Monday, 25 February 2013

የማኅበረ ቅዱሳን አባሎች የፓትርያርክ ምርጫ ላይ ድምጽ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ዘመቻ ተጀምሯል

  • የማህበረ ቅዱሳን አባል የሆነ ከሀገረ ስብከት ተወክሎ ድምጽ እንዳይሰጥ ትዕዛዝ ተላፏል፡፡
  •  ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ያለምንም ተቀናቃኝ የካቲት ሃያ አራት 6ተኛፓትርያርክ ሆነው ይሾማሉ፡

(አንድ አድርገን የካቲት 19 2005 ዓ.ም)፡- የስድስተኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ባቀረባቸው አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ዙሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ እጩዎቹን በማጽደቅ ትላንት ጥር 18 2005 ዓ.ም ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል ፤ ይህ ይፋዊ መግለጫ 2791 በላይ ጥቆማዎች እንደደረሱት ገልጿል ፡፡ ለእጩነት የተጠቆሙት አባቶች በጠቅላላ 36 ሲሆኑ 15ቱ በአግባቡ ባለመጠቆማቸው እነርሱን ጥሎ አስራ ዘጠኙ ላይ በተቀመጠው የመመዘኛ መስፈርት መሰረት አምስቱን አሳልፎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኮሚቴው ያከናወነውን ስራ አባ አስጢፋኖስ እንዲህ በማለት ገልጸዋል “የአስመራጭ ኮሚቴው ከአምስት ያልበለጡ ከሶስት ያላነሱ እጩ ፓትርያርኮችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለማቅረብ ሰፊ ውይይት አድርጓል ፤ በተደረገው ውይይትም አሁን በአገልግሎት ላይ ካሉ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል 19 ሊቃነ ጳጳሳትን በቀጣይነት ለማጣራት አሳልፏል ፤ እጩዎቹን ለመለየት የተከተለው መመዘኛም እድሜና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡”በማለት ገልጸዋል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራትም አምስቱን እጩ ፓትርያርኮችን ለይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቧል ተብሏል ፡፡ እነርሱም 1ኛ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ፤ 2ተኛ ብጹዕ አቡነ ኤልሳ ፤ 3ተኛ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ፤ 4ተኛ ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና 5ተኛ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ  መሆናቸው ታውቋል፡፡ የአምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ስም የቀረበለት ቅዱስ ሲኖዶስም ማጽደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “ለመንጋው የሚሆን እረኛ እግዚአብሔር እንዲሰጠን ምዕመናን ፋጣሪያቸው በጸሎት እንዲጠይቁ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል”ብለዋል፡፡ 


በአሁኑ ሰዓት እየተደረገ ያለው የፓትርያርክ ምርጫ ላይ የምርጫው ቀኑ ሲደርስ ነገሮች አይናቸውን እያፈጠጡ መጥተዋል፡፡ ሲጀመር ሰላም የመሰለው ምርጫ መጨረሻ ላይ ያልታዩ እጆች ወደ ምርጫው በግልጽም ይሁን በስውር ተሰንዝረዋል ፤ የምርጫ ሕጉን ለማጽደቅ ሲኖዶስ ሲነጋገርበት ሳለ የፓትርያርክ ምርጫው በእጣ ይሁን በድምጽ ብልጫ የሚለው ጉዳይ ሲኖዶሱን አነጋግሮም አነታርኮም ነበር ፤ በስተመጨረሻ “በድምጽ ብዛት” ተብሎ መወሰኑ የሚዘነጋ አይደለም ፤ ይህ የድምጽ ብዛት ምርጫ ቡድኖች ፤ውስጣዊ እና ውጫዊ ተጽህኖ ፈጣሪ ቡድኖች(መንግሥት) ከፍተኛውን ድምጽ ለአቡነ ማቲያስ ለመስጠት የምርጫ ስትራቴጂ እቅድ በማውጣት በሀገር ውስጥ በሚገኙ  ሀገረ ስብከቶች ስራ መጀመራቸውን ከየቦታው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ መንግሥት እጁን ከሲኖዶስ ላይ ያራቀ በመምሰል ከፍተኛው የድምጽ ባለቤት የሆኑት ላይ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል ፤ እኛ እንደደረሰን መረጃ ከሆነ ከ20 በላይ የሆኑ ሀገረ ስብከቶች ለምርጫ ወደ አዲስ አበባ የሚልኩት ሰው መስፈርት እየወጣላቸው እና ማንን መምረጥ እንዳለባቸው በግልጽ ለሀገረ ስብከቶቹ ስራ አስኪያጆች እየተነገራቸው ይገኛል፡፡ የሚላኩት ሰዎች የመጀመሪያ መስፈርት የማኅበረ ቅዱሳን አባል መሆን እንደሌለባቸው በግልጽ ተነግሯቸዋል ፡፡ መንግሥት የጀመረውን ጉዞ በማኅበር ደረጃ ቢንቀሳቀስ ይፈታተነኛል ብሎ የሚያስበውን ማኅበረ ቅዱሳንን ከጫወታ ውጪ ለማድረግ በግልጽ ቀጭን ትዕዛዝ ለሀገረ ስብከቶቹ ስራ አስኪያጆች አስተላልፏል፡፡ መልዕክቱም የማኅበረ ቅዱሳን አባል የሆኑትን ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ለፓትርያርክ ምርጫው ሀገረ ስብከታችሁን ወክላችሁ እንዳትልኩ ፤ ይህ ሆኖ ቢገኝ ኃላፊነቱን ራሳችሁ ትወስዳላችሁ፡፡” 

