(አንድ አድርገን ጥቅምት 13 2005 ዓ.ም)፡- ባሳለፍነው ዓመት በወርሀ ግንቦት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ አንድ ወሳኝ ውሳኔ መወሰኑን ይታወቃል ፤ በውሳኔውም በርካቶች የተወገዙበት ቀሪዎቹ ደግሞ መዝገባቸው በይደር እንደቆየ የምናስታውሰው ነው ፤ በጊዜው በፕሮቴስታንቶች እየተደገፉ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት፣ ክርስቲያናዊ ትውፊትና ታሪክ በኅቡእና በገሃድ ተደራጅተው ለማፍረስና ለማፋለስ እየተንቀሳቀሱ ድርጅቶች ፍጹም ውግዘት የሚገባቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች በመለየት ማኅበረ ሰላማ፣ ማኅበረ በኵር፣ የምሥራች አገልግሎት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት፣ አሸናፊ መኰንን፣ አግዛቸው ተፈራ፣ ጽጌ ስጦታው እና ግርማ በቀለ የመሰሉት ሰዎችና ላያቸው ማር የተቀቡ ውስጣቸው ግን ነጣቂ የሆኑ ተቋማት ተለይተው መለየታቸው ይታወቃል፡፡
በጊዜው የተወገዙት ሰባቱ ድርጅቶች ውስጥ ከሣቴ ብርሃን ፤ ማኅበረ ሰላማ ፤ የምሥራች አገልግሎት ፤ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር ፤ አንቀጸ ብርሃን (ከድርጅቱ ጋራ አሸናፊ መኰንንና ዳንኤል ተሾመ) ፤ የእውነት ቃል አገልግሎት ፤ ማኅበር በኵርና የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት ይገኙበታል ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ከተወገዙት 16 ሰዎች የክህነትና የክብር ማዕርጋቸው ተሽሮ የበፊቱ አቶ የሚለው ስም ከተመለሰላቸው ውስጥ በግንባር ቀደምነት አቶ አሸናፊ መኰንን ይገኝበታል፡፡
ይህ ሰው ለዘመናት ኦርቶዶክሳዊ በመምሰል የእኛ ያልሆነ ትምህርት ኑፋቄ የተቀላቀለበት መጽሃፍቶችን በመጻፍ በርካታ ብሮችን መሰብሰብ ከመቻሉም በተጨማሪ ምንፍቅናውን በበርካታ መጽሃፍቶች መዝራት ችሏል ፤ አሁን ግን ይህ ሰው ስራው ታውቆበት ከቤተክርስትያን ከተባረረም በኋላ የመጽሀፍት ነጋዴዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መጽሀፍቶቹ ከትክክለኛ መጽሀፍቶች ጋር በመደባለቅ በገበያ ላይ ይዘዋቸው ይገኛሉ ፤ ስለዚህ ምዕመናን የዚህን ሰው ትምህርት እና መንገድ ቤተክርስትያን ስላወገዘች መጽሀፍቶቹን እና ትምህርቱን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንዲሉ “አንድ አድርገን” መልዕክቷን ታተላልፋለች፡፡ ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ መጽሀፎቹን ላያቸው ተዋህዶ ፤ ውስጣቸው ተሐድሶ የሆኑ መጻህፍት የፊት ሽፋን በመውሰድ በቀላሉ መለየት እንድትችሉ በዚህ መልክ አቅርበንላችኋል፡፡”የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።” የማቴዎስ ወንጌል 7፤15
No comments:
Post a Comment