- የማህበረ ቅዱሳን አባል የሆነ ከሀገረ ስብከት ተወክሎ ድምጽ እንዳይሰጥ ትዕዛዝ ተላፏል፡፡
- ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ያለምንም ተቀናቃኝ የካቲት ሃያ አራት 6ተኛፓትርያርክ ሆነው ይሾማሉ፡፡
(አንድ አድርገን የካቲት 19 2005 ዓ.ም)፡- የስድስተኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ባቀረባቸው አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ዙሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ እጩዎቹን በማጽደቅ ትላንት ጥር 18 2005 ዓ.ም ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል ፤ ይህ ይፋዊ መግለጫ 2791 በላይ ጥቆማዎች እንደደረሱት ገልጿል ፡፡ ለእጩነት የተጠቆሙት አባቶች በጠቅላላ 36 ሲሆኑ 15ቱ በአግባቡ ባለመጠቆማቸው እነርሱን ጥሎ አስራ ዘጠኙ ላይ በተቀመጠው የመመዘኛ መስፈርት መሰረት አምስቱን አሳልፎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኮሚቴው ያከናወነውን ስራ አባ አስጢፋኖስ እንዲህ በማለት ገልጸዋል “የአስመራጭ ኮሚቴው ከአምስት ያልበለጡ ከሶስት ያላነሱ እጩ ፓትርያርኮችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለማቅረብ ሰፊ ውይይት አድርጓል ፤ በተደረገው ውይይትም አሁን በአገልግሎት ላይ ካሉ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል 19 ሊቃነ ጳጳሳትን በቀጣይነት ለማጣራት አሳልፏል ፤ እጩዎቹን ለመለየት የተከተለው መመዘኛም እድሜና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡”በማለት ገልጸዋል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራትም አምስቱን እጩ ፓትርያርኮችን ለይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቧል ተብሏል ፡፡ እነርሱም 1ኛ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ፤ 2ተኛ ብጹዕ አቡነ ኤልሳ ፤ 3ተኛ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ፤ 4ተኛ ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና 5ተኛ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የአምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ስም የቀረበለት ቅዱስ ሲኖዶስም ማጽደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “ለመንጋው የሚሆን እረኛ እግዚአብሔር እንዲሰጠን ምዕመናን ፋጣሪያቸው በጸሎት እንዲጠይቁ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል”ብለዋል፡፡