቲያኒቱ ስትሰደብ ዝም ፤ ጳጳሳቱ ሲሰደቡ ዝም ፤ ማኅበራት ስማቸው ሲጠፋ ዝም ፤ ምዕመኑም ስም እየተሰጠው ሲንገላታ ዝም ካልን ነገ ህዝቡ ላይ የሚያመጣው Psychological impact ልናጤነው ይገባል፡፡ ሰው ዝም ሲል ሁለት አይነት ምልከታ አለው አንድም “ጉዳዩ አያገባኝም ፤ ጉዳዩም ጉዳዬ አይደለም” በማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጡ እየተቃጠለና በነገሩ እየተንቦገቦገ አቅም ስለሌለው ብቻ ዝም ማለቱ ነው ፤ ብዙዎች በየትኛው ውስጥ እንዳሉ ማወቅ አዳጋች አይሆንም፡፡

መንግሥት ዘንድ የሚደርሰው መረጃ
መንግሥት ጋር የሚደርሰው መረጃ እንደሚያመላክተው ተዓማኒነት የሌላቸውና ቤተክርስቲያኒቱን ለማመስ ሌት ተቀን ከሚሰሩ የግል ጥቅማቸው ስለተነካባቸው ብቻ ከሚርመሰመሱ ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ “ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ሊቀመንብር ሆነው መመረጣቸውንና በቀጣይም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ መሆናቸው ከተገለጸ ጊዜ ጀምሮ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆናቸው ምክንያት በማኅበረ ቅዱሳን መንደርና በቤተክህነቱ አካባቢ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ግንኙነት ባላቸው አካላት ዘንድ «ጴንጤ አይገዛንም» የሚል ቅስቀሳ ውስጥ ውስጡን እየተደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡” የሚሉ መሰረት የሌላቸው ዘገቦች ናቸው፡፡ ይህ ጊዜውን ያማከለ መንግሥትን ከተቋማት ጋር ለማላተም የሚሰሩ ሰዎች መንግሥት በተቋማት ላይ የተለየ አመለካከት እንዲኖረው እያደረገ ይገኛል፡፡

በመጨረሻም
ማኅበረ ቅዱሳን÷ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ በማተኮር የተማረው ትውልድ ሃይማኖቱን የሚወድ፣ ግብረ ገብነት ያለው፣ ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን በዕውቀቱ፣ በሞያውና በገንዘቡ የሚያገለግል ብቁ ዜጋ ይኾን ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት በመሥራት ላይ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ማኅበሩ መዋቅራዊ ስፋቱን በመጠቀም ተከታዮቹን በ1997 ዓ.ም ሃገራዊ ምርጫ ላይ ተጠቅሞ ለገዥው ፓርቲ ሽንፈት ምክንያት ሆኗል በሚል መሰረተ ቢስ ውንጀላ ፓርቲውን ከማኅበሩ ለማጋጨት የሚፈልጉ ሰዎች ሥራዎቻቸው ይዘውት የሚመጡት ዳፋ ከግምት ውስጥ በማስገባ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡ መንግሥት የቆመበትን ቦታ በማስተዋል ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ ያመቸው ዘንድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግልጽ የሆነ መረጃን ያማከለ ውይይት ያደርግ ዘንድ መልዕክታችን ነው፡፡

ለመሪዎቻችን ልቦና ይስጥልን

No comments:

Post a Comment