Sunday, 9 February 2014

ከ2000 ዓመት በኋላ እንደ አዲስ እንመዘገባለን፣ እንደ አዲስም እንታወቃለን

ሰሞኑን የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ የወጣ ረቂቅ መመሪያ› የሚል ወረቀት አስተያየት ይሰጥበት ዘንድ ለእምነት ተቋማት አሠራጭቷል፡፡ ይህ መመርያ የያዛቸውን ጉዳዮች እያንዳንዳቸውን እየነጠሉ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ወደፊት የምናደርገው ይሆናል፡፡ ለአሁኑ ግን መመሪያውን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነባራዊ፣ ሉዓላዊና መንፈሳዊ ጠባያት ጋር በማዛመድ ብቻ እንመለከተዋለን፡፡

1. መመሪያው የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዩ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ ነው
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት በምድሪቱ ላይ የኖረች፣ የሰበከች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ክፉውንም ሆነ ደጉንም እኩል የቀመሰች፣ እንዲያውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ ብቻ ልዩ ጉዳት የደረሰባትም ናት፡፡ በጣልያን ወረራ ጊዜ የተሠውትን ጳጳሳትና መነኮሳት ማሰቡ ብቻ ለዚህ የቅርብ ምሳሌ ነው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሂደት ውስጥ በሀገሪቱ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ልዩ የሆነና የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሥርታ ሀገሪቱንም መሥርታለች፡፡

ይህንን ሁሉ ዘንግቶ በ2005 ዓም ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ አዲስ ተመዝገቢ፣ እንደ አዲስ ፈቃድ አውጭ፣ እንደ አዲስ ደንብና መመሪያሽን አምጭ ማለት እጅግ አሳዛኝም አስገራሚም ነገር ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ራሱ ከፈለገ መረጃ ሰብስቦ መመዝገብና ማወቅ ነበረበት እንጂ ሰነድ አምጭ፣ ደንብ አስገቢ፣ ፈቃድ አውጭና ልወቅሽ ማለት አልነበረበትም፡፡