መንግሥት ሶስት ትላልቅ ስራዎችን አስቀድሞ ስለሰራ ምርጫውን መገመት አዳጋች የማይሆንበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ፡፡የመጀመሪያ ተቀናቃኝ ተወዳዳሪዎችን ምርጫው ውስጥ እንዳይካተቱ ማድረግ ፤ ሁለተኛው የሚፈልገውን ፓትርያርክ አምስት ውስጥ የማስገባት ሂደት ሲሆን ፤ ሶስተኛው ደግሞ በዘመቻ መራጮች ላይ ከፍተኛ ስራ መስራትን ያካትታል ፡፡ በምርጫ ማጭበርበር የተካነው መንግሥታችን በዚህ የፓትርያርክ ምርጫ ላይ እንደ 1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ኮሮጆ መገልበጥ ፤ ካርድን በጨለማ መቁጠር ፤ ኮሮጆውን ካርድ አስቀድሞ መሙላት እና በስተመጨረሻ መቀየር  ሳያስፈልገው 6ተኛውን ፓትርያርክ ፍጹም ዲሞክራሲያ እና ሁሉን ባሳተፈ ምርጫ (ቂ..ቂ…ቂ) የካቲት 21 ምርጫውን አካሂዶ ከሶስት ቀናት በኋላ የካቲት 24 በተክለሃይማኖት ቀን ፤ በእለተ ሰንበት በተክለሃይማኖት መንበር ላይ ብጹዕ አቡነ ማቲያስን 6ተኛ ፓትርያርክ አድርጎ  ይሾምልናል፡፡ 

ቀድሞ በመንግሥት ያለቀለትን የምርጫ ሂደት ፤  የተበላ እቁብ ላይ በመግለጫ መልክ ዲስኩር ማብዛት ትዝብት ላይ ይጥላል ፡፡ በዘመን ለህሊናው እና ለቤተ ክርስቲያን የሚቆም ሰው ማጣት አለመታደል ነው ፤ በመጪው የካቲት 21 ከ500 በላይ ካርዶችን ለአቡነ ማቲያስ ለመስጠት የተዘጋጁ መራጮችን አስቀምጦ አምላካችሁን በጸሎት ጠይቁ” ማለት ምን አይነት ምጸት ነው ? እናንተ ያቦካችሁትን እናንተው ጋግሩት ፤ “ማን ያቦካውን ማን ይጋግራል?”፡፡ መንፈስ ቅዱስ ይመራዋል በሚባለው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ይህን አይነት ቁማር ምን ይሉታል?፡፡ ባይሆን ምርጫው እንደ 2002 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኝት ባይጠናቀቅም ከ75 በመቶ በላይ በሆነ ድምጽ አቡነ ማቲያስ እንደሚያሸንፉ እርግጠኞች ሆነን መናገር እንችላለን፡፡ ለራስ ጥቅም በማሰብ ፤ መንበሩን እጅጉን በመመኝት በምርጫ ካልሆነ ሞተን እንገኛለን የተባለለት የፓትያርክ ምርጫ “ቂሳስ” ሊሆን የ5 ቀናትን እድሜ ብቻ ይጠብቃል ፤ ከዛ ስለ ስድስተኛ ፓትርያርክ ምርጫ አጀንዳው ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይዘጋል፡፡

የስድስተኛው ፓትርያርክ ፈተና ከዚህ ይጀምራል……..

ነገም ሌላ ቀን ነው ……….. . .. . ..ቸር ሰንብቱ

No comments:

Post a Comment